የምግብ ዋጋ ንረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት | ዓለም | DW | 29.04.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የምግብ ዋጋ ንረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት

እቅድ፣ ሐሳቡ ለረሐብ ለተጋለጠዉ ሕዝብ ተስፋ፣ ለበጎ አድራጊዎች ጥረት ብስራት መሆኑ አልቀረም።ገቢር የመሆኛዉ መቼና እንዴትነት ግን ቢያንስ ላሁኑ ጥያቄ ነዉ።

ዳቦዉ ተወድዷል

ዳቦዉ ተወድዷል


የምግብ ዋጋ ንረት የሚያስከትለዉ አደጋ በሚቃለልበት ሁኔታ ላይ የሚነጋገር አለም አቀፍ ጉባኤ በርን-ሲዊዘርላንድ ዉስጥ በመካሔድ ላይ ነዉ።ትናንት ተጀምሮ ዛሬ በሚያበቃዉ ጉባኤ ላይ ከሐያ-አምስት የሚበልጡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ልዩ ተቋማት ሐላፊዎችና ተጠሪዎች ተካፍለዋል።ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ለጉባኤተኞቹ እንደነገሩት የምግብ ዋጋ ንረትን ለማስወገድ ፈጣን እርምጃ ካልተወሰደ አደገኛ ቀዉስ ይከተላል።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝሩን አጠናቅሮታል።

በየጊዜዉ፣ በየሥፍራዉ በሚከሰተዉ ድርቅ፣ የዉሐ ሙላትና ግጭት በየአመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር የደኸዉ አለም ሕዝብ እንደተራበ ወይም ለረሐብ እንደተጋለጠ፣ እርዳታ እንደጠየቀ ነዉ።የአሁኑ ግን እስካሁን ከሚታወቁ፣ ከተለመዱትም ምክንያቶች የተለየ- ዉጤቱም አስጊ ነዉ።ድምፅ-አልባዉ ሱናሚ የሚል ቅፅል አበጁለት።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚገምተዉ አለቅጥ ያሻቀበዉ የምግብ ዋጋ ንረት ለአለም አንድ ሚሊዮን ተጨማሪ እርዳታ ፈላጊ ሕዝብ አትርፎለታል።

ዋና ፀሐፊ ፓ ጊ ሙን ለቤርን ጉባኤተኞች እንደነገሩት ደግሞ የድሆቹ ሐገራት ደሐ ገበሬ ካሁኑ ካልተረዳ አለም ካሁኑ ችግር ከባሰ ችግር ትዘፈቃለች።

«ከምግብ ዋጋ ንረት በተጨማሪ የማዳበሪያና የኤሌክትሪክ ሐይል ዋጋ በማሻቀቡ ምክንያት የአዳጊ ሐገራት ገበሬዎች ምርት በጣም ማሽቆልቆሉን አይተናል።አሁን ከደረሰዉ የምግብ እጥረት የባሰ ችግር ወደፊት እንዳይደርስ እነዚያን ገበሬዎች ለመርዳት የተቻለንን ሑሉ ጥረት ማድረግ አለብን።»

የአለም ምግብ ድርጅት ለዘንድሮዉ የአዉሮጳዉያን አመት፣-ሁለት ሺሕ ስምት ለምግብ ፈላጊዎች እሕል መግዢያ ይዞት የነበረዉ በጀት አሁን ባራት ወሩ እየተሟጠጠበት ነዉ።ወደ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ ካለገኘ የድርጅቱ የበላይ ጆስቴ ሺራን እንደሚሉት ለደሐዉ ሕዝብ ምግብ ማቃመስ አይቻልም።የደኸዉ ሕዝብ መከራ ደግሞ በሺራን አባባል ከሚታሰበዉ የባሰ ነዉ።


«የምግብ ዋጋ ንረት የመላዉ አለምን ገበያ እየጎዳዉ ነዉ።ለበለፀጉት ሐገራት ግን የዋጋዉ ልዩነት ይሕን ያሕል የሚባል አይደለም።የምግብ ኋላ ጣፋጭ ምግቦችን ማቆም እንችላለን።በሳምንት አንዴ ወይም ሁለቴ ሥጋ መብላት ማቆም እንችላለን።በቀን ካንድ ዶላር ያነሰ ገቢ ያላቸዉ ሰዎች ግን ማምለጫ የላቸዉም።እና እኛ የምንለዉ ከዚሕ ቀደም ይሕን ያሕል ችግር በማያዉቁ አካባቢዎች እንኳን ብዙ ሕዝብ እየተራበ ነዉ።ብዙ ሰዎች ምግብ እያጡ ነዉ።የተወሰኑት ደግሞ በቀን አንዴ ብቻ እየቀመሱ ነዉ።»

ችግሩ በርግጥ የጠና ነዉ።ፈጣን እርምጃ የሚያሻዉ።ዋና ፀሐፊ ፓ ጊ ሙን ከፈጣኑ እርምጃ የተወሰነዉ ተጀምሯዋል።

«ተጨባጭ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነዉ።የምርት እጥረቱን ለመቀነስ የአለም የእርሻና ምግብ ድርጅት (FAO) ዝቅተኛ ገቢ ላላቸዉ ሐገራት የእሕል ዘርና የእርሻ-ግብአቶች ለመስጠት የአስቸኳይ ጊዜ እቅድ ነድፏል።ድርጅቱ ለዚሕ እቅዱ ገቢራዊነት የ1.7 ቢሊዮን ዶላር በጀት ጠይቋል።የአለም ባንክ በበኩሉ ለዚሕ አላማ ስኬት አለም አቀፍ የድቀት መከላከያ ሥልት ለመዘርጋት እያሰበ ነዉ።»

እቅድ፣ ሐሳቡ ለረሐብ ለተጋለጠዉ ሕዝብ ተስፋ፣ ለበጎ አድራጊዎች ጥረት ብስራት መሆኑ አልቀረም።ገቢር የመሆኛዉ መቼና እንዴትነት ግን ቢያንስ ላሁኑ ጥያቄ ነዉ።