የምግብ ሸቀጦች የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ | ኤኮኖሚ | DW | 20.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የምግብ ሸቀጦች የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ በምግብ ምርቶችና ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት መከሰቱን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጥናት አመለከተ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:14

መግቻ ያጣው የዋጋ ንረት

በተለይም ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ መንግሥት ከወሰደው የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያእና ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ተከትለው በተከሰቱ የመንገድ መዘጋቶች ምክንያት የምርቶች ዝውውር በገበያ ውስጥ በመስተጓጎሉ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱንም አስተያየቶች ጠቁመዋል።              

ገዥው መንግሥት ኢህአዲግ በሀገሪቱ የተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ እና አለመረጋጋት የከፋ ችግር አላስከተለም ከቁጥጥራችን ውጭ አይደለም ይበል እንጂ በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት በንግድ ተቋማት እንቅስቃሴ እና በማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከባድ ጫና እያሳደረ መምጣቱን ነው አስተያየቶች የሚጠቁሙት :: የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በቅርቡ ያወጣው ጥናት ባለፈው ወር ብቻ በሀገሪቱ የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት 20.9 በመቶ ሲያድግ ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ደግሞ 9.8 ጭማሪ ማሳየታቸውን  ያመለክታል:: እንዲህ የዋጋ ግሽበቱ ከነጠላ ወደ ሁለት አሃዝ መሸጋገር ከቻለባቸው እና የዋጋ ንረቱ በደንብ መታየት ከጀመረባቸው ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች አንዱ ከውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው በኋላ መሆኑን የፎርቹን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፋሲካ ታደሰ ትገልጻለች። ከዛ በኋላ በብዙ የምግብ ነክ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል።


11 በመቶ የምጣኔ ሃብት እድገት አስመዝግባለች ሕዝቡም በቀን 3 ጊዜ በልቶ የሚያድርበት ሥልት ተነድፏል በሚባልባት ኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት እና የሸቀጦች ዋጋ መናር ፈታኝ እየሆነ መምጣቱ ለብዙዎች እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ነው የሚናገሩት :: ጋዜጠኛ ፋሲካም ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ለመሰረተ ልማት እና የግንባታ አገልግሎት ግብአት ተፈላጊ በሆኑ እንደ ብረታ ብረት ባሉ ምግብ ነክ ባልሆኑ ምርቶች ላይ ይታይ የነበረው የዋጋ ንረት ካለፈው ወር ወዲህ በተፈጠረው አድማ እና በመንገዶች መዘጋት ምክንያት ገበያ ላይ የምርት እጥረት በመከሰቱ በምግብ ነክ ሸቀጦችም ላይ ጎልቶ መንጸባረቁን ትናገራለች።


ባለፈው የካቲት ወር ጤፍ 33 ብር በኪሎ፣ የሽሮ እህል እስከ 40 ብር የኑግ ዘይት በሊትር 80 ብር አካባቢ ድፍን ምሥር እስከ አርባ ብር ገበያ ውስጥ ሲሸጡ የስኳር እና የስንዴ ዱቄት አቅርቦት እጥረት እንደነበርም መረጃዎች አመልክተዋል። የጥራጥሬ የአትክልት እና ፍራፍሬ በርበሬ እና ቅመማቅመም ምርቶችም የ 50 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል :: የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በያዝነው ዓመት የዋጋ ግሽበቱ በነጠላ አሃዝ ሥምንት በመቶ እንደሚሆን ቢተነብይም የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ ያደረገው የየካቲት ወር የዋጋ ግሽበት 15.6 በመቶ መሆኑን ያመለክታል :: በሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት በቀናት ውስጥ እጅግ እየናረ መሄድ እና አንዴ የጨመረ ዋጋ ምርት ቢትረፈረፍም ሲወርድ አለመታየቱ ሸማቹን ግራ ማግባቱ ይነገራል። የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ በበኩሉ ችግሩን ለመቅረፍ ባለፉት 6 ወራት ያለምክንያት ዋጋ የጨመሩ ከ 4 ሺህ በላይ ነጋዴዎችን ሱቅ የማሸግ ሰባት ሺህ ለሚሆኑት የጽሑፍ እና ለ 8,250 ነጋዴዎችም የቃል ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቋል።

እንዳልካቸው ፈቃደ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic