የሞዛምቢክ ድንጋይ ከሰል ሐብት | ሞዛምቢክ- የድንጋይ ከሰል ማዕድን | DW | 05.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሞዛምቢክ- የድንጋይ ከሰል ማዕድን

የሞዛምቢክ ድንጋይ ከሰል ሐብት

በሞዛምኒክ የቴህት ክፍለ ሀገር ያን ያህል ትኩረት የተሰጠው ቦታ አይደለም። በተለይ ማንም በሞቃታማ አየሩ በሚታወቀው ክፍለ ሀገር በፍቃደኝነት ለመኖር አይፈልግም። ዛሬ ግን ይህ አካባቢ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ስፍራ ሆኗል። ምክንያቱም ከጥቂት አመታት በፊት በዚህ ስፍራ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ተገኝቷል።

ጠበብት እንደሚሉት በአለም ማዕድን ካሉበት ትላልቆቹ ቦታዎች እንደ አንዱ ይቆጠራል።

እኢአ 2007 ዓም የተለያዩ የውጭ የማዕድን ድርጅቶች ወደዚህ አካባቢ ሲሄዱ ብዙዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመለወጥ አላማ ነበራቸው። ብዙውን ጊዜ በዚህ በተፈጥሮ ሀብት በታደለው አካባቢ የሚኖሩት ግን ዕድገትን በጥርጣሬ ይመለከቱታል። የ ዶይቸ ቬለዋ ማርታ ባሮሶ ወደ ቴህት ሄዳ በዚያ ከከሰል ማዕድን አትራፊ እና ክስረት ያጋጠማቸውን አነጋግራለች። ከሩቅ ሲመለከቱ ከሸለቆ በቀር ብዙም የሚታይ ነገር የለም። ዙሪያውን የከበቡት ተራሮችም ጭምር ጥቁር ናቸው። ቀረብ ብለው ሲመለከቱት ግን በሞዛምቢክ ክፍለ ሀገር ቴህት ግዙፍ የከሰል ተራራ ማዕድን መሆኑ ይለያል።

ማዕድኑን በባለቤትነት የያዘው ቫለ የሚባል የብራዚል ኩባንያ ነው። በዚሁ ስፍራ ከሰል የሚያወጡት ቀንና ሌሊት ይሰራሉ። እያንዳንዱ በዚህ ቦታ የሚንቀሳቀስ የጭነት ተሽከርካሪ 400 ቶን ከሰል ያመላልሳል። የቫል ኩባንያ በመጀመሪያው የማዕድን ማውጣት ስራው ብቻ ሁለት ቢሊዮን ዩ ኤስ ዶላር አፍሷል። ኩባንያው በሚቀጥሉት 35 አመታት ከ ሁለት ቢሊዮን ቶን በላይ ከሰል ከመሬት ውስጥ ለማውጣት፣ ከዚህም ጎን ለጎን የአካባቢውን ህዝብ ኑሮ ለማሻሻል እንደሚፈልግ ፓውል ሆርታ የቫለ ሞዛምቢክ ስራ አስኪያጅ ገልፀዋል።

« እንደማምነው የቴህት እና ሞዓቲዜ ከተማዎች በቫለ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ተቋማት አማካኝነትም ጭምር በጣም አትራፊ የሆኑ ይመስላል። እስካሁን በእኛ ማዕድኖች ውስጥ መስራት እንዲችሉ 600 የሚጠጉ የአካባቢው ወጣቶችን አሰልጥነናል። እነዚህ ሰዎች ምግብ እና መጠለያ ያስፈልጋቸዋል። ይህ አንድ ኢኮኖሚያዊ ኃይል እንዲፈጥር ያደርጋል። ይህም በቴህት እና በሞዓቲዜ ማህበረሰብ ላይ ተዕፅኖ አለው።»

በርግጥ በክፍለ ሀገሩ ዋና ከተማ ቴህት ለውጥ ይታያል። በፊት ባዶ ሰፊ መሬት በነበረበት ቦታ አዳዲስ ህንፃዎች ተገንብተዋል። በሁሉም ሆቴሎች ማለት ይቻላል ማደሪያ ቦታ አይገኝም። አዳዲስ ምግብ ቤቶች እና ቡና ቤቶች ተከፍተዋል። በየቦታው አልባሳት እና ምግብ ይሸጣል። ብዙ ባንኮች ተከፍተዋል። በከተማይቱ ከጥቂት አመታት በፊት አራት ባንኮች ብቻ ነበሩ። ዛሬ 15 ደርሰዋል። እንዲያውም በቴህት ከዳቦቤት፣ ከመዳህኒት ቤቶች እና ከአታክልት መደብሮች የበለጡ ባንኮች እንዳሉ ነው የከተማይቱ ነዋሪዎች የሚናገሩት። ይህ ምንም እንኳን የተጋነነ አገላለፅ ቢሆንም በቴህት ለውጥ እየታየ ነው። ማኑኤል ካቴኩታ ይህንኑ ለውጥ እየታዘቡ ይገኛሉ። መንግስታዊ ላልሆነው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት «ሊጋ » ይሰራሉ። እኢአ በ 2001 ቴህት መኖር ሲጀምሩ ከተማይቱ ወደ ጎረቤት ሀገር ማላዊ እቃ ለሚያመላልሱ የጭነት ተሽከርካሪዎች መተላለፊያ ብቻ ነበረች። ካቴኩታ ዛሬ በየመንገዱ ዳር የተሰሩ ቤቶችን ሲመለከቱ እጅጉን ይገረማሉ።

« ይህ ህንፃ አንድ አመት እንኳን አልሆነውም። ቀደም ሲል ይህ የከተማይቱ ቁሻሻ ማስወገጃ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በርካታ ቁሻሻ ማስወገጃዎች አዲስ ቤት ተሰርቶባቸዋል። እዛ ጋ አንድ አዲስ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች መደብር አለ። ከተገነባ ከአንድ አመት በላይ አልሆነውም። » ቴህት ውስጥ የቤት ንግድ ተጧጡፏል። መሬት እና አፓርትማዎች ፣ቢሮ ወይንም መደብሮች ለመግዛት የገንዘብ አቅም ያለው ካለሀሳብ ሊኖር ይችላል ይላሉ ካቴኩታ። ወደ ከተማይቱ ሲመጡ የአንድ ጥሩ ቤት የወር ኪራይ 200 € ነበር ። ዛሬ 4000€ደርሷል። በዋጋ ግሽበት የተነሳ ገንዘብ ለመቆጠብ ሲሉ ካቴኩታ በየቀኑ ለምሳ ሰዓት ወደቤታቸው ይሄዳሉ።

« ሁሉም አንፃራዊ ነው። ከዚህ ቀደም ምንም ስራ ያልነበራቸውና አሁን ስራ ያገኙ ደስተኞች ናቸው። ቀድሞ ስራ የነበራቸው አመለካከት ለየት ያለ ነው። ቀደም ሲል ያኔ በሚያገኙት ደሞዝ ለህይወት አስፈላጊ ነገሮችን ማሟላት ይችሉ ነበር። አሁን ግን ይህን ማድረግ አይችሉም።» ዛሬ ይላሉ የመብት ተሟጋቹ እያንዳንዱ የባለ ተንቀሳቃሽ ስልክ ባለቤት ነው። የሌለው እንዲኖረው ይመኛል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዚህ ክፍለ ሀገር ስልክ አግኝቶ መግዛት ከባድ ነበር። ምናልባት አንድ የጭነት ተሽከርካሪ ሾፌር ከሌላ ቦታ ካላመጣ በስተቀር። ዛሬ ግን በአካባቢው ገበያዎች የተለያዩ የሀገር ብሎም የውጭ ሀገር ምርቶችን መግዛት ይቻላል። የ 29 ዓመቷ ኦሊቪያ እና ፌዝ በትልቁ የገበያ አዳራሽ ውስጥ በጥፍር እና በፀጉር ሰሪነት ሙያ ተሰማርተዋል። እኢአ 2008 ነው ከጎረቤት ሀገር ዚምባብዌ ወደ ሞዛምቢክ የሄዱት። በሀገራቸው የዋጋ ግሽበት ያስመረራቸው ሁለቱ ወጣቶች በቴህት ብዙ ገንዘብ እንደሚገኝ ሰምተው ነበር የሄዱት።

« ቴህት እየበለፀገች ነው። ብዙዎቹ ተቋማት በደቡብ አፍሪቃ እና አሜሪካ እጆች ናቸው። እኔ ወደዚህ ስመጣ መኪናዎች አይታዩም ነበር። አሁን ጥሩ ነው። የውጭ ተቋማት ወደዚህ መምጣት የቴህትን ነዋሪዎች ይጠቅማል። ስራ ያገኛሉ ። ሁሉም ነገር ዕድገት ይኖራል። ኦሊቪያ በቀን ከ 500-1000 ሜቲካስ ማለትም ከ 15-25 ዮሮ ግድም ገቢ ታገኛለች። ገንዘቡም ለመኖር በደንብ ይበቃኛል ትላለች። ከኦሊቪያ እና ፌዝ ሱቅ ጎን መደብር ያላቸው ሌናርድ እና ሮላንድም ከዚምባብዌ ነው ለንግድ ወደ ቴህት የሄዱት። ይሁንና ገንዘቡ ለኑሮ በቂ ነው የሚለውን የኦሊቪያን አመለካከት አይጋሩም። « የወደፊቱን እኮ አይመለከቱም» « መብላት እና መልበስ መቻል ብቻ አይደለም ኑሮ ማለት። ስለ ብልፅግና መናገር የምንችለው ልጆች ት/ቤት መሄድ ሲችሉ እና ጥሩ ትምህርት ሲያገኙ ነው፤ ወደፊት ጥሩ ስራ እና ደሞዝ እንዲያገኙ። ያ ነው ብልፅግና ማለት። እዚህ ግን ብዙ ነገሮች ይጎድላሉ።»

« ቴህት ውስጥ ጥሩ ክፍያ ስራ ያላቸው ብዙዎቹ ከሩቅ ሀገር የሄዱት ናቸው። ተቋማቱ ለሰራተኞቻቸው ምግብ የሚያስመጡት ከጎረቤት ሀገር ደቡብ አፍሪቃ ነው ። ከማዕድን ተቋማቱ ጋ ጥሩ ውሎች የሚፈራረሙት መካከለኞቹ እና ትላልቆቹ ኩባንያዎች ናቸው። አነስተኞቹ ነጋዴዎች ያን ያህል ተጠቃሚዎች አልሆኑም።»

የዘንድሮው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ዕድገት ሠንጠረዥ ላይ ሞዛምቢክ ከመጨረሻው ሀገራት መደዳ በ184ኛው ቦታ ላይ ትገኛለች። ከሞዛምቢክ ያነሰ ዕድገት የሚታይባቸው ብሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ እና ኒጀር ብቻ ናቸው። የሞዛምቢክ የኢኮኖሚ እድገት በእያመቱ 7 ከመቶ መሆኑ ቢነገርም በሀገሪቱ ያለው የድሆቹ ቁጥር አሁንም አልቀነሰም። ልክ በቴህት ክፍለ ሀገር እንደሚታየው የውጭ ሀገር መዋለ ንዋይ በጠቅላላ የሚፈሰው በጥሬ የተፈጥሮ ሀብቱ ዘርፍ ላይ ብቻ ነው ለማለት ይቻላል። የሞአትሴ የድንጋይ ከሰል ማውጫ ማዕድንን የመሣሰሉት ፕሮጀክቶች ግዙፍ የቀረጥ ቅናሽ ያገኛሉ።

እስከ ጥቅምት 2012 ድረስ የክፍለ ሀገሯ አስተዳዳሪ የነበሩት እና ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ የያዙት አልቤርቶ ቫኩኢና ከተፈጥሮ ሀብቱ የሚገኘውን ገቢ በፍትሓዊ መንገድ ያከፋፍል መባሉን በፍፁም አይረዱትም። እያንዳንዱ ዜጋ አትራፊ መሆን የሚችልበትን ዘዴ ራሱ ማመቻቸት መመልከት አለበት ባይ ናቸው። « አንዳንዴ ከሁኔታዎች ጋ ራስን ማስተካከል ያስፈልጋል። ሁሉም ለራሱ መታገል አለበት።

ያ ማለት በአንድ ተቋም ላይ ጥገኛ በመሆን ፋንታ በእውቀቴ እና በችሎታዬ በመጠቀም ክብሬን አስጠብቄ የምኖርበትን መንገድ ማግኘት የኔ ፋንታ መሆን አለበት። » ይህ አነጋገር የድንጋይ ከሰል ማዕድኑ በተገኘበት አካባቢ ይኖሩ ለነበሩት ዜጎች ትርጉም አልባ ነው። እኢአ በ2009 መጨረሻ እና 2010 መጀመሪያ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ በዚሁ ሰበብ በግዳጅ በሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል። የቫለ ኩባንያ በዚሁ ጊዜ ለቴህት ሰዎች አዳዲስ ቤቶች እንደሚሰሩ፣ አዲስ የስራ መስክ እንደሚከፈት፣ ትምህርት ቤቶች እና ሀኪም ቤቶች እንደሚሰሩ ነበር ቃል የገባው። አንዱንም ቃሉን አላከበረም ይላሉ ከሚኖሩበት ከሞቲዜ ከተማ ካተሜ በተባለና 40 ኪሜ ርቆ በሚገኝ ከተማ በግዳጅ የሰፈሩት ነዋሪዎች። « ቫለ በአንድ የግንባታ ተቋም ውስጥ ለብዙ አመታት መስራት እንደምንችል ቃል ገብቶልን ነበር። ይህ ገሀድ አልሆነም። ሁለት ሄክታር መሬትም ይሰጣችኋል ተብለን ነበር። የተሰጠን ግን አንድ ብቻ ነው። ወደ ዋናው ጓዳና የሚያመራው መንገድ ይጠረጋል ተብለን ነበር። ይህም አልተሰራም። ቃል እንደተገባውም እያንዳንዱ ኮሬንቲ አላገኘም። ለ 5 አመታት ይሰጣችኋል ከተባልነው ምግብ ያገኘነውም የአንዱን አመት ብቻ ነው። ከዛ በኋላ ምንም አላገኘንም።»

በካታሜ አዲስ ተሰሩ የተባሉት ቤቶች በጥሩ ሁኔታ ላይ አይገኙም። ግድግዳዎች ተሰነጣጥቀዋል። ዝናብ ይገባባቸዋል። የመብት ተሟጋቹ ዮሊዎ ካሌንጎ ከካቴሜ የተፈናቀሉትን ሰዎች ሁኔታ ይከታተላሉ። እሳቸውም እንደ ማኑኤል ካቴኩታ መንግስታዊ ላልሆነው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት «ሊጋ » ይሰራሉ።

በአመቱ መጀመሪያ በተደረገ አንድ የተቃውሞ ሰልፍ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች በፖሊስ ተይዘው ተደብድበዋል። ከነዚህ ጎሜዝ አንዱ ነው። ካሌንጎ ጎሜዝን አሁን ተሽሎት እንደው ይጠይቁታል። ጎሜዝ ቁስሉ እያሳከከው እንደሆነ ይነግራቸዋል። የደበደበውንም ፖሊስ ማን እንደሆነ ለይቶ ያውቃል። ጥር 10 2012 በመቶዎች የሚቆጠሩ ችግር የበዘባቸው የካቴሜ ነዋሪዎች ማዕድኑ የድንጋይ ከሰል ከሞዓቲዜ ከተማ እስከ ባይራ ወደብ የሚያመላለስበትን የባቡር ሀዲድ በመክበብ ተቃውሞ አሰምተዋል። መብታቸው ለምን እንደማይከበርላቸው እና ለምንስ የቫለ ኩባንያ ቃሉን እንደማይጠብቅ ጠይቀዋል። እስካሁን ግን ምንም መልስ አላገኙም። የቫለ ኩባንያ እንዳስታወቀው እኢአ ከ 2007 ዓም ጀምሮ አገር ውስጥ ከሚገኙ ድርጅቶች ብቻ አንድ ቢሊዮን ዮሮ ገቢ አግኝቷል። እኢአ 2012 ዓም ለአካባቢ ጥበቃ የሚቆረቆረው ድርጅት «ግሪንፒስ» ቫለን በሚመለከት በኢንተርኔት አስተያየት ከሰበሰበ በኋላ የቫለን ኩባንያ የአመቱ መጥፎ ተቋም ሲል ሰይሞታል። ።ምናልባትም የካታሜ ነዋሪዎች የኢንተርኔት አገልግሎት ቢኖራቸው ኖሮ በቫለ አንፃር የበለጠ የወቀሳ ድምፅ ይሰማ ነበር።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

DW.COM

Audios and videos on the topic