የሞያሌው የሰላማዊ ነዋሪዎች ጥቃት እያነጋገረ ነው | ኢትዮጵያ | DW | 12.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የሞያሌው የሰላማዊ ነዋሪዎች ጥቃት እያነጋገረ ነው

በኦሮምያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ባለፈው ቅዳሜ የመከላከያ ሠራዊት በነዋሪዎች ላይ የፈጸመው ጥቃት ሆን ተብሎ ታቅዶ እና ተቀነባብሮ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት ነው ሲሉ አንድ የክልሉ ኃላፊ አወገዙ። ኃላፊው ለዶይቼ ቨለ በሰጡት አስተያየት፤ በጥቃቱ ሰላማዊ ነዋሪዎች ተንበርከኩ እየተባሉ ጭምር በጭካኔ መገደላቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:52

የሞያሌው የሰላማዊ ነዋሪዎች ጥቃት እያነጋገረ ነው

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ሸዋ በር በተባለ የመኖሪያ መንደር መከላከያ ሠራዊት በፈጸመው ጥቃት 10 ሰዎች ሲሞቱ 12 ያህል የሚሆኑ ደግሞ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል። ከተጎጂዎቹ አምስቱ ወደ ሐዋሳ ለከፍተኛ ህክምና መላካቸውም ታውቋል። ከሟቾቹ መካከል ሕጻን ልጃቸውን እና ነፍሰጡር ባለቤታቸውን እቤት ትተው እንደወጡ የቀሩት የመዶ ሚጎ ትምሕርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ተማም ነጌሶ ይገኙበታል።

ግድያውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ሴክሬተርያት ተወካይ ሌተናል ጄኔራል ሀሰን ኢብራሂም በሰጡት መግለጫ ድርጊቱን « የተሳሳተ መረጃ በመያዝ የተፈጠረ ግጭት» ሲሉ ነበር የገለጹት። በድርጊቱ ተሳትፏል የተባለ የአንድ ሻለቃ ጦር ትጥቅ እንዲፈታ ተደርጎ አምስት አባላቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸውም ነው ብለዋል።

በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ፍትህ ቢሮ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ ታየ ደንደአ ይህን አባባል ህዝብን የመስደብ ያህል ነው ሲሉ ይተቻሉ። በመከላከያ ሰራዊት የተፈጸመውን ጥቃት አሳዛኝ ሲሉ የገለጹት አቶ ታየ ድርጊቱን ፈጻሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ትእዛዝ አስተላላፊዎቹ የኮማንድ ፖስቱ እና የመከላከያ ሠራዊት ኃላፊዎቹ ጭምር በሕግ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባልም ብለዋል።

ከጥቃቱ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ አካል ኮማንድ ፖስት፤ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የገቡ የኦነግ ታጣቂዎችን ለመቆጣጠር እና ለመደምሰስ በስፍራው ግዳጅ ላይ ተሰማርቶ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት የተሳሳተ መረጃ ይዞ ባደረገው እንቅስቃሴ በአካባቢው ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በስህተት ጉዳት አድርሷል ሲል በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጿል።

የሞያሌ ከተማ ከንቲባ አቶ አስቻለው ዮሐንስ ግን ህዝብ በብዛት በሚኖርበት የሞያሌ ከተማ የተከስተው ጥቃት ከኦነግ እንቅስቃሴ ጋር አንዳችም ግንኙነት እንደሌለው ነው የሚያስረዱት። በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለማረጋጋት ከሃገር ሽማግሌዎች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ከቄሮ አባላት ጋር ውይይት ተካሂዶ መግባባት ላይ መደረሱንም ከንቲባው ጨምረው ገልጸዋል።

በኦሮምያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ የመከላከያ ሠራዊት በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ ከፈጸመ በኋላ የደህንነት ስጋት ያደረባቸው በሺህዎች የሚገመቱ የጫሙቅ፣ ሸዋበር እና አርበሌ ቀበሌ ነዋሪዎች መኖሪያ ቀያቸውን ለቅቀው ወደ አጎራባች ኬንያ ድንበር ከተማ ወደምትገኘው ሴሺ ሞያሌ ከተማ መሰደዳቸዉ ተገልጿል።

እንዳልካቸው ፈቃደ  

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic