የሠላም ቃል-የጦርነት ምግባር ምድር | ዓለም | DW | 06.01.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሠላም ቃል-የጦርነት ምግባር ምድር

ኢራቅ፥ ሶሪያ፥ ግብፅ፥ ሊቢያ፥ ቱኒዚያ ሠላም ለማዉረድ ወይም ለማደራደር ያንዳቸዉም ድምፅ አለመሰማቱ ነዉ-ትዝብቱ።የአሜሪካኖችም ጭምር።ለዝንተ-ዓለም ሠላም በያዉቀዉ ምድር፥ አንፃራዊ ሠላም የነበራቸዉ ሐገራት ሠላምን እያጠፉ ፍልስጤም እስራኤሎች ተነጥለዉ ሠላም ማዉረድ ከቻሉ በርግጥ ከተዓምር የሚቆጠር ነዉ።

ሶሪያ እልቂት ዘርታ ጥፋት እያጨደች አስከሬን ትወቃለች።ኢራቅ ሽብር አንግሳ፣ ሙቷን ቀብራ፣ ሌላ ጥፋት በሽብር እጊጣለች።ሊባኖስ ሰላሟን-ከሽብሯ ቀይጣ በዉድቀት፣ትንሳኤዋ መሐል ትፈራገጣላች። ግብፅ የዜጎችዋ ትግል፣የሸነቆረዉን የዲሞክራሲ ጭላጭሏን በመፈንቅለ-መንግሥት መርጋ፣ ለመለሰን የዜጎቿን ሥጋ በዜጎችዋ ደም ታቦካለች።ሊቢያ፣ የጠገበ እየገደለ፣ እየዘረፈባት በየአዉራጃዉ ነግሶ-ሰነጣጥቋታል።የዶሐ፣ የሪያድ፣ የአንካራ ሐይለኞች ሶሪያ ላይ እንደወዳጅ፤ ግብፅ ላይ እንደ ጠላት እልቂት ጥፋቱን ያጋግሙታል።መካከለኛዉ ምሥራቅ ሠላም አልነረም።የለምም።ያ ምድር ከሠላም የራቀበትን ጎዳና ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የቀየሰችዉ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ሠላም ሊያስፍኑለት አስሬ ተመላለሱበት።የኬሪን አስረኛ ተልኮ ከአካባቢዉ እዉነታ ጋር እያጣቀሰን ላፍታ መካከለኛዉ ምሥራቅ እንበል።አብራችሁኝ ቆዩ።እስራኤል በተለየያ ወንጀል የምትጠረጥራቸዉ ወይም የፈረደችባቸዉ አምስት ሺሕ ፍልስጤማዉያንን አስራለች።በዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ አግባቢነት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከአምስት ሺዎቹ እስረኞች ሃያ-ስድስቱን ባለፈዉ ሰኞ ለቀቁ።እስረኞቹ በርግጥ ተደሰቱ።«እባካችሁ፥ የእኔ መፈታት በጥሩ ሁኔታ ነዉ የተደረገዉ አቡ ማዝን (አባስን) እና የፍልስጤም መስተዳድርን አመሰግናለሁ።በእስረኞች ጉዳይ ብዙ ጥረዋል።»

ከተለቀቁት አንዱ ኢብራሒም ታኩኩ።ሌላዉ ቀጠሉ፥-

«ያለንበት ሁኔታ መጥፎ ቢሆንም እስረኞቹን የማስፈታቱ ሒደት በተገቢዉ መንገድ ጥሩ እርምጃ ነዉ።ፍልስጤማዉያን እስረኞች በሙሉ ሳይፈቱ የመጨረሻ ስምምነት እንደማይኖር አቡ ማዝን ሁል ጊዜ ሲናገሩ እንሰማለን።»

የተለቀቁት እስረኞች ወላጅ፣ ወዳጅ፣ ዘመዶቻቸዉ ፈነደቁ።ደስታ፥ ቡረቃ ፍንደቃዉ በርግጥ የዕለት ደግሞም የጥቂቶች ነዉ።ያም ሆኖ ለሕዝባቸዉ የተስፋ-ደስታ፣ የድል፣ ገድል ምግባር ከዉነዉ የማያዉቁት፥ ወይም መከወን የማችሉት ፕሬዝዳት ማሕሙድ አባስና ባለሥልጣናቸዉ ደስታ ከማያዉቀዉ ሕዝባቸዉ የጥቂቱን ያፍታ ደስታ፥ ሕዝባዊ ድጋፍ ለማግኘት የማይጠቀሙበት ምክንያት አልነበረም።

እስረኞቹ እንዳመሰገኗቸዉ ሁሉ የፍልስጤም መሪዎችም የጥረታችን ዉጤት፣ የትግላችን፣ ድል እያሉ ደስታዉን ተቋደሱ።እንደተባለዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስረኞቹን የለቀቁት ለሰላም ሲሉ ነዉ።ለሠላም የቆመ እስረኛዉን መልቀቅ አይደለም ደመኛዉን ይታረቃል፥ ጠላቱን ይቅር ይላል ወንጀለኛን ይምራል።ለዚሕ ማንዴላን መሆን አያስፈልግም።ይሕን ያደረገ እሱ የሰላም ጀግና፥ ከማንም በላይ ደስተኛ በሆነ ነበር።

ኔታንያሁ ግን ከአምስት ሺሕ ወገኖቹ የሃያ ስድስቱ ብቻ መለቀቅ ለዝንተ ዓለም ደስታ ከማያዉቀዉ ፍልስጤም ጥቂቱ ያዉም ለቅፅበት በመደሰቱ ተናደዱ፣ ተቆጡ፤ አወገዙም።ኔታንያሁ በሒብሩ በረጅሙ ያዥጎደጎዱትን ቁጣ-ዉግዘት ቃል አቀባያቸዉ ማርክ ሬጌቭ በእንግሊዝኛ ባጭሩ ደገሙት።

«ትናንት ማታ የፍልስጤም መስተዳድር አሸባሪዎችን ሲያወድስ አይተናል።ንፁሕ ሰላማዊ ሰዎችን ፥ ሕፃናትን የገደሉ ወንጀለኛ ግለሰቦችን ሲያደንቁ ነበር።አሁን፥የፍልስጤም መስተዳድር አሸባሪነትን ማወደሱን የሚያቆምበት ጊዜ ነዉ።ሽብርን ማሞገሳቸዉን የሚያቆሙበት ጊዜ ነዉ።»

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ እዉቅ ሴናተር፥ የቀድሞዉ እጩ ፕሬዝዳት ጆን ኬሪ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ከያዙ አስራ-አንድ ወራቸዉ ነዉ።ባለፉት አስራ-አንድ ወራት እንደ እስራኤልና ፍልስጤም የጎበኙት ሥፍራ የለም።እስከ ትናንት የዘለቀዉ ያሁኑ ጉዟቸዉ አስረኛዉ ነዉ።የሁሉም ጉዟቸዉ ዓላማ አንድ ነዉ።እስራኤልና ፍልስጤሞችን ማደራደር።

በአስሬ ጉዟቸዉ እስካሁን በተጨባጭ የተሳካላቸዉ ከአምስት ሺሕ የፍልስጤም እስረኞች ስምምነቱ ከያዘ ከመቶ ጥቂት በለጥ የሚሉትን ማስለቀቃቸዉ ነዉ።የእስራኤል መሪዎች ተደራዳሪዎቻቸዉን በአሸባሪ ደጋፊና አወዳሽነት እያወገዙ፥ ፍልስጤሞች ለድርድሩ አለመጀመር እስራኤሎችን እየወቀሱ ኬሪ ግን ተስፋ አለ ይላሉ።

«ተመልሼ መጥቼ የሚቀጥለዉን እርምጃ ለመዉሰድ የሚያስፈልገዉን መሠረት ለመጣል ቡድናችን መስራቱን ይቀጥላል።ሥለዚሕ ይሕ ከባድ ሥራ ነዉ።»

ለክብደቱ የሰጡት ምክንያት የለም።ፍላጎት ካለ የሚከብድበት ምክንያትም ግን ግልፅ አይደለም። ፍልስጤም እና እስራኤሎች «የማይታሰብ» የነበረዉን ድርድር የጀመሩት በ1991 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ነበር።ሁለቱ ወገኖች ድርድር የጀመሩት ለመደራደር ሥለ-ፈለጉ ወይም ሥላልፈለጉ አልነበረም።ድርድሩን ፈልገዉት ከነበረ የፈለጉትን፥ ካልፈለጉትም እንዲፈልጉት ያደረገዉ ከሁለቱ ወገኖች ዉጪ የነበረ እዉነታ ነበር።በ1990 የያኔዋ ጠንካራ፥ ሐብታም፥ አረባዊት ሐገር ኢራቅ አረባዊ ጎረቤትዋን ኩዌትን ወረረች። ወረራዉን በሐይል ለመቀልበስ ያቀዱት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ጆርጅ ሐዋርድ ዳብሊዉ ቡሽ (ቀዳማዊ) ኢራቅን ለመዉጋት የዓለም፥ ዓረብን ሲያስተባብሩ ከየአረብ ገዢዎች ይቀርብ የነበረዉ ጥያቄ «የፍልስጤሞች ጉዳይስ» የሚል ነበር።

ከሁሉም በላይ የያኔዉ የፍልስጤም ነፃ አዉጪ ድርጅት ሊቀመንበር ያሲር አረፋት ዓለም ለጥፋታቸዉ ካበረባቸዉ ከኢራቅ ፕሬዝዳት ከሳዳም ሁሴን ደረት ላይ ተለጥፈዉ ለሳዳም ያላቸዉን ድጋፍ አረጋገጡ።የአረፋት ዲፕሎማሲ፥ የሳድም አቅም ጦርነቱን ከኢራቅ አሜሪካነት ይልቅ የአሜሪካ-እስራኤል እና የአረቦች ጦርነት ያደርገዋል ብለዉ የፈሩት ቡሽ እስራኤሎች ከፍልስጤሞች ጋር እንዲደራደሩ የማስገደድ ያክል ገፋፉ።

ጥቅምት ሠላሳ-1991 የመጀመሪያዉ የፍልስጤም እስራኤሎች ጉባኤ ማድሪድ-ስጳኝ ተጀመረ።ኋላ ለበጎ ይሁን ለመጥፎ ኦስሎ ላይ ለተፈረመዉ ስምምነት ያደረሰዉ የሚስጥር ድርድር ቀጠለ።ከዚያ በኋላ ብርዥ ጥርዥ የሚለዉ ድርድር በቀጠለበት ዘመን፥ አረፋት በየድርድሩ መሐል የሚሔዱ፥ የሚያማክሩት አላጡም ነበር።

ዛሬ አረፋት የሉም።ሳዳም ሁሴይን የሉም።ኢራቅም በአዲስ አበባ አራዶች ቋንቋ «ቀባሪ አጣች» እንጂ ሞታለች።ወይም ለመቀበር ባግዳድ፥ ባስራ፥ ኪርኩክ፥ በሌሎችም ከተሞቿ በቦምብ ትጋያለች።ሰሞኑን ደግሞ የእልቂት ፍጅት ዛሯ ረማዲና ፋሉጃ ላይ ያስደልቃታል።ምክንያት፥-ጀርመናዊዉ የፖለቲካ አዋቂ ጊዶ ሽታይበርግ ዉስብስብ ይሉታል።

«በመጀመሪያ ረማዲና ፋሉጃ ላይ የተቀጣጠለዉ ዉጊያ የተጫረዉ መንግሥት ታዋቂዉን የሱኒ የምክር ቤት እንደራሴ አሕመድ አል አላዋን ለማሰር በመሞከሩ ነዉ።ሙከራዉ ተቃዉሞ እና ግጭት አስከትሎ ነበርም።አል-ቃኢዳ ይሕን አጋጣሚ ተጠቅሞ ተዋጊዎቹን ወደነዚሕ ከተሞች አዝምቷል።ያም ሆኖ ብዙ ሱኒዎች ራሳቸዉ አል-ቃኢዳን አሁንም ይቃወማሉ።ሥለዚሕ ጉዳዩ የሺዓ እና የሱኒዎች ጠብ ተብሎ በቀላሉ ከሚታየዉ ግጭት በጣም የተወሳሰበ ነዉ።»

Friedesprozess in Oslo 1993

ራቢን፤ክሊንተንና አረፋት

ግብፅ እንደ ኢራቅ በርግጥ ለሞት እያጣጣረች አይደለም።ግን ለፍልጤም-እስራኤሎች ልትተርፍ ቀርቶ እራሷም እንደ ሐገር አልቆመችም።ሐገሪቱን ከ1952 ጀምረዉ የገዙት የጦር ጄኔራሎች በሕዝብ የዘመናት ትግል፥ አመፅ የተቀሙትን ሥልጣን ባለፈዉ ሐምሌ በመፈንቅለ መንግሥት ከነጠቁ ወዲሕ ዴሞክራሲ፥ ፍትሕ፥ ነፃነት፥የሚጠይቀዉን ሁሉ ባደባባይ እያስገደሉ፥ ሌላዉን እያሳሰሩ፥ ተቋማትን እየዘጉ ጠንካራ፥ ጥንታዊ፥ የብዙ ሕዝቦችን ሐገር ቁል ቁል እየደፈቋት ነዉ።

ማሕሙድ አባስ ከረመላሕ ጓዶቻቸዉ ዉጪ መካሪ ጠንካራ መሪ የላቸዉም።የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪም ካይሮ ላይ የሚያማክሩት የለም።አማን ሔዱ።ሆስኒ ሙባረክን ከሥልጣን ያስሸቀነጠረዉን ዓይነት ሕዝባዊ አመፅን ለማፈን የሚባትሉት፥የሶሪያዉን ጦርነት በማጋጋም፥ ስደተኞችን በማስተናገድ ሽቅብ ቁል ቁል የሚሉት የዮርዳኖስ ነገሥታት ሥለ ፍልስጤም እስራኤሎች ድርድር የሚጨነቁት ከድርድሩ መቀጠል-ወይም አለመቀጠል የሚያተርፉት ካለ ብቻ ነዉ።

የኬሪ ሁለተኛ ጉዞ ሪያድ ነዉ።እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ሁሉ የሶሪያ አማፂያንን የሚደግፉት የሪያድ ነገሥታት ዘግናኙን ጦርነት ለማቀጣጠል ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር እየከሰከሱ ነዉ።በሕዝብ የተመረጡትን የግብፅ መሪን በመፈንቅለ መንግሥት ላስወገዱት የጦር ጄኔራሎችም ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር እያንቆረቆሩ ነዉ።በየሐገሩ ድሕነት ጠንቶበት ሠርቶ ለመኖር ከሐገራቸዉ የገባ ሥደተኛን ግን እያባረሩ ነዉ።

የፍልስጤም እስራኤልን ድርድር ከቀጠለ ላለፉት ሃያ-ሰወስት ዓመታት እንደተነገረዉ የመጨረሻ ግቡ ፍልስጤሞች ከእስራኤል ጋር በሠላም የሚኖር መንግሥት እንዲመሠርቱ ማድረግ ነዉ።የፍልስጤሙ ዋነኛ ተደራዳሪ ሠዓብ ኢቃት ይሕ እንዳይረሳ በቀደም ደገሙት።

«እስከ 1967ት በነበረዉ ድንበር መሠረት፥ ከእስራኤል መንግሥት ጋር ጎን ለጎን በሠላም የሚኖር የፍልስጤም መንግሥት ለመመሥረት ማለትም፥ የሁለት መንግሥታት መፍትሔን ከግብ ለማድረስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኮሪ የሚቻላቸዉን ሁሉ ጥረት እያደረጉ ነዉ።»

ድርድሩ እንደተናፈቀዉ ከቀጠለ፥ እንደተወራለት ፍልስጤሞችን ለመንግሥትነት ቢያበቃ እንኳን በሪያድ፥ አማን ነገስታት፥ በካይሮ ጄኔራሎች ድጋፍ ፍትሐዊ፥ ዴሞክራሲያዊ፥ ሕዝባዊ ሥርዓት ይመሠረታል ብሎ ማሰብ ከባድ ነዉ።ሳዳም ሁሴንን እና ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ከነ-ሥርዓቶታቸዉ ለማስገደል የሪያድ፥ የቀጠር፥ የአማን ነገሥታት ከዋሽግተን ብራስልሶች ጎን መቆሙ አልገደዳቸዉም።አንካራን ጨምረዉ የሶሪያን አማፂያንንም በገፍ እያስታጠቁ፥ አሰድ-እነ ሳዳምን እንዲያሰልሱ አበክረዉ እየጣሩ ነዉ።

Syrien Aleppo Zerstörung Luftangriffe 28.12.2013

ሶሪያየካይሮ ተቀናቃኞችን በመደገፍ ግን ይቃረናሉ።ሪያድ መፈንቅለ መንግሥት አድራጊ ጄኔራሎችን ትደግፋለች።ቀጠርና አንካራ በመፈንቀለ መንግሥት የተወገዱትን ፕሬዝዳት ወገኖች ይደግፋሉ። ይሕ ሁሉ ሆኖ ኢራቅ፥ ሶሪያ፥ ግብፅ፥ ሊቢያ፥ ቱኒዚያ ሠላም ለማዉረድ ወይም ለማደራደር ያንዳቸዉም ድምፅ አለመሰማቱ ነዉ-ትዝብቱ።የአሜሪካኖችም ጭምር።ለዝንተ-ዓለም ሠላም በያዉቀዉ ምድር፥ አንፃራዊ ሠላም የነበራቸዉ ሐገራት ሠላምን እያጠፉ ፍልስጤም እስራኤሎች ተነጥለዉ ሠላም ማዉረድ ከቻሉ በርግጥ ከተዓምር የሚቆጠር ነዉ። ለማየት ያብቃን።ሥለ ማሕደረ ዜና ያላችሁን አስተያየት በደብዳቤ፥ በኢሜይል፥ በስልክ፥ በኤስ ኤም ኤስ ላኩልን።የላካችሁልንን አመሰግናለሁ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic