የሞተር ባይስክሎች እገዳ፤ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 21.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የሞተር ባይስክሎች እገዳ፤

ሞተር ባይስክሎች ከሰኔ 30 ቀን 2011ዓ,ም ጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ የከተማዋ አስተዳደር ይፋ ያደረገው ውሳኔ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:47

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የከተማው አስተዳደር የኗሪዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በጥናት ላይ የተመረኮዘ ያለውን ውሳኔውን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኦማ ይፋ ካደረጉ በኋላ ብዙዎች ውሳኔውን በመደገፍ እና በመቃወም አስተያየት ሲለዋወጡ ታይተዋል። በአስተዳደሩ ይፋ የተደረገው ውሳኔ እውንነትም ያጠራጠራቸው አልጠፉም፤

«ቆይ ግን ፡ የምር ሞተርሳይክሎች ተከለከሉ?» ብላ ትጠይቃለች ሙኒት መስፍን አበበ፤ ያዳን ካኑማ ፣ «ከሰኔ 30 በኋላ ይከለከላሉ፤ አሁን ግን እየተለማመዱት ነው ወይ እያሟሟቁ።» የሚል ምላሽ ሲሰጥ፣ ዳዊት ፍቃዱ ደግሞ፤ «እንኳን ሞተር ቦይንግ አውሮፕላንም ተከልክሏል።» ብሏል።

የሞተር  ብስክሌቶችን የመታገድ ዜና የሰሙ ለተቃውሞ አደባባይ ለመውጣት ሲሞክሩ በፖሊስ መከልከላቸውን ከሰሙት መካከል ደግሞ ፤ ሳሚ ብሩ፣«ተገቢ ነው፤ ሥርዓተ አልበኝነቱ በበዛ ግዜ አይቃወሙም ነበር? ፖሊስ መልካም አደረገ።» ሲሉ አስናቀ ሸዋአሳየ ደግሞ፣ «አረ ሞተር ባይክ አያስፈልግም፤ ግሩም ሥራ ነው።» አሉ፤ ሚኪራ ሞርካታም፤ «ሕይወትም ማትረፍ ነው፤ በየቀኑ እየሞቱ አይደም እንዴ ሞተረኞቹ?» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አሌክስ አማረ፣ «ትክክለኛ ውሳኔ ነው እንደውም ዘግይቷል።» ነው ያሉት።

ዘካሪያስ ኪሩብ ደግሞ እንዲህ አሉ፤ «ምንም ነገር ስንወስን ጥቅም እና ጉዳት አለው፤ ዋናው ግን የቱ ነው አመዛኙ ሚለው ነው። እውነት ነው በአግባቡ ሚሠሩ አሉ ግን ለጥቂቶች ተብሎ 100ሚሊየን ህዝብ በሞተር መሰቃየቱ ነው ሚሻለው? ሞተር ካለው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ በዝቶዋል በተለይም  አደጋው ወጣት እየጨረሰ ነው ስለዚህም ውሳኔው ትክክል ነው።»

የሞተር ባይስክል ከመጪው ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ በአዲስ አበባ ላይ መታገድን በአዎንታዊነት የደገፉት እንዳሉ ሁሉ የተቃወሙም አልጠፉም። ረዲ ማን፤ «በጣም ጥቂት በሆኑ ጽንፈኛ በሆኑ ኃይሎች ምክንያት  የብዙ ሰዎችን ጉሮሮ መዝጋት ተገቢ አይደለም፤ አዲስ አበባ ውስጥ ሞተር መከልከሉን እቃወማለሁ» የሚል መልእክታቸውን ሌሎቹም እዲያጋሩላቸው ጠይቀዋል። ሞገስ ተፈሪም ፤ «እኔ እላለሁ፤ ፖሊስ ዜጎችን መጠበቅ አልቻለም? ይህ አንሶ የመገኘት ምልክት ነው። ውስን ወንጀለኛን መቆጣጠር ባለመቻል ብዙሃን ለፍቶ አዳሪን ማሸማቀቅ ተገቢ አይመስለኝም። በሉ እንግዲህ በሕዝብ ገንዘብ ሁሉንም ሞተር ግዙና አቃጥሉት። መቼም ለቅርስ አያስቀምጡት።» በማለት በትምህርተ ስላቅ አስተያየታቸውን በፌስቡክ አጋርተዋል።

ማሙሽ አከለው በበኩላቸው እንዲህ ብለዋል፤ «ይሄ ነገር በጣም አደጋ አለው። በትንሹ ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሞተር ሳይክሎች፤ ይሄንን ሥራዬ ብሎ የዕለት ጉርሱን የሚያገኝ እና ልጆቹንም የሚያስተምር አለ። ሌላው ነገር ከቀበሌ ተበርዶ የገዛ አለ፤ ሴቶች እህቶቻችን አረብ ሀገር ሠርተው የገዙ አሉ። የተገዙበትም ገንዘብ ቀላል አይደለም። የአንዱ ዋጋ እስከ 100 ሺህ ይደርሳል። ወንጀለኞችን በሌላ አማራጭ መከላከል ቢቻል እላለሁ።» ቁድወቲ ሙሀመድ በበኩላቸው፤ «የማይመስል ወሬ፤ ሌብነትን ለማጥፋት ሳይሆን ሌብነትን ማደራጀት መሆኑ መታወቅ አለበት። 1,500 ብር የቀን ገቢ አለኝ፤ ይህ ገቢ ሲቀርብኝ ገብቼ የምተኛ ይመስልሀል? ይብላኝ ለሚያወሩት፤ እነ ታከለ ብቻ ተውት ውስጡ ሌላ ዕቅድ አለ፤ ጠርጥር፤ ጠርጥር ጠርጥር አሁንም ጠርጥር።» ብለዋል።

ቅዱስ ዳዊት ደግሞ እንዲህ አሉ፤ «በሞተር የሚዘርፉ እንዳሉ ሁሉ ፣ ቤት ተከራይተዉ ትዳር መስርተዉ ልጆች ወልደዉ በመልካም ስብህና  ሥራቸዉን የሚሰሩ የዳቦ መግዣ የሚፈልጉ አሉ ታዲያ አብሮ ማገድ አግባብ አልነበረም ወንጀል ፈጻሚን መለየት ፣ መያዝ ፖሊስ ከኅብረተሰቡ ጋር መሥራት ነበረበት የበለጠ ሥራ ሲፈቱም እኮ ሌላ ወንጀል እንዲያስቡ ማድረግ ነዉ ለምጣዱ ሲባል አይጡን አለመንካት ነዉ ፦ባይሰበር መልካም ነዉ አይጡን ግን ከምጣዱ ላይ በዱላ ሳይሆን በጥንቃቄ ለመያዝ ሌላ መፍትሄ ማፈላለጉ ሳይሻል አይቀርም ባይ ነኝ እኔ !» መቅደስ ታደሰ በበኩላቸው፤ «በአግባቡ  የሚተዳደሩበት  ሞልተዋል  ግን  በምን  ይለዩ  ወዳጄ  የሕጋዊዎቹንም  ሞተር  ተከራይተው እኮ  ነው  መውጫ  መግቢያ  የሚያሳጡን።  ልሰርቅበት ነው ብለው  አይከራዩዋቸው ።»

በትዊተር አስተያየታቸውን ካስነበቡት መካከል ደግሞ፤ አጥናፍ ብርሃኔ ደግሞ፤ «በሞተረኛ ላክልኝ፤ ሕይወት ያቀል ነበር።» ሲል በፍቃዱ ዘሃይሉ ደግሞ፤ «የአዲስ አበባ አስተዳደር ቀውሱን ከመጥፎ ወደ ክፉ እየለወጠው ይሆን? ሞተር ባይስልክን ማገዱ በርካታ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩት ሰዎችን ሥራአጥ ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ምናልባት ለወንጀል እና ለተቃውሞዎች አስተዋፅኦ ሊኖረው ይችላል።» ከዚህም አክሎ በፍቃዱ ምን መደረግ አለበት ታዲያ በሚል ለቀረበት ጥያቄ  በመፍትሄነትም የፀጥታ ኃይሉን አቅም እና ወንጀልን የመከላከል ብቃት ማጠናከር እንደሚበጅ አሳስቧል።  ቢኒያም በበኩሉ፤ «ሥርዓት ማስያዝ እንጂ ክልከላ መፍትሄ አይሆንም። ካምፓላ ዩጋንዳ ውስጥ 500 ሺህ ቦዳ ቦዳ የሚሏቸው የሞተር ሳይክሎች ትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣሉ። ሥራአጥ ለሚበዛባት አፍሪቃ የሥራ ዕድል ሆኖ ሳለ ክልከላው የአስተዳደሩ ደካማነት ነው።» የውጭ ዜጋ መሆናቸውን ፎቷቸውና ስማቸው የሚያመለክተው አና ቾይንካም እንዲሁ በትዊተር፣ «ወንጀል በመጨመሩ ምክንያት ሞተር ባይስክሎችን ማገድ፤ በፈተና ወቅት ማጭበርበር ይፈፀማል በሚል ኢንተርኔት እንደመዝጋቱ ያለ ነው። በዚህ አመንክዮም የሚጎዳ እንቅስቃሴን ለመግታት ሁሉንም ነገር ማገድ ሊመጣ ነው ማለት ነው። መንገዱን ከመዝጋት ለመሠረታዊ  ምክንያቱ መፍትሄ ይፈለግ።» የሚል አስተያየታቸውን አስነብበዋል።

ኤሊያም መሠረት በፌስቡክ የሰጠው አስተያየት ደግሞ እንዲህ ይነበባል፤ የታይላንድ ሞተረኞች! በታይላንድ ሞተረኞች እንዲህ ጎላ ተደርጎ የተፃፈ ልዩ የመለያ ቁጥር ይሰጣቸዋል። የዚህ ዋና ጥቅም ተገልጋዮች በቀላሉ የሞተረኛውን ማንነት እንዲለዩ ማረግ ቢሆንም ሞተሩ ወንጀል ቢፈፀምበት እንኳን ሊያመልጥ ሲሞክር ጎልቶ በሚታየው ቁጥሩ እንዲለይ ይሆናል። ከዛ ውጪ በከተሞች ይህን መለያ ሳያደርግ ቢዝነስ መስራት ይከለከላል። በሞተር የሚፈፀም ወንጀል ያስቸገራቸው ሌሎች ሀገራት ያስፈፀሙት ሌላው አማራጭ ደግሞ ሞተረኞች ሰው እንዳይጭኑ መከልከል ነው። ያው በአንድ ሰው ብቻም ወንጀል ሊፈፀም ይችላል፣ ይህ ግን ተደራጅተው ድርጊቱን የሚፈፅሙትን ለመቀነስ ያግዛል። እኛስ እነዚህን ብንጠቀም?» በማለትም ይጠይቃል።

የደራሲ አውግቸው ተረፈ ሕልፈት

በዚህ ሳምንት የበርካቶች አስተያየት በማኅበራዊው መገናኛ የተነበበው ከታዋቂው ደራሲ እና ተርጓሚ አውግቸው ተረፈ ሕልፈተ ሕይወት ጋር በተገናኘ ነው። በሳምንቱ መጀመሪያ ያረፈው የ68 ዓመቱ ደራሲ በብዕር ስሙ ይጽፍ እንደነበር የገለፁት አስተያየት ሰጪዎች በዚሁ በማኅበራዊ መገናኛው ለቀብሩም ሲጠራሩ ታይቷል። ደራሲ ውድአላት ገዳሙ፤ «ዕውቁ  ደራሲ እና ተርጓሚ አረፈ! በጎጃም ጠ/ግዛት፣ በብቸና አውራጃ፣ በእነማይ ወረዳ በምትገኘው ጋቸሟም ማርያም ቀበሌ በ1945 ዓ.ም.የተወለደው አንጋፋው ደራሲ ሕሩይ ሚናስ በሞት መለየቱ አሳዝኖኛል፣ ነፍስ ይማር!» ስትል፤ ፍሬው አበበ ደግሞ፤

«ደራሲ ሕሩይ ሚናስ (አውግቸው ተረፈ) ዜና ዕረፍት አሳዝኖኛል። በአንድ ወቅት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣ ባልደረባ ነበር። ነገርግን ሥራውን ጠልቶት እርግፍ አድርጎ በመተው ብሔራዊ ቲያትር አካባቢ ሜዳ ላይ የመጽሐፍ ችርቻሮ ንግድ ላይ መገኘቱ በወቅቱ ብዙዎቻችንን አስገርሞን ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በርካታ መጽሐፍትን ያሰነበበን ብርቱ ሰው ነበር። ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑርልን።» ብሏል።

Symbolbild Bücher lesen

« ኅሩይ የልቤ ወዳጅ የነበረ ሰው ነው። ከልቤ እሱን ለማግኘት ፈልጌ አልሆነልኝም። የማንበብ ፍላጎቴን ካሳደጉት ወዳጆቼ መካከል አውግቸው ተብሎ በብዕር ስም የሚጠራው ወዳጄ ነው። አንድም ቀን በብር እጦት ማንበብ እንዳላቆም የረዳኝ መልካም ሰው ነው። ስለ እርሱ ብዙ ሊሉ ከሚችሉት አንዱ ነኝ።የእውቀት ጥማቱ ይደንቀኛል፣ ለመርዳት የሚያደርገው ጥረት እንዳከብረው ረድቶኛል።» ያሉት ደግሞ ገዛኸኝ በቀለ ናቸው።

ራሔል ሲሳይ፤ «ነፍስ ይማር!....«ያንገት ጌጡ» ከምትለው  የአጫጭር  ልቦለዶች  መድብል  ውስጥ የተካተቱትን...«ያንገት ጌጡ፣ የገና ስጦታ እና እቃ ቤት ጠባቂው» ን አብዝቼ እወዳቸዋለሁ፡፡» ብላለች።

«ኦኦኦኦ ኢትዮጵያ ዛሬ አንድ  የጥበብ  ባለውለታዋን  ሰው  አጥታለች ። ደራሲ አውግቸው ተረፈ በተለይ እብዱ፣  ወይአዲስ አበባ  የተሰኙ  የድረሰት ሥራዎቹ  በሚገርም  ገፀባህሪይ አቅርቦ ለተደራስያን  ያቀረበ  ትልቅ  የጥበብ  ሰው  ማጣት  ምንኛ  ያሳዝናል  ነፍስህን  በብሄ ረ ገነት ያኖርልን ዘንድ  አንለምናለን።» ብለዋል አምባቸው መሐሪ። ዮናስ መስፍን፤ «ወይ አዲስ አበባ  የተሰኘውን መጽሐፉን  የመጀመሪያ  ደረጃ  ተማሪ  ሳለሁ  አንብቤው  ነበር። እያስመዘገብኩ ነው  የሚለው ድርሰቱም  ወደ ራዲዮ  ድራማ  ተቀይሮ  በግሩም  አተዋወን  በጋሽ  ፍቃዱ  ተክለማርያም  ቀርቦ እንደነበር  አስታውሳለሁ። ነፍስ ይማር።» ታምሩ ባልቻ ደግሞ በአጭሩ፤ «ታላቅ ጸሐፊ በሰላም ያሳርፍህ!» ብሏል። ጌዲኦ ጀባቲም « ይች ሀገር ትልልቅ ሰዎቿን  እየሸኘች  ነው ማነው የነገ ሰው ?» በማለት ጠይቀዋል።

አቶ ለማ መገርሣ የት ገቡ?

ሌላው በዚህ ሳምንት የብዙዎች ጥያቄ የሆነው ደግሞ አቶ ለማ መገርሣ የት ገቡ? የሚለው ነው። ለረዥም ዓመታት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት የነበሩት እና በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ ሞተር መሆናቸው በአደባባይ የሚነገርላቸው ለማ መገርሣ በቅርቡ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል። በአደባባይ ከታዩ ሰነበቱ በሚል ጥቂት የማይባሉ ወገኖች ፎቷቸውን በመለጠፍ አረ የትናቸው? ሲሉ ጠይቀዋል። አላዲን አላዊ ሲዲቂ በፌስቡክ፤

ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ።
አቦ ለማ መገርሳ የት ነው ያሉት? የት ነው የጠፉት? የት ነው የተደበቁት? ሀገር ውስጥ መኖር አለመኖራቸው እንኳ አይታወቅም። ብዙዎች ሰውዬው ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ይፈልጋሉ። ስለዚህ በአስቸኳይ ያሉበትን ሁኔታ ልትነግሩን ይገባል።» የሚል ዘለግ ያለ መልእክታቸውን አስፍረዋል።  ፋዲ ምሳፊም ይህንኑ በመደገፍ፤ « በትክክል ሊነገረን ይገባል። ስለ ድርጅቱ/ፓርቲው አያገባንም (እንድያገባንም አይፈልጉም) የሳቸው ጉዳይ ግን ያሳስበናል።» ብለዋል፤ ታሬ ቶክቻው ፀጋዬም፤ «ዜጎች የዚህ አይነት ጥያቄ  ሲያነሱ  መልስ  መስጠት  ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።» በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

 

Audios and videos on the topic