የሞምባሳ ፍርድ ቤትና የባህር ላይ ወንበዴዎች | ኢትዮጵያ | DW | 10.11.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የሞምባሳ ፍርድ ቤትና የባህር ላይ ወንበዴዎች

የሞምባሳው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዘጠኝ ሶማሊያውያንን ነጻ ለቀቀ። የዓለም ዓቀፉ የባህር ድርጅት ውሳኔው ለባህር ንግድ ኢንዱስትሪው አሳፋሪ ነው ይላል።

default

የሞምባሳው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትላንት የሰጠው ብይን በዓለም አቀፉ የባህር ድርጅት እይታ አሳፋሪ ሆኗል። የፍርድ ቤቱ ዳኛ ሞሀመድ ኢብራሂም የባህር ላይ ዘራፊዎች ተብለው ለፍርድ ቀርበው የነበሩትን ዘጠኙ ሶማሊያውያን አስፈላጊ ጥበቃና የደህንነት ከለላ ይሻሉ ሲሉ ነበር ነጻ የመሆናቸውን ውሳኔ የገለጹት። የትላንቱ የሞምባሳ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚሳዝን ነው ይላሉ የዓለም ዓቀፉ የባህር ድርጅት ዳይሬክተር ፑቲንጋል ሙኩንዳ፤

ድምጽ

«የውሳኔው መሰረት ምን እንደሆነ አናውቅም። እነዚህ የባህር ላይ ወንበዴዎች በዚህ መልኩ ነጻ እንዲሆኑ መደረጋቸው በጣም የሚያሳዝን ነው። የተሳሳተ መልዕክት የሚያስተላልፍም ነው። በዚያ ባሉት የወደብ መስመሮች ላይ ዝርፊያ ለሚፈጽሙት ወንበዴዎች ብርታትን የሚሰጥ ነው። በተለይ እንደ ኬንያና ታንዛኒያ ባሉት መስመሮች ዙሪያ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር ነው።»

የሞምባሳው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትላንት ነጻ ያደረጋቸው ዘጠኙ ሶማሊያውያን ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ነበር በጀርመን የባህር ኃይል የተያዙት። ወንበዴዎቹ ከጀርመንዋ ብሬመን ከተማ ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ፤ 18 የባህር ላይ ሰራተኞችን ይዛ የምትጓዝን አነስተኛ መርከብ ሊያግቱ ሲሞክሩ ነበር በቁጥጥር ስር የዋሉት። የሞምባሳው ፍርድ ቤት ግን በአዲሱ የኬንያ ህገ መንግስት ላይ ሶማሊያውያኑን በፍርድ ሊያስጠይቅ የሚችል ህጋዊ መሰረት የለም በማለት በነጻ እንዲሰናበቱ ወስኗል። የዓለም ዓቀፉ የባህር ድርጅት ዳይሬክተር ግን ውሳኔው ችግሩን ያባብሳል እንጂ የሚፈይደው ነገር የለም ይላሉ።

ድምጽ

«የውሳኔውን ህጋዊ ትንታኔ አላውቅም። ይህ የህገ መንግስት ጉዳይን የሚመለከት ሊሆን ይችላል። እኔ እንደሚመስለኝ ግን የውሳኔው ውጤት በባህር ላይ ዝርፊያ ዙሪያ በጥቅሉ የሚኖረው እንድምታ የከፋ ይሆናል። በዚህ ዓመት በሶማሊያ ከፍተኛ የሆነ የባህር ላይ ዛርፊያ እየተፈጸመ መሆኑን የሚያሳይ አሀዝ አለን። በእነዚህ የባህር ላይ ወንበዴዎች ላይ አንድ እርምጃ ካልተወሰደ የጥቃቱ መጠን ይቀንሳል የሚል እምነት የለኝም።»

የትላንቱ የሞምባሳው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በቅርቡ 17 ተጠርጣሪ የባህር ላይ ወንበዴዎች በነጻ እንዲሰናበቱ በተደረገ በቀናት ልዩነት የተላለፈ ነው። በቂ ማስረጃ አልተገኘባቸውም የተባሉት 17ቱ ተጠርጣሪዎች ከተለቀቁ በኋላ ትላን የሞምባሳው ፍርድ ቤት በተጨማሪ ነጻ ያላቸው ዘጠኙ ሶማሊያውያን ግን ከማስረጃ ጋር በተያያዘ ሳይሆን ተጠርጣሪዎችን የሚዳኝ ህግ አልተቀመጠም በሚል ምክንያት ነው። የሞምባሳው ፍርድ ቤት ዳኛ ሚሀመድ ኢብራሂም ተጠርጣሪዎቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ የመንግስት ግዴታ ነው፤ ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንጻርም መብታቸው ተጠብቆ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሊሸኙ ይገባል ባይ ናቸው። የዓለም ዓቀፉ የባህር ድርጅት ዳይሬክተር ፑቲንጋል ሙኩንዳ ግን የባህር ላይ ወንበዴዎቹ በሌላ ሀገር ፍርድ ሊያገኙ ይገባል ይላሉ።

ድምጽ

«ይህ የሀገራቱ ጉዳይ ነው የእኛ አይደለም። ከእኛ እይታ አንጻር የባህር ላይ ወንበዴዎች በእንዲህ መልኩ ነጻ እንዲሆኑ መወሰኑ ለባህር ንግድ ኢንዱስትሪው አሳፋሪ ነው። የእኛ እምነት እነዚህ የባህር ላይ ወንበዴዎች ከተያዙ ተገቢ በሆነ ችሎት ውሳኔ ሊሰጣቸው ይገባል። ችሎቱ በሶማሊላንድ አልያም በፑንትላንድ ወይም በሌላ የዓለም ክፍል ሊሆን ይችላል። ያ ችግር አይሆንም። ይህ በሰው ልጅ ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው።»

Audios and videos on the topic