የሞ ኢብራሂም ሽልማት ለዮአኪም ቺሳኖ | አፍሪቃ | DW | 23.10.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሞ ኢብራሂም ሽልማት ለዮአኪም ቺሳኖ

የቀድሞው የሞዛምቢክ ፕሬዚደንት ዮአኪም ቺሳኖ በሀገራቸው ሰላም እንዲወርድ ለተጫወቱት ሚናቸውና ለተከተሉት የመልካም አስተዳደር ዘይቤአቸው ብዙ የተነገረለትን የሞ ኢብራሂም ተቋም ሽልማት ተሰጣቸው።

ዮአኪም አልበርት ቺሳኖ

ዮአኪም አልበርት ቺሳኖ

ቺሳኖ ይህን ለመጀመሪያ ጊዜ ትናንት ለንደን የተሰጠውን አምስት ሚልዮን ዶላር የያዘውን ሽልማት ያገኙ የመጀመሪያው አፍሪቃዊ መሪ ናቸው። ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ የሆነውን ሽልማት ያዘጋጁት መንበሩን ብሪታንያ ያደረገው የግዙፉ የሞባይል ተቋም ባለቤት፡ ሱዳናዊው ሚልዮኔር ሞ ኢብራሂም ናቸው።
እአአ በ 1986 ዓም በአይሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን የገዢው የግራ መስመር ተከታዩ የፍሬሊሞ ፓርቲ መሪንና የሀገሪቱን ፕሬዚደንት ሳሞራ ማሼልን የተኩት ዮአኪም አልበርት ቺሳኖ በፍሬሊሞ እና በተቀናቃኙ የቀኙ መስመር ተከታይ ሬናሞ መካከል እአአ በ 1975 ዓም ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ የተላቀቀችው እስከ ዓም ድረስ በቀጠለው ውጊያ በተዳቀቀችው የደቡባዊቱ አፍሪቃ ሀገራቸው ውስጥ ብሄራዊ ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ፡ የዴሞክራሲያዊው ሂደት እንዲቀጥልና የኤኮኖሚው ልማት ወደፊት እንዲራመድ ላበረከቱት ድርሻቸው ለዚህ ታዋቂ ሽልማት መብቃታቸውን ተሸላሚውን አፍሪቃዊ መሪ የሚመርጠው ቡድን አባል የሆኑት የቀድሞው የተመድ ዋና ጸሀፊ ኮፊ አናን ትናንት በለንደን ማዘጋጃ ቤት ኮፊ አናን አመልክተዋል። ትናንት የስድሳ ስምንት ዓመት የሞላቸው ቺሳኖ እአአ 1992 ነበር ከሬናሞ ጋር ለአስራ ስድስት ዓመት የተካሄደውን የርስበርስ ጦርነት ያበቃውን የሰላም ውል ሮማ ኢጣልያ ውስጥ የተፈራረሙት። እአአ በ 1994 ና 1999 ዓም በሀገሪቱ በተካሄዱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች የተመረጡት ሞዛምቢክን አስራ ዘጠኝ ዓመት የመሩት፡ ፕሬዚደንት ቺሳኖ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው ካበቃ በኋላ ስልጣናቸውን የለቀቁበት ድርጊት የሞዛምቢክ የፖለቲካ ብስለትን ማጉላቱንና የሀገሪቱ ተቋማትና ዴሞክራሲያዊው ሂደትም ከግለሰብ ዝና የበለጠ ትርጓሜ እንዳያዙ ማሳየቱን አናን ሽልማቱ ይፋ በሆነበት ስነ ስርዓት ላይ አስታውቀዋል።
« ሽልማቱ ተሸላሚዎቹ ባላቸው ልምድና ችሎታ ተጠቅመው ለአፍሪቃ እና ለመላው ዓለም አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ያተጋቸዋል የሚል ተስፋ አለን። ሽልማቱ የአፍሪቃ መሪዎች ከቀጥታ የፖለቲካ ተሳትፎአቸው በጡረታ ሲገለሉ የገንዘብ ዋስትና የገንዘብ ዋስትና ስለሚሰጥ በስልጣን ዘመናቸው ከፍተኛ ደረጃ ያለው ምግባር እንዲያራምዱ ያበረታታል ብለንም ተስፋ እናደርጋለን። »
በዓለም ለአንድ ግለሰብ የሚሰጠውን ትልቁ ሽልማት ትናንት ያገኙት ቺሳኖ ለሌሎች አፍሪቃውያን መሪዎች አርአያ ሊሆኑ እንደሚችሉና በሽልማት ባገኙት ገንዘብም የሀገራቸውን ህዝብ መርዳት እንደሚችሉ ተስፋ ማድረጋቸውን ከዩጋንዳ መዲና ካምፓላ ገልጸዋል። ይሁንና፡ በተመሳሳይ ጊዚያት፡ በስልጣን በነበሩባቸው ዓመታት ጭምር፡ በርካታ ሽልማቶችን ማግኘታቸውን ያስታወቁት በወቅቱ በዩጋንዳ ተቀናቃኝ ወገኖችን እንዲሸመግሉ የተመድ ልዩ ልዑክ ሆነው የተሾሙት ቺሳኖ አሁን ለሞ ኢብራሂም ሽልማት መብቃታቸው እምብዛም እንዳላስገረማቸው አስታውቀዋል።
ስልጣናቸውን ከሶስት ዓመታት በፊት የለቀቁ የቀድሞ አፍሪቃውያን መሪዎች በሀገር አስተዳደሩ ረገድ ያከናወኑትን መልካም ተግባር የመረመረው ከኮፊ አናን ጎን የቀድሞ የአየርላንድ ፕሬዚደንት ወይዘሮ ሜሪ ሮብንሰን፡ የቀድሞው የፊንላንድ ፕሬዚደንት ማርቲ አህቲሳሪና የቀድሞው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ሳሊም አህመድ ሳሊም የሚጠቃለሉበት የሞ ኢብራሂም ሽልማት ዳኞች ቡድን የአስራ ሶስት የቀድሞ አፍሪቃውያን ርዕሳነ ብሄር ተግባርን ከተመለከተ በኋላ ነበር ሽልማቱን ለቺሳኖ ለመስጠት የወሰነው። ሽልማቱ አፍሪቃ አዎንታዊ ገጽታ እንዳላት የሚያረጋግጥ መሆኑንን ሳሊም አህመድ ሳሊም አመልክተዋል።
« ይህ ዓይነቱ ሽልማት በመጀመሪያ ደረጃ አፍሪቃ የችግሮችና የበሽታዎች ወይም የርስበርስ ጦርነቶች ብቻ አህጉር የሚካሄድባት አህጉር አለመሆንዋን ለዓለም ያሳያል። በአፍሪቃ የኤኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ መሻሻል አለ። ዴሞክራሲያዊው ሂደትም ተነቃቅቶዋል። »
ሽልማቱ ይፋ በሆነበት በትናንቱ ዕለት በለንደን መገኘት ያልቻሉት ቺሳኖ ሽልማቱን በቅርቡ በአሌግዛንድርያ ግብጽ በሚደረግ ልዩ ስነ ስርዓት እንደሚቀበሉ የሞ ኢብራሂም ሽልማት ድርጅት አስታውቋል።

ተዛማጅ ዘገባዎች