የምድር ነውጥና አደጋ መቀነሻው መላ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 06.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የምድር ነውጥና አደጋ መቀነሻው መላ

ሚያዝያ 17 ቀን 2007 ዓ ም በሂማላያ ተራሮች በምትገኘው ሀገር ፤ ኔፓል በሪኽተር መለኪያ 7,8 የደረሰ ብርቱ የምድር ነውጥ መዲናይቱን ካታማንዱን ጭምር ክፉኛ አርግፍግፎ፣ የአፈርና ቋጥኝ መደርመስ ፤ የቤቶችን መፈራረስ አስከትሎ ቁጥራቸው ከ 7,365

የማያንስ ሰዎችን ገድሏል , 14,000 ያህል አቁስሏል። በአጎራባች ሃገራት ቻይናና ሕንድም ይኸው የምድር ነውጥ ከ 100 በላይ ሰዎች ነው የገደለው። በኔፓል ከሞቱት ከ 7,365 በላይ ሰዎች 57 ቱ የውጭ ተወላጆች ሲሆኑ 112 ቱ ደብዛቸው እንደጠፋ ነው። የምድር ነውጥን የሚያስወግድ ኃይል ባይኖርም ውድመትን፤ መግታትም ሆነ መቀነስ ይቻላል?

በኔፓል ፣ የአደጋው መድረስ እንደታወቀ ፤ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የታቻለውን ለማድረግ ተንቀሳቅሷል። ኔፓል በቅድሚያ ነፍስ የማዳን ርብርብ ነበረ ያስፈለጋት። ከዚያም የህክምናና የምግብ ርዳታ! በዚህ ርብርቦሽ ፤ ሕይወት ለመታደግ የተሠማሩ የአገሪቱ ድርጅቶችም የታቻላቸውን ከማድረግ አልቦዘኑም።

«ቦቴዎችን ፣ ትልልቅ ቦቴዎችን፤ ለማከፋፈል በመጣር ላይ ነን። በሆስፒታሎችም የህክምና ተግባራትን ለማከናወን ፤ ቀዶ ጥገና ለማካሄድ የሚያስፈልጉትን ሁሉ በማቅረብ ላይ እንገኛለን። »

ይኸው የሰብአዊ ርዳታ ድርጅት እንደሚለው በድቀት ላይ ለምትገኘው ሃገር ሕዝብ ርዳታውን በተሟላ ሁኔታ ለማቅረብ ረጅም ጊዜ ማስፈለጉ አይቀሬ ነው።

«ግብረ ኃይላችን፣ ለማከናወን ብዙ የሚጠብቀው አለ። ሳምንት ፤ ሁለት ሳምንት 3 ወር ወይም፤ 6 ወር መፍጀቱ አይቀርም።»

በኔፓል መዲና በካታማንዱ፤ አይሮፕላን ማረፊያ መባልእትና አላቂ ዕቃዎች ለአገልግሎት እንዲከማቹ ለማድረግ፤ DHL በተሰኘው ማለት እ ጎ አ በ 1969 ፤ አድሪያን ዳልሲ ፤ ላሪ ሂልብሎም እና ሮበርት ሊን በተባሉ ግለሰቦች የተቋቋመውና ፤ በሦስቱ ሰዎች የቤተሰብ ስም የመጀመሪያ ፊደላት ተገጣጥሞ DHL በመባል የታወቀው የዓለም አቀፉ የመርከብ ጭነትና የፓኬት አገልግሎት ባልደረባና የካታማንዱውን ግብረ ኀይል ኀላፊነት ወስደው ሲያስተባብሩ የሰነበቱት ክሪስ ዊክስ----

«የአይሮፕላን ጭነት ካራገፍህ በኋላ፤ ቦታው ተመልሶ ባዶ እስኪሆን ድረስ ዕቃ የተከማቸበትን ቦታ እንደገና አትጠቀምበትም። የአይሮፕላን ጭነትን እንዲሁ ባዶ ቦታ ላይ መደርደሩም፤ በቦታው ለመጠቀም አያስችልም። የሚቆለል የተራገፈ ጭነትን በጊዜ ማንሣት አለመቻልም ሁኔታውን የከፋም ሆነ የሚያሥፈራ ያደርገዋል።»

የኔፓል ጦር ሠራዊት አባላት ለመርዳት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ። በተተከሉ ሰማያዊ ድንኳኖች በምድር ነውጥ ሳቢያ ቤተሰቦቻቸውን ዘመዶቻቸውን ያጡትን 2,8 ሚሊዮን ዜጎች ነው ለማገዝ የሚረባረቡት። ይሁንና ወታደሮቹ፣ አነስተኛ ጥቅል ዕቃዎችን በማመላለስ ነው የሚረዱት። በሰፊው የሚቀርብ ርዳታን ለመጫን ትልልቅ መሣሪያዎች ያስፈልጋሉ።

«ባለፉት 5 ዓመታት የጥቅል ዕቃዎችን መጠን ለማሻሻል ተችሏል። ከዚያ አያሌ ዓመታት በፊት ፣ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ጥቅል ዕቃዎች ቀስ በቀስ ነበረ የሚገቡት፤ አሁን ግን፤ በትልልቅ የጭነት አይሮፕላኖች እንዲቀርቡ ማድረግ ተችሏል።ጭቅል ዕቃዎቹን እንዲሁ ጡንቻ አለኝ !ብሎ ማንቀሳቀሱ አዳጋች ነው። ኔፓልን በመሰለ ሀገር መሣሪያው ፣ እንደልብ አይገኝም። እዚህ አሮጌ ዕቃዎችን ከተደረደሩበት ሰቅስቆ በማንሳት ሌላ ቦታ የሚያደርስ ማሺን አለ። 25 ዓመት ይሆናዋል። ግን ምን ይደረግ-! ባለን መሣሪያ ነው መጠቀም ያለብን።!»

አንዱ ችግር ሲወገድ ሌላው ይተካል። የክሪስ ዊክስ ባልደረባ ፤ ለምሳሌ ያህል ቀላል ዕቃዎችን ከአንድ ጥግ ወደሌላው የሚያንቀሳቅሱ ትራክተሮች ነዳጅ (ቤንዚን) እንደሌላቸው ሲገነዘቡ የሚሰማቸውን መገመት ይቻላል። መጫንም፣ ማራገፍም አዳጋች ነውና!

ብርቱ አደጋን ለመቋቋም ፣ ለጥሪ ምላሽ ሰጪ የሆነው ግብረ ኃይል፣ ባልደረባ የሆኑት ፖል ዶውሊንግ እንዲህ ብለዋል።

«ትልቅ ዓለም አቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ በሌለው አካባቢ ከባድ አደጋ ሲያጋጥም፤ ከተመሳሳይ ተግዳሮት ጋር ነው የምንጋፈጠው። ቦታ ፤ መሣሪያና ጥሬ-ሀብት የለም። ይሁንና እዚህ ከ 48 ሰዓት በላይ አሳልፈናል። ሁኔታዎችም ይበልጥ በተደራጀ መልኩ መከናወን መጀመራቸውንም በመታዘብ ላይ ነን።»

ተራራማይቱ ሀገር ኔፓል፤ በሺ የሚቆጠሩ ዜጎችን ብቻ አይደለም ያጣች። አያሌ ጥንታዊ ቅርሶችም ወድመውባታል።

«እንደሚመስለኝ ፤ ይህ ብርቱ ጥፋት በእጅጉ የሚያሳዝን ነው። ጉዳዩ የኔፓልን ተወላጆች ብቻ ሳይሆን መላውን የሰው ልጅ የሚመለከት ትልቅ የባህል ቅርስ እጦት ነው። ምክንያቱም ፤ እዚህ ያሉ መታሰቢያዎች ፍጹም ያማሩና በዓይነታቸው የተለዩ ናቸውና!»።

የምድር ነውጥ ያስከተለውን ውደመት ልክ እንደነበረው መልሶ መተካት ባይቻልም ፤ ተመሳሳይ አድርጎ ለመሥራት ጥረት ይደረጋል ነው የተባለው።

«በዝርዝር የቀረቡ ፎቶግራፎች አሉን። የህንጻ ንድፎችና ስዕሎች፤ መለኪያ መሣሪያዎችና የመሳሰሉትን ይዘናል። እነዚህ ሁሉ ወደፊት ለምናደርገው የመልሶ ግንባታ ተግባር መሠረቶች ይሆኑናል። ያም ሆነ ይህ ፤ እጅግ ሰፋ ያለ ወጪ የሚያስከፍል ነው። የኔፓል መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) ይህን መጠነ ሰፊ የመልሶ ግንባታ ሥራ ለማከናወን፣በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ትብብር ላይ ተስፋ አሳድሯል።»።

የመሬት መንቀጥቀጥም ሆነ የምድር ነውጥ የሚያጋጥመው ከዚህ ቀደም ፤ በዚህ ክፍለ ጊዜ ባለሙያዎች እንዳብራሩልን፣ በክፍለ ዓለማዊ የየብስና የባህር ወለል ንጣፍ መገፋፋት ፣ መጋጨት ወይም መፈርቀቅ ነው ። ይህም አሥራ ሁለት ገደማ በሚሆኑት የምድራችን የአፈርና ቋጥኝ ንጣፎች መካከል የሚያግጥም ነው። በምድራችን በተደጋጋሚም ሆነ በይበልጥ የምድር ነውጥ የሚጠናወታቸውና እሳተ ገሞራ የሚፈነዳባቸው አካባቢዎች ተለይተው ይታወቃሉ።

እነርሱም ለምሳሌ ያህል ፣ ከሰሜን አሜሪካ ከአላስካ ምዕራባዊውን ጫፍ በማካለል በደቡብ አሜሪካም በተመሳሳይ ሁኔታ ሰላማዊውን ውቅያኖስ ተንተርሶ የሚወርደው ተራራማ ምድር። ከሜድትራንያን ባህር ሰሜናዊ ጫፍ ተዋሳኝ ሃገራትን ይዞ ኢጣልያን ግሪክን ቱርክን ፣ ኢራንና ሂማልያን የሚያገናኛው የምድር የአፈርና ቋጥኝ ንጣፍ፤ የምሥራቅ አፍሪቃው ስምጥ ሸለቆ፤ ምዕራባዊው ቻይና ኢንዶኔሺያ ፊሊፒንስ ፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ ጃፓን ኒውዚላንድ ና በሰላማዊው ውቅያኖስ የሚገኙ የተጫፈሩ ደሴቶች ጭምር ይገኙበታል።

ኔፓል የምድር ነውጥ አደጋ የሚያጋጥማት ሀገር መሆኗ ከድሮ ጀምሮ ይታወቃል። እንዲያውም ፤ እ ጎ አ, በ 1934 አገሪቱን ያጋጠማት አደጋ ካሁኑ የባሰ እንደነበረ ነው የሚነገረው። ከኔፓል ቀጥሎ ፤ ትናንት ፤ ፓፑዋ ኒው ጊኒንም ፣ ብርቱ የምድር ነውጥ (በሪሽተር መለኪያ 7,5) ፤ አጋጥሟታል። ታዲያ በዚያም ሆነ ፣ በየትኛውም የምድር ነውጥ በሚያሠጋው አካባቢ፣ ከመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ራስን ተከላክሎ መኖር ይቻላል? የሚለው ጥያቄ የመልክዓ-ምድር ባለሙያዎችንም ሁሉ የሚያመራምር ጉዳይ ሆኗል። የሚሰጠው ምክርም በተለይ ለምድር ነውጥ ተጋላጭ የሆኑ አገሮች ታላላቅ ከተሞች፣ በካርታ ተለይተው እንዲታወቁ ማድረግ ብቻም ሳይሆን፤ የቤት ፤ የድልድይ፤ የሀዲድና የመሳሰሉ ግንባታዎችን በተለየ ልዩ ጥንቃቄ ማከናወን ይገባል የሚል ነው። ይህም ሲሆን ጥፋቱን ፤ ድቀቱን እጅግ መቀነስ ይቻላል፤ የምድርn ነውጥ ማስቀረት ግን በሠው ሠራሽ ጥበብ ከቶውንም የማይቻል ነው።

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic