የሠርግ ድግስ ከማስዋብ ወደ ተቋም ባለቤትነት | ባህል | DW | 25.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የሠርግ ድግስ ከማስዋብ ወደ ተቋም ባለቤትነት

አስር ሚሊዩን ሰዎች፡፡ ሰላሳ አምስት ሺህ ዝግጅቶች፡፡ 160 ሀገሮች፡፡ እነዚህ ከዓለም አቀፍ የሥራ ፈጠራ ሳምንት ክንውኖች ጀርባ ያሉ እውነታዎች ነው፡፡ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ከሚከበረው ሳምንት ውስጥ አጓጊው የዓመቱ ወጣት የሥራ ፈጣሪዎች ውድድር እና አሸናፊውን የማሳወቅ ሥነ-ስርዓት ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:51

የዓመቱ ወጣት የሥራ ፈጣሪ

ዓለም አቀፉን ሁነት ከአምስት ዓመት በፊት የተቀላቀለችው ኢትዮጵያም ባለፈው ሳምንት በሴት እና ወንድ ምድብ አሸናፊዎችን አሳውቃለች፡፡በወንዶች ምድብ የዓመቱ ወጣት የሥራ ፈጣሪ በመባል ዕውቅና ያገኘው ነዋሪነቱ እና ሥራውን በባህርዳር ከተማ ያደረገው ደሳለኝ ሸዋንግዛው ነበር፡፡ የሴቶቹን ምድብ ደግሞ የአዲስ አበባዋ ምህረት ምትኩ አሸንፋለች፡፡ ምህረትን ብዙዎች መርሲ በሚል ነው የሚያውቋት፡፡ በቁልምጫ ስሟ በሰየመችው የዲኮር ድርጅቷ እና የዲዛይን እና ሞዴሊንግ ማሰልጠኛ ተቋሟ 500 ገደማ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥራለች፡፡ 

የ28 ዓመቷ ምህረት ከዲኮር ሥራ ጋር የተዋወቀችው ገና የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለች ነበር፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ እናቷ በቤት ውስጥ የሚያደርጉትን የሚያጊያጌጥ ሥራ ልብ ብላ ትመለከት ነበር፡፡ በተለይ በገና ወቅት የሚሰሩትን ቤት የማሳመር ሥራ አትረሳም፡፡ እንደርእሳቸው ነገሮችን የማቆንጀት ፍላጎት ቢኖራትም ትኩረቷን ትምህርቷ ላይ አድርጋ ቆየች፡፡ ጠበቃ የመሆን ህልም ነበራት፡፡ 

“መጀመሪያ እኔ ትምህርት ቤትም ስገባ ጠበቃ መሆን ነበር የምፈልገው፡፡ የሆነ የቤተሰብ ጉዳይ ነበረብን እና ለአባቴ ተከራክሬ አስፈጽምልሃለሁ እለው ነበር” ትላለች ምህረት ስለ ልጅነት ምኞቷ ስታስታውስ፡፡ 

የዛሬ ሰባት ዓመት ግን ህይወቷን የለወጠ አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ምህረት የቅርብ ዘመዷ ሊያገባ እንደሆነ ሰማች፡፡ በድፍረት ወደ እርሱ ዘንድ ሄዳ የሰርግ የዲኮር ሥራውን እርሷ ልትሰራለት እንደምትፈልግ ትነግራዋለች፡፡ ዘመዷ ወዲህ ዝምድናው ወዲያ ደግሞ ወጪ መቆጠቡ ይገፋዋ እና እሺታውን ይሰጣታል፡፡ ስለ ሰርግ ማጊያጌጥ ፍላጎት እንጂ ምንም የምታውቀው ነገር ያልነበራት ምህረት አፍንጮ በር ትምህርት ቤቷ ደጃፍ የሚገኝን አንድ የዲኮር ቤት መማሪያ ታደርገዋለች፡፡ 

የትምህርት ቤት የደንብ ልብሷን እንደለበሰች ወደ ሱቁ ገብታ ለሰርግ ዕቃዎችን መከራየት እንደምትፈልግ ትናገራለች፡፡ ማጊያጌያጫዎችን እያገላበጠች እና ዋጋ እየጠየቀች ቆይታ፣ የ500 ብር ዕቃ ልትከራይ ተስማምታ ወደ ዘመዷ ትመለሳለች፡፡ ጨርቆች፣ መጋረጃዎች እና ፊኛዎች ይዛ እዚያው ሰፈሯ አቅራቢያ በነበረ መናፈሻ የሚደረገውን የዘመዷን ሰርግ ዲኮር በመሥራት ሀ አለች፡፡ ምህረት የመጀመሪያ ጊዜያዋን አንዲህ ታስታውሳለች፡፡ 

“መቼም መጋረጃ እንደመስቀል በለው፡፡ ሰቀልነው፡፡ በዚያ ሰዓት ላይ ፊኛው መታሰሩን ብቻ ነው ያየነው፡፡ ጨርቆች ተጠቀምኩ እና ሁሉም ሰው በጣም ያምራል [አለኝ]፡፡ ቤተሰብም ስለሆኑ ሊሆን ይችላል በጣም ቆንጆ ነበር አሉኝ፡፡ አሃ! ስለዚህ ይህ ካደገ ጥሩ ነገር ይመጣል አልኩ፡፡ ብቻ በእንደዚህ አይነት ቀጠልኩበት” ስትል የመጀመሪያ ሙከራዋን በፈገግታ ትተርካለች፡፡    

በመጀመሪያ ሙከራዋ ከሰፈርም፤ ከዘመድም አድናቆትን ያገኘችው ምህረት ይህንን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሸጋገር እንዳለባት ትወስናለች፡፡ የዲኮር ሥራን በንግድ ቤት ደረጃ ለመሥራት  አዲስ አበባ  ሰሜን ሆቴል አካባቢ ያለ የቤተሰቧን ሱቅ ታስፈቅዳለች፡፡ ውጥኗን ዕውን ለማድረግ የመጀመሪያ እርምጃዋ ወደ መርካቶ ሄዶ ዓይነ ገብ ጨርቅ መግዛት ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙ ገንዘብ አልመደበችም፡፡ ያላትን 100 ብር ብቻ አንጠልጥላ መርካቶ ወረደች፡፡ 

የገዛቸውን ጨርቅ የሯሷን ፈጠራ ተጠቅማ አሰማመረችው፡፡ ለየት ያለ አሰሯሯ አላፊ አግዳሚውን እየሳበ ወደ ንግድ ቤቷ ጎራ እያለ መጠየቅ ጀመረ፡፡ ሰርግ የሚደግሱ ሰዎች አንድ ሁለት እያሉ ወደ እርሷ መምጣት ጀመሩ፡፡ እርሷም ቀብድ እየተቀበለች፡፡ በምታገኘው ገንዘብ ዕቃዎችን እየተከራየች እና እየገዛች በአንድ እግሯ ቆመች፡፡ 

“መነሻዬ ራሱ ከሰዎቹ ላይ ነው፡፡ ገንዘቡን ራሱን እየሰበሰብኩ ነው ዕቃ የኖረኝ፡፡ በሶስት ወሩ ሙሉ ዕቃ ኖረኝ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በሁለት ወር ውስጥ ወዲያው ነበር ወደ ሶስት ሺህ ብር የኖረኝ ግን ሁሉም ስራ ላይ ናቸው፡፡ እጄ ላይ ምንም ብር አልነበረም” ትላለች፡፡

እንዲህ እንዲህ እያለች ጥረቷን የተመለከቱ ሰዎች እያገዟት ሥራውን ታቀላጥፍ ያዘች፡፡ ነገሮች የተሳኩላት ቢመስልም እርሷ ግን ባገኘችው ስኬት ረክታ መቀመጥ አልፈለገችም፡፡ የተሻለ ነገር ፍለጋ ወደ አቢሲኒያ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ገባች፡፡ እዚያ ለዲኮር ሥራ የሚያስፈልጉ የጥበብ ዕውቀቶችን መቅሰም ጀመረች፡፡ ኮላጅ፣ ቀለም፣ መስመር እያለች ከአስተማሪዋቿ ከምትማረው በሻገር ከጥበብ ጋር ያልተያያዘ ሌላም ነገር ልቅም አድርጋ በደብተሯ ትመዝገብ ቀጠለች፡፡ 

የመማሪያ ደብተሯን የሞላው የአንድ ትምህርት ቤት የዕለት ተዕለት አሰራር እና አወቃቀር ነበር፡፡ ባገኘችው ትርፍ ጊዜ ደግሞ ከአስተማሪዎቿ ጋር ስለ የስርዓተ ትምህርት «ካሪኩለም» አነዳደፍ፣ የትምህርት አስተዳደር እና መሰል ጉዳዩች መወያየቷን አልረሳችም፡፡ የጀመረችውን የትምህርት ቤት አሰራር ጥናት ለተጨማሪ ትምህርት እንጦጦ አጠቃላይ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ስትገባም ገፋችበት፡፡ ከሁለቱ መማሪያ ቦታዎቿ የሰበሰበቻቸው ተሞክሮዎች ሜርሲ የዲኮር ዲዛይን ማሰልጠኛ ተቋምን ወለደ፡፡ ምህረት የማሰልጠኛ ተቋም ለምን መክፈት እንደፈለገች እንዲህ ታስረዳለች፡፡ 

“በየቦታው ስትሄድ ሰው ‘ወይኔ ዲኮር መማር እኮ እፈልግ ነበር፤ ትምህርት ቤት እኮ የለም ’ ይለኝ ነበር፡፡ እና እኔ ደግሞ የመጣሁበት መንገድ ረጅም ነበረ፡፡ ለሰው በቀለለ መንገድ ብታሳይ ለሌላ ሰው ስራ ይሆናል፤ ይቀልለታል፡፡ እና አንድ ሰው ማሰራት እንኳ ስትፈልግ አንተ አሳይተኸው፣ በሂደት ነው ወደ ዲኮር ስራ የምትቀይረው፡፡ ትምህርት ቤት ቢኖር ግን የተማረ ሰው የፈለግኸውን በቀላሉ ሊሰራልህ ይችላል፡፡ እንደገና ደግሞ ሰው የራሱን ፍላጎት በቀላሉ ማውጣት ይችላል” ስትል የማሰልጠኛ ተቋሙን መነሻ ታብራራለች፡፡ 

የማሰልጠኛ ተቋሙ በ2005 ዓ.ም ሥራውን ሲጀመር የስድስት ወር የዲኮር ትምህርት በመስጠት ነበር፡፡ የሰልጣኞችን ፍላጎት በመመልከት ግን በአሁኑ ወቅት ከአንድ ወር ከ15 ቀን እስከ አራት ወር የሚዘልቁ ትምህርቶችን ያስተምራል፡፡ በዲኮር የተጀመረው ስልጠናም በስተኋላ ላይ ፋሽን ዲዛይን እና ሞዴሊንግን ጨምሯል፡፡ በአዳማም ቅርንጫፍ እስከመክፈት ተጉዞ ነበር፡፡  

ስምንት ሰራተኞች ያሉት ተቋሙ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን 500 ገደማ ወጣቶችን አስተምሯል፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎች ወጣቶች ሲሆኑ ከባህርዳር፣ መቀሌ እና ሀረር ጭምር እየመጡ እንደሚማሩ ምህረት ትናገራለች፡፡ በመቀሌ ተወልዳ ያደገችው የ26 ዓመቷ ዮርዳኖስ ሲያስብ ከእነዚህ ውስጥ አንዷ ናት፡፡ 

ዮርዳኖስ ከአራት ዓመት በፊት ዘመድ ጥየቃ ወደ አዲስ አበባ በመጣች ጊዜ የትምህርት ቤቱን ማስታወቂያ ትመለከታለች፡፡ ከእርሷ በፊት የተማረች ጓደኛዋን ታማክራና ወደ ተቋሙ ለስልጠና ትገባለች፡፡ የስድስት ወር ትምህርቷን ስትጨርስ ወደ መቀሌ ተመልሳ የራሷን ሥራ ለመክፈት ትወስናለች፡፡ የትምህርት ቤት ቆይቷዋን እንዲህ ታጋራለች፡፡

“በእዚያ የነበረኝ ቆይታ በጣም ደስ ይል ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ እዚህ መጥቼ ዮርዲ ዲኮር የሚባለውን የእኔን ስራ [ከፈትኩ]፡፡ ከእኔ ጋር የሚሰሩ አራት [ሰራተኞች] አሉኝ፡፡ አሪፍ ትምህርት ስላገኘሁም ይመስለኛል ቶሎ ወደዚህ ስራ የገባሁት፡፡ በራስ መተማመን ነበረኝ” ትላለች፡፡

“እንደ እህቴ ነው የምቀርባት” ስለምትልላት የቀድሞ አስተማሪዋ ምህረት ደግሞ ተከታዩን ብላለች፡፡

“ዲኮር ልከፍት ስሄድ ራሱ እንዴት እንደተባበረችኝ ልነገርህ አልችልም፡፡ በጣም ነው የምታግዝህ፡፡ መርካቶ ሄዳ ዕቃ አጋዛችኝ፡፡ ከአስተማሪ በላይ የምትሆንልህ ነገር አለ፡፡ በጣም ጥሩ ሰው ናት፡፡ አሁንም እደውልላታለሁ የሆነ ነገር ስፈልግ፡፡ አዲስ ነገር ሲኖር እየደወለች ትነግረኛለች፡፡ እኔም አዲስ አበባ ስሄድ እጠይቃታለሁ” ስትል ከመቀሌ በስልክ ለዶይቸ ቨለ ተናግራለች፡፡   

 በተማሪዋቿ እንዲህ የሚመሰክርላት ምህረት ወጣት የሥራ ፈጣሪዎችን ባወዳዳሩ ዳኞችም የአሸናፊነት አክሊል ተቀዳጅታለች፡፡ ዓለም አቀፍ የሥራ ፈጠራ ሳምንትን አስመልከቶ የኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ማዕከል በሚያዘጋጀው ውድድር ላይ ተሳትፋ አሸንፋለች፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በአዲስ አበባ በተከናወነ የሽልማት ሥነ-ስርዓት ላይ የዕውቅና ሽልማቷን ከተጋበዙ እንግዶች እጅ ተቀብላለች፡፡ በዳኝነት የተሳተፉትና በማዕከሉ የንግድ ምክር አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሀና ፈለቀ ምህረትን ለሽልማት ያበቋትን መስፈርቶች ይዘረዝራሉ፡፡

“ምህረት የተመረጥችባቸው ሰባት መስፈርቶች ነበሩ፡፡ የስራ ፈጠራ ክህሎት፣ የስራ ህብረት፣ የአካባቢ አስተዋጽኦ፣ ፈጠራ፣ ተአማኒነት እና የስራ ዕድገት ሁኔታ ናቸው፡፡ በእነዚህ መስፈርቶች ውይይት ተደርጎ ነው ምህረት የተመረጠችው” ይላሉ ወ/ሮ ሀና፡፡

እንደ ዮርዳኖስ ላሉ ሥራ ፈጣሪዎች መንደርደሪያ የሆነው የማሰልጠኛ ተቋም ምህረትን ቢያሸልማትም ክፉኛ ግን ፈትኗታል፡፡ ወደ ዲኮር ሥራ ስትገባ ካጋጠማት ተግዳሮት ይልቅ ተቋሙን ለመክፈት ላይ ታች ስትል የገጠማት ፈተና ብዙ እንደነበር ትናገራለች፡፡ ከተከፈተ ከአንድ ዓመት በኋላ ዕውቅና ያገኘው ተቋሟ ጎን ለጎን እንደምትሰራው እንደዲኮር ሥራዋ አትራፊ እንዳልሆነ ታስረዳለች፡፡ ነገር ግን ማስተማሯን ትወደዋለች፡፡ እርሷ ጋር የተማሩ ወጣቶች ራሳቸውን ችለው መየቷ ትልቁ ደስታዬ ነው ትላለች፡፡ 

“ማስተማር በጣም ደስ ይላል፡፡ ምንድነው ደስ የሚለው ነገር? ሰው የራሱን ስራ አግኝቶ፣ ከተቀጣሪነት ወጥቶ፣ የራሱን ገንዘብ ማግኘት ሲጀምር እነዚያ ሰዎች መጥተው የሚሉህ ነገር አለ፡፡ ፍቅራቸው ራሱ ለየት ያለ ነው የሚሆነው፡፡ ራሱ የሚያሳዩህ ነገር ራሱ በጣም ነው ደስ የሚልህ፡፡ ለምን ያውቁታል? ብዙ ዓይነት ዲኮር ቤት አለ፡፡ ከእነሱ ጋር ሄደው ነው የሚስተካከሉት እና ስራ ይሰራሉ፡፡ እነዚህ ልጆች እነሱ ብቻ ሳይሆኑ እነሱ ጋር  ቢያንስ ስድስት ሰው ይሰራል፡፡ አብረዋቸው የተማሩም ይኖራሉ፣ አዲስም ሰው ሊቀጥሩ ይችላሉ፡፡ አንድ ዲኮር ስትሰራ ብቻህን አይደለም፡፡ ቢያንስ ከአምስት እስከ 10 ሰው ይኖራል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ያንን ሰው ጠቀመ ማለት ነው” ትላለች፡፡    

ምህረት የዲኮር ሥራዋ ተስፋፍቶ ከአንድም ሁለት ቅርንጫፍ ከፍታ አይታዋለች፡፡ የማሰልጠኛ ተቋሟ መቶዎችን ሲያስመርቅ ደስታቸውን ተጋርታለች፡፡ አሁንም ግን ማለሟን አላቋረጠችም፡፡ ማሰልጠኛዋ የራሱ ህንጻ ኖሮት ወደ ኮሌጅ አድጎ የማየት ፍላጎት አላት፡፡ ያኔ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር የመሥራት አላማም አላት፡፡ ድፍረት እና ጽኑ ፍላጎት የሰነቀችው ወጣቷ ህልሟን እንደምታሳካ ታምናለች፡፡   

ተስፋለም ወልደየስ 
አዜብ ታደሰ 

Audios and videos on the topic