የሞሱሉ ዉጊያ፤ IS ፍፃሜ | ዓለም | DW | 03.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሞሱሉ ዉጊያ፤ IS ፍፃሜ

ኢራቅ፤ የኢራቅ አልቃኢዳ፤ አንሳር ኢስላም፤ አል-ነቅሻባብይ፤ የመሕዲ ጦር፤ አንሳር አል-ሱና፤ ሙጃሒዲን ሹራ፤ ሠላፊይ፤ በቅርቡ ደግሞ ዳኢሽ ወይም የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት ISIS ወዘተ የሚባሉ ቡድናት መደራጃ ማከፋፋይም የሆነችዉ ነፃ መዉጣትዋ፤ የዓለም ሠላም መከበሩን የልዕለ ኃያሊቱ ሐገር መሪ በነገሩን ማግሥት ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:38

የሞሱሉ ዉጊያ፤ IS ፍፃሜ

በ2003 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የኢራቅን ሕዝብ «ነፃ ለማዉጣት» ሐብታሚቱን አረባዊት ሐገር ላይ የወረዉ ጦር ዛሬም እዚያዉ ይዋጋል።የዓለም ብቸኛ ልዕለ ኃያል ሐገር መሪ ዶናልድ ትራምፕ ግን ጋዜጠኞችን ለመስደብ ይባትላሉ።አዉሮጶች የአረብ-አፍሪቃ ስደተኛ እንዳይመጣባቸዉ ድንበራቸዉን የሚዘጉ፤ የአፍሪቃ አንባገነኖችን በዩሮ የሚገዙበትን ብልሐት ያዉጠነጥናሉ።የዓረብ ቱጃር፤ኃያል፤ትላልቅ መንግስታት ባንድ አድመዉ አረባዊቷን ትንሽ ሐገርን ይቀጣሉ።ሶሪያዎች የዓለም ዘመናዊ ጦር መሳሪያ ይፈተሽባቸዋል።ኢራቆች በተለይ ሞሱሎች ዛሬም ያልቃሉ አስራ-አራተኛ ዓመታቸዉ። እስከመቼ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

                          

መጋቢት 2003 የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኢራቅን በቦምብ-ሚሳዬል ማንደድ፤ ድፍን ኢራቃዉያንን በሰቅጣጭ-አስደንጋጭ ድምፅ ማሸበር ሲጀምር ወረራዉ ባንድ ሰዉ ወይም ቡድን ላይ እንዳልነበረ ለመላዉ ዓለም ግልፅ ነበር።በወረራዉ የመጀመሪያ ሳምንታት ከአሜሪካዉ ዓለም አቀፍ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ CNNን መረጃ ለማግኘት የሞከረ ግን ወረራዉ ባንድ ሰዉ ያነጣጠረ ይመስል «ጥቃት በሳዳም ሁሴን ላይ» የሚል በትላልቅ ፊደላት የተፃፈ ርዕሥ ያነብ ነበር።

ያኔ የትልቂቱን ሐገር ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎችን ዘገባ «ሐሰት» ለማለት የደፈረ አልነበረም።ቢኖርስ ማን ሰምቶት።በአስራ-አራተኛ ዓመቱ

በቀደም የብቸኛዋ ልዕለ ኃያል ሐገር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶናልድ ትራምፕ FNN አሉት CNNን።የሐሰት ዜና መረብ እንደማለት።የሐሰት ምክንያት ተሰጥቶት፤ በሐሰት ዘገባ የተሸፋፈነዉ ወረራ ኢራቅን ከማጥፋት አልፎ ዩናይትድ ስቴትስን ማክሰሩ በተረጋገጠ ማግሥት የዛሬዉ ፕሬዝደት ወረራዉን ያወገዙት ዛሬ የሐሰት ዜና መረብ እያሉ በሚያበሻቅጡት ጣቢያ መሆኑ ነዉ ዚቁ።2008።

«ጦርነቱ ታላቅ ዉድቀት ነዉ።ጥፋት ነዉ።ከዚሕ ያነሰ አይደለም።ይሕ በመሆኑ አሳፋሪ ነዉ።እንደ እዉነቱ ያሁኑ ፕሬደንት አባት ኢራቅ ላይ ጦርነት ባለመክፈታቸዉ ከፍተኛ አክብሮት አለኝ።ጦርነቱን ካሸነፉ በኋላ ከዚሕ በላይ መሔድ የለብንም ብለዉ አቆሙ።ትክክል መሆናቸዉ ታዉቋል።እና ሳደም ሁሴይን አነሱ ወደዱትም አልወደዱት አሸባሪን ይጠላ ነበር።አሸባሪዎችን ገድሏል።አሁን ግን (ኢራቅ) የአሸባሪዎች መፈልፈያ ሆናለች።»

በርግጥም ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽና ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ያዘመቱት ጦር ኢራቅን ከወረረበት ከ2003 ጀምሮ ያቺ ሐብታም፤ የጥንታዊ ሥልጣኔ ምድር የአሸባሪዎች መደራጂያ፤ማከፋፈያና ማሰራጪያ ሆናለች።ቡሽ የብሪታንያዉን ጠቅላይ ሚንስትር አስከትለዉ ኢራቅን ሲወሩ የወረራዉ ዓላማ ኢራቆችን ከኢራቃዊ መሪያቸዉ ነፃ ለማዉጣት ነዉ ብለዉ ነበር።ወረራዉ እንደተጀመረ የአሜሪካ ትላልቅ ማሠራጪያ ጣቢያዎች «ጥቃት በሳዳም ሁሴን ላይ» እያሉ ዓለምን ለማደናበር የመኮሩትም የመሪያቸዉን የሐሰት ወረራ ለመደግፍ መሆኑን ለማወቅ ያኔም አሁንም የፖለቲካ ተንታኝን አስተያየት መጠበቅ አላስፈገም።

ቡሽ እንደ

ድል አድራጊ ጦር አዛዥ ወረራዉ በድል መጠናቀቁን ሲያዉጁም የነፃ ጋዜጠኝነት ሰባኪዎቹ የተጨባጩን ሐቅ ምንነት፤ የአዋጁን ትክክለኛነት፤የወረራዉን መዘዝ እንዴትነት ለማስተንተን አልቃጡም።አብራሐም ሊንከን ከተሰኘዉ አዉሮፕላን ተሻካሚ መርከብ የተንቆረቆረዉን የድል ብሥራት፤ ፌስታ ፈንጠዝያዉን ግን  በዓለም ናኙ።ግንቦት 1, 2003

                                  

«ኢራቅ ዉስጥ የሚደረገዉ ዋና ዉጊያ ተጠናቅቋል።በኢራቁ ጦርነት ዩናይትድ ስቴትስ እና ተባባሪዎቻችን አሸንፈዋል።ኃይላችን አሁን ፀጥታን በማስከበርና ሐገሪቱን ዳግም በመገንባት ላይ አተኩሯል።በዚሕ ጦርነት የተዋጋነዉ ለነፃነት እና ለዓለም ሠላም  ነዉ።ሐገራችንና ተባባሪዎችዋ በተገኘዉ ዉጤት ይኮራሉ።»

ቡሽ እና ተከታዮቻቸዉ እንዳሉት «ነፃነት» ከሆነ፤ ወራሪዉ ጦር የኢራቅን የ24 ዘመን ገዢ ከሥልጣን አስወግዷል።ኋላም ባደባባይ አሰቅሏል። ልጆች ቤተሰባቸዉን፤ ተከታይ አድናቂያቸዉን ከነሥርዓታቸዉ ገድሏል።ኢራቅ፤ የኢራቅ አልቃኢዳ፤ አንሳር ኢስላም፤ አል-ነቅሻባብይ፤ የመሕዲ ጦር፤ አንሳር አል-ሱና፤ ሙጃሒዲን ሹራ፤ ሠላፊይ፤ በቅርቡ ደግሞ ዳኢሽ ወይም የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት ISIS ወዘተ የሚባሉ ቡድናት መደራጃ ማከፋፋይም የሆነችዉ ነፃ መዉጣትዋ፤ የዓለም ሠላም መከበሩን የልዕለ ኃያሊቱ ሐገር መሪ

በነገሩን ማግሥት ነበር።

ከብዙዎቹ አሸባሪ ቡድናት ጠንክሮ የደረጀዉ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግስት (ISIS)ብሎ የሚጠራዉ ቡድን ኢራቅን ማተራመስ የጀመረዉ በ2012 ነበር።ቡድኑ በ2014  የኢራቅን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ሞሱልን እስከሚቆጣጠር ድረስ ግን ኃያሉ ዓለም ሥለቡድኑ የሚያዉቀዉን ለዓለም ማጋራት አልፈለገም።

አንዳድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ እስከ 2014 ድረስ ISIS ሲደራጅና ሲጠናከር እያዩ-እንዳላየ ያለፉት ባንድ በኩል አል-ቃኢዳን በሌላ በኩል የሶሪያዉን ፕሬዝደንት የበሽር አል-አሰድን መንግሥት ጦርን ያዳክምልናል በሚል ሥልት ነበር።በሰፊዉ ለመደራጀትና ለመጠናከር ረጅም ጊዜ ያገኘዉ ISIS ሰኔ 2014 በተቆጣጠራት ሞሱል ከተማ ኸሊፋዊ መንግስት ሲያዉጅ ግን ዓለም ቡድኑን ለማጥፋት ይራወጥ ያዘ።

አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅን ከወረረበት ከ2003 ጀምሮ ከጦርነት-ሽብር፤ ከእልቂት ስደት ሌላ፤ ሌላ ለማያዉቀዉ ለኢራቅ ሕዝብ ግን  ያዉ የተጨማሪ እልቂት ፍጅት ሌላ ምዕራፍ ነዉ።ቡድኑ ሞሱልን ከተቆጣጠረበት ከሰኔ 2014 እስካለፈዉ መጋቢት ድረስ ብቻ ሞሱል ዉስጥ በተደረገዉ ዉጊያ ብቻ ከ8000 ሺሕ በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

ባለፈዉ መጋቢት አጋማሽ የአሜሪካ ጦር አንዴ የተኮሰዉ ሚሳዬል ብቻ ከአንድ መቶ በላይ ሠላማዊ ሰዎች ገድሏል።ሚሳዬሉ ሠላማዊ ሰዎች በተሰበሰቡበት በምዕራባዊ ሞሱል ላይ ያነጣጠረበት ምክንያት፤የሞቱት ሰዎች ብዛት፤ እና ማንነት በሚያነጋግረበት መሐል፤ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግራ አጋቢ መልዕክት ተሰማ።ትራምፕ የኢራቅን ወረራ እንደሚቃወሙ በ2008 በግልፅ ተናግረዋል።በ2016 የምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅትም ደግመዉት ነበር።

                             

«በኢራቁ ጦርነት 2 ትሪሊዮን ዶላር አዉጥተንበታል።በሺ የሚቆጠር ሕይወት ከፍለንበታል።ኢራቅን እንኳ አልተቆጣጠርንም።የዓለም ሁለተኛዉ ነዳጅ የተከማቸባትን ኢራቅን፤ ኢራን ወስዳታለች።ጆርጅ ቡሽ ተሳስተዋል።»

የፕሬዝደትነቱን ሥልጣን በያዙ-በሁለተኛዉ ወር መጋቢት አጋማሽ ሞስል ላይ በአሜሪካ ሚሳዬል የተገደሉት ኢራቃዉን አስከሬን ሲቆጠር ትራምፕ ተቃራኒዉን አሉ።«ኢራቅ ዉስጥ ጥሩ እየሰራን ነዉ።ወታደሮቻችን ከዚሕ በፊት በማይታወቅ መንገድ እየተዋጉ ነዉ።ዉጤቱ በጣም ጥሩ ነዉ።ሁሉም ሰዉ ይወቀዉ።»

ሁሉም ሰዉ የሚያዉቀዉ ትራምፕ የፕሬዝደትነቱን ሥልጣን ከመያዛቸዉ በፊት ከተናገሩት ጋር መቃረናቸዉን ነዉ።ሁሉም ሰዉ የሚያዉቀዉ

የአሜሪካ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ኢራቅ ያዘመቱት ጦራቸዉን ዉጊያ በቅጡ አለማወቃቸዉን ነዉ።ኢራቅ የሚዋጋዉ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ጄኔራል  ስቴፈን ቶዉንሴንድ ጋር አለመደማመጣቸዉን ነዉ።

                   

«ያንን አካባቢ በመምታታችን  እኛ (ጥፋቱን) ሳናደርሰዉ አንቀርም።የመጀመሪያ ደረጃ ቅኝቴ ግድያዉን በማድረስ እኛ ሚና ሳይኖረን አይቀርም።የማላዉቀዉ እንዚሕን ሰዎች እዚያ የሰበሰበዉ ጠላታችን ይሆን ወይ የሚለዉ ነዉ።»ሞሱልን  ከISIS እጅ ለመማረክ ከ2014 ጀምሮ የኢራቅ መንግሥት ጦር፤ የኢራቅ ሺዓ ሚሊሺያዎች፤ የኩርዲስታን ጦር፤ የኢራን ሚሊሺያ፤የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን (ሒዝቡላሕ)፤ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራቸዉ የ60 መንግሥታት ጦር ካየር፤ከምድር፤ከባሕር ይዋጋል።አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በየሳምንቱ በአምስት መቶ ጨረር መራሽ ሚሳዬል ሞሱልን ትቀጠቅጣለች።

የኢራቅ ሕዝብም በአሸባሪዎች  ቦምብ፤በተባባሪዎቹ ሐገራት ጦር ሚሳዬል፤ በኢራቅ መንግሥት ጦር መድፍ አዳፍኔ፤ በሚሊሺያዎቹ ጥይት ዕለት በዕለት ይረግፋል።ይቆስላል፤ ይሰደዳል።እሳቸዉ የትንሽ ወንድ ልጃቸዉን ዕጣ ይተርካሉ።«በመጠምዘዢያዉ መንገድ በኩል ወደ ዉጪ ሸሸን።እሱ ሲሮጥ ፈንጂ ላይ ወጣ።ፈነዳ።ሮጥን ግን ቅልጥሙ ተቆርጦ ጭኔ ላይ ወደቀ።»

እኚሕኛዋ ደግሞ የሴት ልጆቻቸዉ መጥፋት ነዉ-የሚያንገበግባቸዉ።«ልጆቼ፤ ወይኔ ልጆቼ።ተከበዉ ነበር።ቤቱን የአዉሮፕላን ቦምብ መታዉ።ልጆቼን አጣሁ።እንነሱ ወዳሉበት እመለሳለሁ።ምናልባት ተርፈዉ እንደሁ ማየት እፈልጋለሁ።»

የባግዳድ መንግስት እንዳስታወቀዉ ካለፈዉ ጥቅምት ጀምሮ በተከፈተዉ የማጥቃት ዘመቻ ከዘጠኝ ሺሕ በላይ የኢራቅ መንግሥትና የተባባሪዎቹ ሚሊሺያ ቡድን አባላት ተገድለዋል።ስምት ሺሕ ያሕል የISIS ተዋጊዎች ተገድለዋል ተብሎ ይታመናል።ከሞተዉ ሠላማዊ ሕዝብ በተጨማሪ ከ860 ሺሕ በላይ ሕዝብ ከተማይቱን ለቅቆ ወጥቷል።የሞሱል ጥንታዊ ቅርሶች፤ ዘመናይ ሕንፃዎች፤ የመሠረተ ልማት አዉታሮች ወድመዋል።

ጥንታዊቱ፤ ዉብ፤ ትልቅ ለም ከተማ  ለወትሮዉ የሱኒ እስልምና ሐራጥቃ ተከታዮች የሚበዙባት ከተማ ናት።ከተማይቱን

ከISIS ለማስለቀቅ ባለፉት ሰወስት ዓመታት በተደረገዉ ዉጊያ ከኢራቅ መንግሥት ጦር በላይ ተዋጊ ያሰለፉት ግን የኢራን ሺዓ ሚሊሺያዎችና ፔሽ ሜርጋ የተሰኘዉ የኩርድ ጦር ናቸዉ።ISIS ሲጠፋ ሞሱል የምን ትሆናለች።የሱኒ፤ የሺዓ ወይስ የኩርድ።

የበርሊኑ የሳይንስና የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተመራማሪ ራይክ ሄንላይን የድል ማግስቱን ክፍፍል ድል አድራጊ ወደ ቴሕራን ይጠቁማሉ።

                      

« ኢራቅ ዉስጥ ብቻ ሕዝባዊ ዘመቻ በተባለዉi መርሕ ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ሚሊሺያዎች አሉ።እነዚሕ ሚሊሺያዎ ሺዓ ናቸዉ።የሺዓ እስልምና ሐራጥቃ አደራጅ ደግሞ ኢራን ናት።ይሕ ሲጤን ኢራን በተጨባጭ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለማድረስ እየጣረች ለመሆኑ ግልፅ ምልክት ነዉ።»

የኢራቅ መንግስት እንዳስታወቀዉ ጦሩና ተባባሪዎቹ ሞሱልን በዕለታት እድሜ ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠሯታል።እስካሁን በISIS  ቁጥጥር ሥር የሚገኘዉ የከተማይቱ አካባቢ ከ1 ስኩዌር ኪሎ ሜትር አይበልጥም።የዘመቻዉ አጠቃላይ ድል አዋጅ ሲጠበቅ ዛሬ  ግን የISIS ታጣቂዎች ባፈነዱት ቦምብ 14 ሰዉ አጥፍተዉ-ጠፍተዋል።ድሉ ይጠበቃል።ጥፋት-ሽብሩ ግን በርግጥ ቀጥሏል።  

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic