የሣምንቱ ስፖርት | ስፖርት | DW | 25.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የሣምንቱ ስፖርት

ያለፈው ሰንበት የኢትዮጵያ አትሌቶች በተለያዩ ዓለምአቀፍ የማራቶን ሩጫ ውድድሮች ግሩም ውጤት ያስመዘገቡበት ነበር። በቶኮዮ ማራቶን ምንም እንኳ በወንዶች ድሉ የኬንያ ቢሆንም በሴቶች የኢትዮጵያ አትሌቶች የማይበገሩ ሆነው ታይተዋል።

አበሩ ከበደ 42ቱን ኪሎሜትር በሁለት ሰዓት ከ 25 ደቂቃ 34 ሤኮንድ ጊዜ በማቋረጥ ስታሸንፍ የሺ ኢሣኢያስም ሁለተኛ ወጥታለች።

በወንዶች ሶሥት ኬንያውያን ቀደምት በመሆን ከግባቸው ሲደርሱ ዴኒስ ኪሜቶ አሸናፊ፣ ማይክል ኪፕየጎ ሁለተኛ እንዲሁም በርናርድ ኪፕየጎ ሶሥተኛ ሆኗል። ኢትዮጵያዊው ፈይሣ በቀለም በዚሁ ሩጫ ስድሥተኛ ወጥቷል። በሆንግ ኮንግ ማራቶን ደግሞ በወንዶች ኬንያዊው ጁሊየስ ማይሣይ የአገሩን ልጅ ጀምስ እምቡጉዋን አስከትሎ ሲያሸንፍ የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ ደርቤ ሮቢ ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽሟል።

በሴቶች እንደ ቶኪዮ ሁሉ ድሉ የኢትዮጵያ ሲሆን ምሥክር ደምሴ ቀዳሚዋ ሆናለች። ከዚሁ ሌላ በኒው ኦርሊንስ ግማሽ ማራቶን ሩጫ የብሪታኒያው የኦሎምፒክ አምሥትና አሥር ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሞ ፋራህ በስፍራው ፈጣን ጊዜ አሸናፊ ሆኗል። ሞ ፋራህ ሩጫውን በአንድ ሰዓት ከ 59 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም አሸናፊ የሆነውም በመጨረሻዎቹ 200 ሜትሮች ገብሬ ገብረማርያምን በፍጥነት በማምለጥ ነው።

ከሶማሊያ የመነጨው የብሪታኒያ ዜጋ ፋራህ በፊታችን ሚያዚያ ወር የለንደንን ማራቶን በከፊል በመሮጥ በቀጣዩ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሙሉው ርቀት ለመሳተፍ ያስባል። ሌሎች እንደርሱ በመካከለኛ ርቀት ሩጫ ዝናን ያተረፉ ታላላቅ አትሌቶችም በማራቶን ላይ እያለሙ መሄዳቸው በየጊዜው የሚሰማ ነገር ነው። ለማንኛውም በኒው ኦርሊንስ ግማሽ ማራቶን በሴቶች መሰረት ደፋር አሜሪካዊት ተፎካካሪዋን ሻሌን ፍላናጋንን በአንድ ደቂቃ ልዩነት ከኋላዋ በማስቀረት ለማሸነፍ በቅታለች። ለኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ሰንበቱ በዕውነትም እጅግ የሰመረ ነበር።

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር ሃያላኑ ክለቦች ከሞላ ጎደል በሙሉ ቀደምት እንደሆኑ ሲቀጥሉ በተለይም በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺን አመራሩን ይበልጥ በማስፋት የማይደረስበት እየሆነ ነው። ባየርን ብሬመንን 6-1 በመቅጣት እስካሁን ባካሄዳቸው 23 ግጥሚያዎች ለ 19ኛ ድሉ ሲበቃ አመራሩን ወደ 17 ነጥቦች ማስፋቱ ሰምሮለታል። ለባቫሪያው ክለብ ማምለጥ በተለይ የጠቀመው የሁለተኛው የዶርትሙንድ ከግላድባህ 1-1 መለያየት ነው።

ሶሥተኛው ሌቨርኩዝንም በበኩሉ ግጥሚያ ከፉርት ባዶ-ለባዶ በመለያየት ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ለማለት የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ባየርንን በሣምንቱ አጋማሽ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር የእንግሊዙን ክለብ አርሰናልን 3-1 በማሸነፍ በወቅቱ ጠንካራ መሆኑን በሚገባ ማስመስከሩ አይዘነጋም። ዘንድሮ ኮሶሥት ዓመታት በኋላ መልሶ ሻምፒዮን መሆኑ የማይቀር ነው የሚመስለው። በያዝነው ሣምንት አጋማሽ በጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ከዶርትሙንድ ጋር በሚያደርገው ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያም በብዙዎች ከወዲሁ አሸናፊ ሆኖ በመታየት ላይ ነው።

በተረፈ በቡንደስሊጋው ውድድር ፍራንክፉርት ከፍራይቡርግ 0-0 ቢለያይም አራተኛነቱን እንደያዘ ሲቀጥል ፍራይቡርግ አምሥተኛ፣ ሃምቡርግ ስድሥተኛና ሃኖቨርም ሰባተኛ በመሆን ለመጨው የአውሮፓ ሊግ ውድድር ተሳትፎ ለመብቃት ዕድላቸውን እንደጠበቁ ነው። ብሬመን በአንጻሩ በባየርን በደረሰበት ሽንፈት ወደ 12ኛው ቦታ ሲንሸራተት ወደ አውሮፓው ሊጋ ዕጩዎች ሰፈር ለመመለሰ በመጪዎቹ ሁለት ሶሥት ግጥሚያዎች የግድ ማሸነፍ ይኖርበታል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ባለፈው ቅዳሜ ኩዊንስ-ፓርክ-ሬንጀርስን 2-0 ሲረታ ሊጋውን በ 12 ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። ለማኒዩ ጎሎቹን ያስቆጠሩት ወጣቱ ብራዚላዊ ተከላካይ ራፋኤልና የ 39 ዓመቱ የመሃል ሜዳ መንኮራኩር ራያን ጊግስ ነበሩ። የዩናይትድ የከተማ ተፎካካሪ ማንቼስተር ሢቲይም የአይቮሪ ኮስቱ ያያ ቱሬና የአርጄንቲናው ካርሎስ ቴቬዝ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ቼልሢይን ሲረታ በወቅቱ ሁለተኛ ነው።

ቼልሢይ ሶሥተኛ ሲሆን አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ አራተኛ የሆነው ቶተንሃም ሆትስፐር የቀረውን ግጥሚያ ዛሬ ማምሻውን ከዌስት-ሃም-ዩናይትድ ጋር ያካሂዳል። ከዚሁ ሌላ ስዋንሢይ ሢቲይ ደግሞ ትናንት በዝነኛው ዌምብሌይ ስታዲዮም በተካሄደ የሊጋ ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ብራድፎርድ ሢቲይን 5-0 በማሸነፍ ለታላቅ ድል በቅቷል። ዋንጫው በክለቡ ታሪክ የመጀመሪያው መሆኑ ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ቀደምቱ ባርሤሎናና ሶሥተኛው ሬያል ማድሪድ ሁለቱም የሰንበቱን ግጥሚያቸውን ለማሸነፍ ከኋላ ተነስተው መታገል ነበረባቸው ባርሣ ሤቪያን 2-1 ሲረታ ሬያልም ዴፖርቲቮ-ላ-ኮሩኛን በተመሳሳይ ውጤት ማሸነፉ የኋላ ኋላ ሰምሮለታል። ለባርሣ ጎሎቹን ሊዮኔል ሜሢና ዴቪድ ቪያ ሲያስቆጥሩ ተጫዋቾቹ ባለፈው ሣምንት በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር በ ኤ ሢ ሚላን ደርሶባቸው ከነበረው ሽንፈት በፍጥነት ያገገሙ ነው የሚመስለው።

ለማንኛውም የሬያል ማድሪድ የጎል ዋስትና የሆኑት ደግሞ የብራዚሉ ካካና የአርጄንቲናው ጎንዛሎ ሂጉዌይን ነበሩ። በፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ውድድር ሁለተኛው አትሌቲኮ ማድሪድም ኤስፓኞልን 1-0 በሆነች ውጤት ረትቷል። በጥቅሉ ከሰንበቱ 25ኛ ግጥሚያዎች በኋላ ባርሤሎና በ68 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን አትሌቲኮ 12 ነጥቦች ዝቅ ብሎ በ 56 ሁለተኛ፤ ሬያል ማድሪድም በ 52 ነጥቦች ሶሥተኛ ነው። ማላጋ፣ ቫሌንሢያና ሬያል ሶሢየዳድ ደግሞ ከአራት እስከ ስድሥት የሚከተሉት ናቸው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ጁቬንቱስ ቱሪን ትናንት ዝቅተኛውን ክለብ ሢየናን ያለብዙ ድካም 3-0 መርታቱ ተሳክቶለታል። ጁቬንቱስ እስካሁን ባካሄዳቸው 26 ግጥሚያዎች 58 ነጥቦችን ሲሰበስብ አመራሩን ወደ ሰባት ነጥብ ክፍ አድርጓል። እርግጥ ሁለተኛው ናፖሊ በዛሬው ምሽት ቀሪ ግጥሚያውን ከኡዲኒዘ የሚያካሂድ ሲሆን ልዩነቱ ገና ጊዜያዊ ነው። ኤ ሢ ሚላን ከኢንተር ሚላን 1-1 ሲለያይ ሁለቱ የሚላን ክለቦች ሶሥተኛና አራተኛ ሆነው ቀጥለዋል። አምሥተኛው ዛሬ ማምሻውን የጎደለ ግጥሚያውን ከፔስካራ የሚያካሂደው ላሢዮ ነው።

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ቀደምቱ ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን የቅርብ ተፎካካሪው ሆኖ የቆየውን ክለብ ኦላምፒክ ማርሤይን 2-0 ሲረታ እንግሊዛዊው ዴቪድ ቤክሃምም በሊጋው ውስጥ የሰመረ ጅማሮ ሊያደርግ በቅቷል። ሰንበቱ ሎሪየንትን 3-1 ለረታው ለሊዮንም የቀና ነበር። ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን አሁን በ 54 ነጥቦች ሊጋውን የሚመራ ሲሆን ኦላምፒክ ሊዮን ሶሥት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ይከተላል፤ ማርሤይ በ 46 ነጥቦች ሶሥተኛ ነው።

በኔዘርላንድ የክብር ዲቪዚዮን ውድድር ቀደምቱ አይንድሆፈን በሶሥተኛው በፋየኖርድ 2-1 ሲረታ አመራሩ ወደ ሁለት ነጥቦች ልዩነት ጠበብ ብሏል። ሁለተኛው አያክስ በበኩሉ ግጥሚያ ከዴን ሃግ በ 1-1 ውጤት ባይወሰን ኖሮ ከአይንድሆፈን በነጥብ እኩል ሊሆን በበቃ ነበር። ግን አልሆነም። አይንድሆፈን በ 50 ነጥቦች ይመራል፤ አያክስ በ 48 ሁለተኛ ነው። ፋየኖርድ ሶሥተኛ፤ አርንሃይም አራተኛ፤ ትዌንቴ አምሥተኛ! በተረፈ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶና ቤንፊካ እኩል ነጥብ እንደያዙ በፉክክራቸው ቀጥለዋል።

በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ በአራተኛ ቦታ የሚገኘው የስፓኙ ዴቪድ ፌሬር ትናንት አርጄንቲና ውስጥ ተካሂዶ የነበረው የብዌኖስ አይርስ ኦፕን ፍጻሜ ግጥሚያ አሸናፊ ሆኗል። ፌሬር ለዚህ ክብር የበቃው የስዊስ ተጋጣሚውን ስታኒስላቭ ቫቭሪንካን 6-4,3-6,6-1 በሆነ ውጤት ከረታ በኋላ ነው። ለስፓኙ ተወላጅ የትናንቱ ሃያኛው የፍጻሜ ድል ሲሆን ባለፉት አራት ዓመታት በብዊኖስ አይርስ ኦፕን ፍጻሜ ሶሥቴ ለፍጻሜ መድረሱም ነው።

በሜምፊስ ኦፕን ደግሞ ጃፓናዊው ኬኢ ኒሺኮሪ የስፓኝ ተጋጣሚውን ፌሊቺያኖ ሎፔዝን በለየለት 6-2,6-3 ውጤት በማሸነፍ ጠቃሚ ለሆነ ድል በቅቷል። የ 23 ዓመቱ ጃፓናዊ በዚሁ ድሌ በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ ከ 22ኛው ወደ 16ኛው ቦታ ከፍ ማለቱ ሆኖለታል። ሎፔዝም ቢሆን ለሜንፊስ ፍጻሜ በመድረሱ ደረጃውን በ 12 ቦታዎች ወደ 35ኛው ማሻሻል ችሏል።

በተቀረ ባለፈው ሣምንት መጨረሻ አዲስ አበባ ውስጥ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን የ 29ኛ አፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ተሳትፎ አስመልክቶ የምክክር መድረክ የተሰኘ የሁለት ቀናት ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። በመድረኩ ላይ ከአሠልጣኞቹና ከፌደሬሺኑ የቴክኒክ ሃላፊዎች አጠቃላይ ዘገቦች ሲቀርቡ አንዳንዶቹ በይዘታቸው ማከራከራቸውም አልቀረም። የክለብ አመራር ዓባላትም ሆኑ የፕሬሚየር ሊጉ አሠልጣኞችና ሌሎች በቀጥታ ከእግር ኳስ የተሳሰሩ ወገኖች በተለይ በስብሰባው የመጀመሪያ ዕለት በብዛት አለመገኘታቸው ተመልክቷል። ይህ ለስብሰባው አንድ ትልቅ የድክመት ምልክት ሆኖ የሚታይና ሊጤንም የሚገባው ጉዳይ ነው።

በመድረኩ ስብሰባ ለመሆኑ ከምን ተጨባጭ ግብ ለመድረስ ነበር የተፈለገው? ትክክለኛው ግንዛቤስ ነበር ወይ? ወደፊት መራመድ እንዲቻል እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ይፈልጋሉ። አንድ ሃቅ አለ!ይሄውም ኢትዮጵያ ከ 31 ዓመታት በኋላ እንደገና በአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ለመሳተፍ በመብቃት ትልቅ ዕርምጃ ማድረጓ ነው። ይህ ደግሞ በአጋጣሚ ሣይሆን በተለይም በተጫዋቾቹና በአሠልጣኞቹ ጥረት ድካም የተገኘ ውጤት መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

እርግጥ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በውድድሩ ከሩብ ፍጻሜ እንኳ አልደረሰም። ግን የዋንጫ ባለቤት የነበረችውን ዛምቢያን በአሥር ሰው ማንገዳገዱ ቢቀር የኳስ አጨዋወት ብቃት እንዳለው ያሳየ ነበር። በማጣሪያው ሂደትም ብዙ አበረታች ሁኔታዎች ታይተዋል። እርግጥ ትችት አይሰንዘር አይባልም። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አጨዋወቱን ስኬታማ ለማድረግ ሊያሟላቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች አሉ። የጎደለውን አሟልቶና አስተካክሎ ወደፊት ለመራምድ ከስህተቶች ትምሕርትን መቅሰምንም ይጠይቃል። ታዲያ የተገኘውን እንደጨበጡ መቀጠልንም እንዲሁ!

እናም አሁን ትልቁ ጉዳይ እስካሁን የተገኘውን አክብሮ መያዝ፤ ለተጫዋቾቹና ለአሠልጣኞቹ አስተዋጽኦ ተገቢውን ዕውቅና መስጠትና ሙያ እንዲቀድም ማድረግ፤ ከዚህም ጋር በደቡብ አፍሪቃው ውድድር ጎድሎ የታየውን ለማሟላት ሳይውል ሳያድር በተግባር መሰማራት ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቅርቡ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያ የሚጠብቀው ሲሆን ተጫዋቾቹ በረጋ መንፈስ እንዲዘጋጁ ዕድል መስጠት ይጠበቃል።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic