የምግብ ዋጋ ንረት፣ መንስዔና መፍትሄው | ኤኮኖሚ | DW | 01.05.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የምግብ ዋጋ ንረት፣ መንስዔና መፍትሄው

የምግብ ዋጋ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መጠን መናር በወቅቱ በተለይ በታዳጊው ዓለም ብዙሃኑን ለከፋ ረሃብ እያጋለጠ ነው። የምርቱ እጥረትና የዓለም ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄድም ችግሩን በቀላሉና በአጭር ጊዜ የሚፈታ ነገር አያደርገውም።

default

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ተቋም ቀውሱን ድምጹን አጥፍቶ የመጣ ትሱናሚ፤ ማዕበል ነው ብሎታል። ዛሬ በታዳጊ አገሮች አያሌ ሕዝብን ከሕልውና ፈተና ላይ ለጣለው አስደንጋጭ ችግር እርግጥ የቆዩ ምክንያቶችም አሉት። የዓለም ንግድ ስርዓት ፍትሃዊ አይደለም። ምዕራቡ ዓለም በእርሻ ምርት የውጭ ንግዱ ረገድ የሚከተለው የድጎማ ፖሊሲም ከአፍሪቃ እስከ ላቲን አሜሪካ ድሃ ገበሬዎችን የፉክክር ብቃት በማሳጣት የገጠር ልማትን ሲጫን የቆየ ጉዳይ ነው። የታዳጊው ዓለም ቤት-ሰራሽ ችግሮችም የራሳቸው አስተዋጽኦ አላቸው። አስደንጋጭ ደረጃ የደረሰው የምግብ ዋጋ ንረት መሠረታዊ ምክንያቶቹ በጥቂቱ እነዚህ ናቸው።

የምግብ ዋጋ ሰማይ-ጠቀስ በሆነ መጠን መናር ከአሁኑ በርከት ባሉ ታዳጊ አገሮች ብርቱ የሕዝብ ተቃውሞን ሲቀሰቅስ እየተባባሰ በመሄድ ለሕብረተሰብ ሰላምና ልማት ጠንቅ እንዳይሆን ማስጋቱ አልቀረም። ሁኔታው በእርግጥም ከፍተኛ ለሆነ ስጋት መንስዔ የሚሆን ነው። በዓለም ባንክ መግለጫ መሠረት ሁኔታው በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት በአሁን መልኩ ከቀጠለ መቶ ሚሊዮን ሕዝብን ለባሰ ረሃብ ሊያጋልጥ የሚችል ነው የሚሆነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የዓለም ባንክ ይህንኑ በማጤን ሰሞኑን ችግሩን ለመቋቋም የተግባር ሃይል ለማቆም፤ እንዲሁም የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ወስነዋል።

በወቅቱ የታዳጊውን ዓለም ረሃብተኞች ለመርዳት አስቸኳይ ዕርምጃ መውሰዱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀደምት ዓላማ ነው። ግን ለዚህ ተግባር ስኬት የበለጸጉት ለጋሽ አገሮች የገቡትን የዕርዳታ ቃል ገቢር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የእስካሁኑ ልምድ ብዙም የሚያበረታታ አይደለም። ሆኖም የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክ እንዳሉት የወቅቱ ሁኔታ ፋታ የሚሰጥ አይደለም።

“ይህ የተፈጥሮ ቁጣ አይደለም። በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ግን ቀውስ ነው። የዓለም የምግብ ተቋም የሚጎለውን 750 ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ የዕርዳታ ቃል መገባት አለበት። 450 ሚሊዮን ዶላር ለማቅረብ ቃል ተገብቷል። ግን ቃል በመግባት ብቻ የተራበ ሆድን መሙላት አይችልም። ለጋሽ ሃገራት አሁኑኑ ገንዛባቸውን ጠረጴዛ ላይ ቁጭ በማድረግ የዓለም የምግብ ተቋም ለተግባሩ ሰፊ ነጻነት እንዲያገኝ ማድረግ አለባቸው”

በአጭር ጊዜ የሚጠበቀው ይህ ሲሆን በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የታዳጊ አገሮችን የእርሻ ልማት ማራመዱና የዓለም ንግድንም ፍትሃዊነት ማረጋገጡም ችግሩን በሚገባ ለመቋቋም ወሣኝ ነገሮች ናቸው። የዓለም ንግድን ፍትሃዊ ለማድረግ ከዓመታት በፊት የተጀመረው የዶሃ ድርድር ዙር በተለይ የበለጸጉት መንግሥታት በእርሻ ድጎማ ፖሊሲያቸው በመጽናታችው ሲከሽፍ በዚህም ተጎጂ ሆኖ የቀጠለው ይበልጡን የታዳጊው ዓለም ገበሬ ነው። ታዳጊውን ዓለም ከረሃብ ለማላቀቅ በውስጥም ሆነ በውጭ ተገቢው ዕርምጃ አልተወሰደም። Welthungerhilfe የተሰኘው የጀርመን የዓለም የረሃብ ዕርዳታ ድርጅት ባልደረባ ዶር/ራፋኤል ሽናይደር እንደሚሉት የአሁኑም የምግብ ቀውስ የዓመታት ጎጂ ፖሊሲ የቀሰቀሰው እንጂ ድንቀት ከሰማይ የወረደ ዱብ ዕዳ አይደለም።

“በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ድንገት የመጣ ቀውስ አይደለም። በየዜና አውታሩና በዓለም የምግብ ተቋም እንደተነገረው ድምጹን አጥፍቶ የመጣ ትሱናሚ፤ ማዕበል ነው ሊባል አይችልም። ይልቁንም ብዙ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ የረጅም ጊዜ ሂደት ውጤት ነው። ይህ እንግዲህ አንዱ ምክንያት ይሆናል። ዋናው ነገር ደግሞ ባለፉት ሁለት አሠርተ-ዓመታት በታዳጊዎቹ አገሮች የገጠርና የእርሻ ልማት ላይ የፈሰሰው ገንዘብ ጥቂት መሆኑ ነው”
ማለት በአፍሪቃ፣ በእሢያና በላቲን አሜሪካ የእርሻው ልማት ዕድል በሚገባ አልተሟጠጠም። ይህን አሁን በግድ ማሟላት ያስፈልጋል ማለት ነው። እስከ ገጠሮች የሚዘልቁ መንገዶች መዘርጋት፣ የመስኖ ይዞታዎች መሻሻል፣ የዕሕል ጎተራዎችም መታነጽ ይኖርባቸዋል። የምግብ ዋስትናን ለዘለቄራው ለማረጋገጥ መዋቅራዊው ዕርምጃ ቁልፍ ነው። ሆኖም በገጠር አካባቢዎች ይህን የምግብ ቀውስ ለመቋቋም መወሰድ ያለባችው ዕርምጃዎች ብዙዎች ናችው። እንግዲህ ተግባሩ ትዕግስትን የሚጠይቅ መሆኑ ነው።

“እርግጥም ጊዜ ይወስዳል። አሁን በተቀዳሚ ግን በአስችኳይ ዕርምጃ የተራቡትን በምግብ መርዳቱ አስፈላጊ ነገር ነው። ከዚሁ ተያይዞ የገጠር አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት የረጅም ጊዜ ልማትን ማራመዱ ግድ ይሆናል። መታሰብ ያለበት የዓለም ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ነው የሚሄደው። የምግብ ፍላጎቱም እንዲሁ ማደጉን ይቀጥላል። እና ይህ ሊታሰብ የሚገባው ነገር ነው” ራፋኤል ሽናይደር!

በአጭር ጊዜ ሲታይ ሌሎች ችግሩን የሚያከብዱ ሁኔታዎችም አይታጡም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የዓለም ባንክ አንዳንድ አገሮች ወደ ውጭ የሚሸጡትን ምርት ገደብ አድርጎ በመያዝ የሚወስዱት ዕርምጃ ለምሳሌ የምግብ ቀውሱን ያባብሳል ባይ ናቸው። የጀርመኑ የዓለም የረሃብ ዕርዳታ ድርጅት ባልደረባ ራፋኤል ሽናይደር በበኩላቸው ጥገኛ የሆኑት አገሮች በዚሁ ተጎጂ እንዳይሆኑ ነው የሚያሳስቡት።

“ይህን ጉዳይ ነጣጥሎ መመልከት ያስፈልጋል። የተትረፈረፈ ምርት ያላቸው አንዳንድ አገሮች አሉ። ታዲያ እነዚሁ ከውጭ ምግብ የሚያስገቡ አገሮች ከረሃብ ቀውስ ላይ እንዳይወድቁ ምርታቸውን ወደ ውጭ ከመሸጥ ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም። እና ጥገኞቹ አገሮች በዓለም ገበያ ላይ ሩዝ፣ ስንዴና በቆሎን የመሳሰሉ ምርቶች ለመግዛት መቻላቸው እጅግ አስፈላጊ ነው”

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የዓለም ባንክ የችግሩን ክብደት በማጤን የተግባር ሃይል ለማቆም ወስነዋል። ግን ይህ ቀውሱን ለመታገል ምን ያህል ጠቃሚና ፍቱን ሊሆን እንደሚችል በወቅቱ እንዲህ ብሎ መናገሩ አዳጋች ነው። ለማንኛውም ግን በልማት ትብብርና በምግብ ዕርዳታ ረገድ ተግባሩን በጋራ ማቀናበሩ ለስኬቱ ወሣኝነት ይኖረዋል። እስካሁን የተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማትና ኮሚቴዎች በነዚሁ ተግባራት ላይ ሲያተኩሩ ቆይተዋል።
በርከት ያሉ በልማትና በምግብ ዕርዳታ ላይ የተሰማሩ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማትም አሉ። አሁን ከነዚህ ሁሉ የሚጠበቀው እንግዲህ በተሻለ ሁኔታ በመነጋገር ተግባራችውን ማቀናበራችው ነው። እርግጥ ዋናው ነገር የተግባር ሃይል በማቆም አስቸኳይ ዕርምጃ ከመውሰድ ባሻገር የረጅም ጊዜ ልማትን ማራመድ መቻሉ ነው። ሆኖም ራፋኤል ሽናይደር አያይዘው እንደሚሉት ምዕራቡ ዓለምም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል።

“ምዕራቡ ዓለም በመጀመሪያ ደረጃ ምርቶቹን በረከሰ ዋጋ በታዳጊ አገሮች በማራገፍ የነዚሁኑ የእርሻ ዘርፍና ለፉክክር ብቁ ያልሆነውን ድሃ ገበሬ መጉዳቱን ማቆም ይኖርበታል። ድርጊቱ የታዳጊውን ዓለም የእርሻ ልማት ዕድል ለአሠርተ-ዓመታት ሲያወድም የኖረ ጉዳይ ነው። ይህ እንግዲህ የመጀመሪያው ዕርምጃ ይሆናል። ሌላው የምዕራቡ ዓለም ቀጣይና አስፈላጊ ዕርምጃ የረጅም ጊዜ ዕድገትን ለማረጋገጥ እንዲቻል የልማት ፖሊሲውን በእርሻ ልማት ላይ ያረፈ ማድረግ ነው። ይህ ከተሳካ የረሃብ ቀውስን መቋቋሙ የሚቻል ነገር ነው የሚሆነው”

የወቅቱ የምግብ ዋጋ መናር ላስከተለው ቀውስ የአውሮፓ ሕብረትም በተጠያቂነት መወቀሱ አልቀረም። የዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የኦክስፋም ባልደረባ ቲየሪይ ኬስተሎት እንደሚሉት ምንም እንኳ ከአጭር ጊዜ አንጻር በአውሮፓ ሕብረት የእርሻ ድጎማና በወቅቱ የምግብ ቀውስ መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት ባይኖርም የረጅም ጊዜው ሂደት ሲታይ ግን ታዳጊ አገሮች በሁለት እግሩ የቆመ የእርሻ ልማትን እንዳያራምዱ መሰናክል የሆነ ጉዳይ ነው። ሆኖም የሕብረቱ የእርሻ ኮሜሣር ቃል አቀባይ ሚሻኤል ማን ወቀሣውን አይቀበሉትም።

“ዕውነቱን ለመናገር ይህ ወቀሣ ጨርሶ አይገባኝም። ሕብረቱ የምግብ ምርቶችን በዝቅተኛ ዋጋ በዓለም ገበዮች ይሸጥ በነበረት ጊዜ ከ 15 ዓመታት በፊት ቢሆን ኖሮ ወቀሣው በተገባ ነበር። ያኔ ለውጭ ንግዱ ድጎማ የተደረገው ወጪ አሥር ሚሊያርድ ኤውሮ ደርሷል። ባለፈው ዓመት ግን ለመተሳሳይ ተግባር የወጣው 1,4 ሚሊያርድ ኤውሮ ብቻ ነበር”

የሆነው ሆኖ በምዕራቡ ዓለምና በታዳጊ አገሮች መካከል የሚካሄደው ንግድ አሁንም ፍትሃዊ መሆን ቀርቶ በከፊል እንኳ መሠረታዊ መሻሻል አድርጓል ለማለት አይቻልም። በዚህ በኩል ጠቃሚ ዕርምጃ መደረጉ ከመቼውም በላይ አስፈላጊ ነው የሚሆነው። አለበለዚያ የወቅቱን ቀውስ ማሸነፉ አዳጋች ሆኖ ይቀጥላል።