የሞዛምቢክ ዕጣ ከምርጫ በኋላ | አፍሪቃ | DW | 16.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሞዛምቢክ ዕጣ ከምርጫ በኋላ

በሞዛምቢክ ባለፈው ረቡዕ የተካሄደው ፕሬዚደንታዊ እና ምክር ቤታዊ ምርጫ አልፎ አልፎ ከታዩ አንዳንድ ያልተስተካከሉ አሰራር በስተቀር ከሞላ ጎደል በሰላማዊ ሁኔታ ተከናውኗል።

እንደሚታወሰው፣ በገዢው እና የቀድሞው የነፃነት ታጋይ የፍሬሊሞ ፓርቲ እና በተቀናቃኙ ትልቁ የተቃውሞ ፓርቲ ሬናሞ መካከል ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየው የፖለቲካ ውጥረት ሀገሪቱን እንደገና ወደርስ በርሱ ጦርነት እንዳያስገባ አስግቶ ነበር። ፍሬሊሞ የተቃዋሚውን ወገን አግልሎዋል በሚል በ2012 ዓም ጀምሮት የነበረው የሽምቅ ውጊያ ያበቃው እና በሀገሪቱም አጠቃላይ ምርጫ ሊካሄድ የቻለው እአአ ባለፈው ነሀሴ ስምምነት ከደረሱ በኋላ ነው። ይሁንና፣ ሁለቱ ትልቆቹ ፓርቲዎች ለደቡብ ምሥራቃዊቷ አፍሪቃዊት ሀገር ሥልጣን የሚደረገውን ምርጫ እንዳለፉት ጊዚያት ብቻቸውን ሊወስኑ እንደማይችሉ የቅርብ ጊዜው ሁኔታ አሳይቶዋል። አዳዲስ ፓርቲዎችም፣ በተለይ የሞዛምቢክ ዴሞክራቲክ ንቅናቄ ፣ በምሕፃሩ « ኤም ዲ ኤም» በሀገራቸው ፖለቲካ ላይ ሰፊ ተሳትፎ ለማግኘት ጠንክሮ ተንቀሳቅሶዋል።

ለአጠቃላዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ድምጽ የመስጠት መብት ካለው ወደ 11 ሚልዮን ሕዝብ መካከል ብዙው ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ወጥቶዋል። ለሀገሪቱ እና ላካባቢ ምክር ቤታዊ መንበሮች ከገዢው የፍሬሊሞ ፓርቲ እና ከትልቆቹ የተቃውሞ ፓርቲዎች ፣ ሬናሞ እና «ኤም ዲ ኤም» ጎን ወደ 30 የሚጠጉ ፓርቲዎች ተወዳድረዋል።

በሞዛምቢክ ሕገ መንግሥት መሠረት፣ ለሶስተኛ ጊዜ መወዳደር የማይችሉትን እና ሁለት የሥልጣን ዘመናቸውን በማጠናቀቅ በሀገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ እንዲካሄድ ያመቻቹትን ተሰናባቹን ፕሬዚደንት አርማንዶ ገቡዛን ለመተካት ሶስት ዕጩዎች ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ በተወዳዳሪነት ቀርበዋል፤ እነርሱም፣ ለፍሬሊሞ የፕሬዚደንት ገቡዛ ታማኝ እና የቀድሞው የመከላከያ ሚንስትር ፊሊፔ ኻሲቶ ንዩዚ፣

Wahlen Mosambik 15.10.2014 Filipe Nyusi

ፊሊፔ ኻሲቶ ንዩዚ

ከሬናሞ ደግሞ አፎንሶ ድላካማ፣ እንዲሁም፣ በ2009 ዓም እአአ ከሬናሞ ተገንጥሎ የተቋቋመው የሞዛምቢክ ዴሞክራቲክ ንቅናቄ ዕጩ ዳቪስ ሲማንጎ ናቸው። በአጠቃላዩ ምርጫው ሀገሪቱን ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ ከተላቀቀች እአአ ከ1975 ዓም ወዲህ በመምራት ላይ የሚገኝው ፍሬሊሞ እንደሚቀናው ታዛቢዎች እስካሁን የወጡ ውጤቶችን በመጥቀስ ገልጸዋል። ገዢው የፍሬሊሞ ፓርቲ ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ንዩዚም ፓርቲው የሀገሪቱን ልማት ለማራመድ እና አሁንም በከፋው ድህነት ላይ የሚገኘውን ሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ያከናወነው ተግባር ለድል እንደሚያበቃቸው በምርጫ ዘመቻ ወቅት ለተሰበሰበው ሕዝብ ሲናገሩ ተሰምተዋል። ከሁለት ዓመታት በፊት በባህር ጠረፏ ግዙፍ የጋዝ እና የነዳጅ ዘይት ንጣፍ ያገኘችው ሞዛምቢክ፣ በዓመት ሰባት ከመቶ ዕድገት በማስመዝገብ በአፍሪቃ ፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት ካስገኙት ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ለመሆን መብቃቷን ነው ንዩዚ ያጎሉት።

« አንድ ሰው ድል እቀዳጅ እንደሆን ጠይቆኝ ነበር። እኔም ምንም ጥርጥር እንደሌለኝ ነበር የገለጽኩለት። መንግሥታችን ባለፉት ዓመታት በጋራ ጥረት ያከናወነውን መልካም ስራ ተከታትላችሁት ይሆናል። ይኸው ገዢው ፓርቲ ያስገኘው ውጤትም የፓርቲውን ዕጩ፣ ማለትም እኔን ለድል ያበቃኛል። ይህን ነው አሁን ለናንተ እና ለጠቅላላ የሞዛምቢክ ሕዝብ የማስተላልፈው መልዕክት። »

Wahlen Mosambik 15.10.2014 Armando Guebuza

አፎንሶ ድላካማ

ይሁንና፣ ገዢው ፓርቲ በሙስና ሰበብ ብዙ የመራጭ ድምጽ ሊያጣ እንደሚችል ታዛቢዎቹ ሳይጠቁሙ አላለፉም። ሲብል ማህበረሰብ ቡድኖች እስካሁን ያወጡዋቸው የመጀመሪያዎቹ የአጠቃላዩ ምርጫ ውጤቶች እንዳሳዩት፣ ፍሬሊሞ እና ፕሬዚደንታዊው ዕጩ ንዩዚ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ የብዙኃኑን ድምጽ አግንተዋል።

ካሁን ቀደም በሀገሪቱ የተደረጉት ምርጫዎች በጠቅላላ የተጭበረበሩ ነበር በሚል ወቀሳ ያሰሙት የሬናሞ መሪ አፎንሶ ድላካማ ለፕሬዝደንትነቱ ሥልጣን በዕጩነት ሲቀርቡ ያሁኑ አምስተኛ ጊዜ ሲሆን፣ ያሁኑ ምርጫ ነፃና ትክክለኛ እንደሚሆን ተስፋቸውን እንዲህ ነበር የገለጹት።

« እንደምታውቁት፣ አፍሪቃ ውስጥ የምርጫ ውጤቶች ነፃ አይደሉም። ሆኖም፣ ያሁኑ ምርጫ ውጤት ሞዛምቢክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀባይነት የሚያገኝ ትክክለኛ እና ተዓማኒ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ይህ ገሀድ እንደሚሆንም እምነቴ ነው። »

ከነፃነት በኋላ ከፍሬሊሞ ጋ ለ16 ዓመታት ውጊያ ያካሄደው ተቀናቃኙ ሬናሞ በዚህ ምርጫ ትልቅ ሽንፈት ከደረሰበት እንደገና ወደ ሽምቅ ውጊያ እንዳይገባ አንዳንዶች ሰግተዋል። በ2013 ዓም በሞዛምቢክ በተካሄደው ያካባቢ ምርጫ ጥሩ ውጤት ያስመዘገበውጡ የሞዛምቢክ ዴሞክራቲክ ንቅናቄ ፣ «ኤም ዲ ኤም» በተለይ የወጣት መራጮች ድጋፍ ቢኖረውም፣ በምርጫው አሁን እንደታየው፣ ከሬናሞ ቀጥሎ የሶስተኛነቱን ቦታ ብቻ ነው የያዘው። ፓርቲው ከአንድ ዓመት በፊት ከሀገሪቱ ትላልቅ ከተሞች መካከል በአራቱ ድል መቀዳጀቱ የሚታወስ ሲሆን፣ የፓርቲው ማዕከላይ ኮሚቴ አባል ዶሚንጎስ ማኑዌል «ኤም ዲ ኤም » ሀገር ለመምራት ዝግጁ መሆኑን ነበር ያስታወቁት።

Wahlen Mosambik 15.10.2014 Afonso Dhlakama

ዳቪስ ሲማንጎ

« የ«ኤም ዲ ኤም» መሪ ዳቪስ ሲማንጎ ይህችን ሀገር መምራ የሚችሉ ትክክለኛው ግለሰብ ናቸው። ፓርቲያችን ሀገር የማስተዳደሩን ችሎታ ባካባቢ ደረጃ አስመስክሮዋል። መራጩ ሕዝብ ከዚሁ ተሞክሮ በመነሳት ትክክለኛውን ውሳኔ እንደሚወስድ ተስፋ እናደርጋለን። ገዢው ፓርቲ ላለፉት 40 ዓመታት የሀገሪቱን ኤኮኖሚ ያዳቀቀበት የተዛባ አሰራር መቆም አለበት። ሕዝቡ መንግሥት እየተከተለው ባለው ግልጽነት የጎደለው አሰራር ተሰላችቶዋል። »

ይሁን እንጂ፣ ሲማንጎ እና «ኤም ዲ ኤም» ባለፈው ዓመት ውጤታማ ቢሆኑም፣ የ61 ዓመቱ ድላካማ የሚመሩትን ሬናሞ እንደ ሁለተኛ ትልቅ የተቃውሞ ፓርቲ መተካቱ አሁንም አልተሳካለትም። በለንደን የሚገኘው «ቻተም ሀውስ» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ አሌክስ ቫይንስ እንዳሉት ፣ባለፈው ረቡዕ የተደረገው አጠቃላይ ምርጫ ባለፉት 20 ዓመታት የሞዛምቢክ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ትርጓሜ የተሰጠው ነው፣ ምክንያቱም፣ ካለፉት 39 ዓመታት ወዲህ ሥልጣኑን የያዘው ፍሬሊሞ ፣ ባለፉት ምርጫዎች አንፃር፣ ከተቀናቃኙ ሬናሞ እና የሀገሪቱን የፖለቲካ መድረክ ከጥቂት ጊዜ በፊት ከተቀላቀለው « ኤም ዲ ኤም» ለመጀመሪያ ጊዜ ጠንካራ ፉክክር ገጥሞት ነበር። እርግጥ፣ ምርጫው የሥልጣን ለውጥ እንደማያስገኝ ከበፊቱም ግልጽ እንደነበር ያመለከቱት ቫይንስ ፣የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምክር ቤት የሚይዙት መንበር ብዛት ፣ወደፊት በሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ አያያዝ ሊፈጥር እንደሚችል ገምተዋል። ጥያቄው ግን፣ ፓርቲዎቹ የምርጫውን ውጤት ያከብራሉ ወይስ ወደቀድሞ የፖለቲካ ውዝግብ ይመለሳሉ አይመለሱም የሚለው በመሆኑ ፣ ሂደቶችን ጠብቆ ማየት ግድ ይላል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic