የሞዛምቢክ ጦርነት ፍፃሜ 20ኛ ዓመት | አፍሪቃ | DW | 03.10.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሞዛምቢክ ጦርነት ፍፃሜ 20ኛ ዓመት

ሞዛምቢክን 15 ዓመታት ሙሉ ያዳቀቀውን የርስበርስ ጦርነት ያበቃው የሰላም ውል ከተፈረመ ነገ እአአ ጥቅምት አራት ቀን 20 ዓመት ይሆነዋል። በምሕፃሩ ፍሬሊሞ በመባል በሚታወቀው ገዢው የሞዛምቢክ ነፃ አውጪ ግንባር እና በአንፃሩ በታገለው በምሕፃሩ ሬናሞ በተባለው ብሔራዊ የሞዛምቢክ ተቃዋሚ ቡድን መካከል የተካሄደው ውጊያ ካበቃ

ሁለት አሠርተ ዓመታት ቢሆነውም፡ የርስበርሱ ጦርነት በሀገሪቱ፡ በተለይም በዱር አራዊቱ ይዞታ ላይ ትቶት ያለፈው መዘዝ ዛሬም ጎልቶ የሚታይ ነው።
የሬናሞ ዓማፅያን በፍሬሊሞ አንፃር የብረቱን ትግል የጀመሩት እአአ በ 1977 ዓም ነበር። ቡድኑ በዚያን ጊዜ ሮዴዥያ ትባል በነበረችው በዛሬዋ ዚምባብዌ እና የዘር አድልዎ አመራር ይከተል በነበረው የደቡብ አፍሪቃ ነጮች መንግሥት ድጋፍ ላይ ጥገኛ ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪም በተለይ በብዛት ከደቡባዊ ሞዛምቢክ በተውጣጡ የፍሬሊሞ ካድሬዎች በተቋቋመው መንግሥት እንዳልተወከሉ ከተሰማቸው ብዙ የማዕከላይ ሞዛምቢክ ነዋሪዎችም ሰፊ ድጋፍ አግኝተው የነበረው ሬናሞ እአአ በ 1970 ዓም የመንግሥት ወታደሮች ይቆጣጠሩዋቸው ከነበሩት ትላልቅ ከተሞች ራቅ ብሎ በዚሁ አካባቢ በሚገኘው ታዋቂው የጎሮጎንዛ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ዋና ሰፈሩን ማቋቋሙ ይታወሳል።

ይሁንና፡ ባካባቢው እንቅስቃሴአቸውን ያጠናከሩት የሬናሞ ዓማፅያን በፓርኩ ባስፋፉት ሕገ ወጡ አደን ጥበቃ ይደረግላቸው የነበሩት ዝሆን፡ አንበሣ፡ አውራሪስ፡ ጎሽን የመሳሰሉት የዱር አራዊት ለጥፋት ተዳረጉ። ዓማፅያኑ ዝሆኖችን እየገደሉ ጥርሳቸውን ለጦር መሣሪያ እና ለምግብ መግዣ ማዋል ጀመሩ። ይሁን እንጂ፡ የሬናሞ ዓማፅያን ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥቱ ወታደሮችም በዚሁ ሕገ ወጥ አደን ተሳታፊዎች ነበሩ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በርስበርሱ ጦርነት ጊዜ በማዕከላይ ሞዛምቢክ በተከሰተው የረሀብ አደጋ ወቅት ያካባቢው ነዋሪዎች እና ዓማፅያኑ ጭምር በፓርኩ የቀሩትን የዱር አራዊት በብዛት መግደላቸው አይዘነጋም።

በዚህም የተነሳ፡ ከርስበርሱ ጦርነት በፊት እና በቅኝ አገዛዙ ዘመን የዱር አራዊት በብዛት ይገኙበት የነበረው ፓርኩ ከሞላ ጎደል ሕይወት አልባ የመሆን ዕጣ ገጥሞት፣ በውስጡ ከነበሩት የዱር አራዊት መካከል 90% የሚሆኑት የርስበርሱ ጦርነት ከተጀመረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ መጥፋታቸው ተመዝግቦዋል።እርግጥ፡ ቱሪስቶችን የሚያስጎበኘው ሙቲኖ እንደገለጸው፡ በሀገሪቱ ሰላም ከወረደ ዛሬ ከሀያ ዓመታት በኋላ በጎሮጎንዛ ፓርክ የዱር አራዊቱ ቁጥር በመጨመር ላይ ይገኛል። ያም ቢሆን ግን፡ ያለፈውን ዕጣ ያልረሱት አራዊቱ፡ በተለይ ዝሆኖች፡ አሁንም ፍርሀት እንዳላቸው ሙቲኖ አስረድቶዋል።
« ያካባቢው ዝሆኖች ባለፈው በገጠማቸው ችግር የተነሳ አሁንም ይፈራሉ። ዝሆኖቹ ሌሎች ዝሆኖች ሲገደሉ አይተዋል። እና ዛሬ የተሽከርካሪ ድምፅ ሲያዩ፡ አደጋ እንደመጣባቸው ስለሚያስቡ ይሸሻሉ። ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው ሁኔታውን ቀስ በቀስ እየተለማመዱ ያሉት። »
የዱር አራዊቱን ለመጠበቅ እና ቁጥራቸውም እንዳይመናመን የሞዛምቢክ መንግሥት በ 120 የፓርኩ ጠባቂዎች አማካኝነት አስፈላጊውን ጥበቃ የማድረግ ጥረቱን ቢያጠናክርም፡ ሕገ ወጡ አደን አሁንም ትልቅ ችግር እንደደቀነ ይገኛል። መንግሥት ያወጣቸው መዘርዝሮች እንደሚያሳዩት፡ በሀገሪቱ በያመቱ ወደ 6,000 የሚጠጉ የዱር አራዊት በሕገ ወጥ አዳኞች ይገደላሉ። ይህንኑ አሳሳቢ ችግር ለማስወገድ እና የጎሮጎንዛ ብሔራዊ ፓርክን ጥበቃ በተሻለ መንገድ ማረጋገጥ ይችል ዘንድ መንግሥት እአአ በ 2008 ዓም የካር ተቋም ከተባለ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ አሜሪካዊ ድርጅት ጋ ውል ተፈራርሞ በመስራት ላይ ይገኛል። የድርጅቱ መሥራች ግሬገሪ ካር እንደገለጹት፡ ድርጅታቸው እስካሁን ለፓርኩ ጥበቃ 40 ሚልየን ዶላር ያወጣ ሲሆን፡ ድርጅቱ በርስበርሱ ጦርነት ወቅት በፓርኩ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማብቃት እና ሕገ ወጦቹን አዳኞች ወደዚሁ ተግባር የገፋፋቸውን ባካባቢው የሚታየውን ድህነት ለማብቃት ጥረት ጀምሮዋል። በፓርኩ አቅራቢያ ትምህርት ቤቶችን እና የጤና ጥበቃ ማዕከላትን ከማቋቋሙ በላይ 350 የስራ ቦታዎችን ፈጥሮዋል።


« በፓርኩ ከሚሰሩት መካከል 98% የሞዛምቢክ ዜጎች ናቸው። ፓርኩ የራሳቸው ነው፡ ችሎታው አላቸው። ቡድናችን አንድ በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል። ጎሮጎንዛን በጣም ግሩም ፓርክ የማድረግ ዓላማችንን ከግብ እንደምናደርስ አምናለሁ። »
በፓርኩ ተቀጥረው የሚሰሩትን ቀድሞ ከፍሬሊሞ ወይም ከሬናሞ ጎን ተሰልፈው የተዋጉትን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸውም የዱር አራዊቱን ይዘት በመጠበቅ ብዙ ቱሪስቶች እንደገና ወደሀገራቸው እንዲመጡ የማድረጉ ዓላማቸው ነው።

ማርታ ባሮዞ /አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic