የምድራችን ግለት መጨመርና አነጋጋሪ የሆነው ዓለም አቀፍ መፍትኄ፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 28.10.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የምድራችን ግለት መጨመርና አነጋጋሪ የሆነው ዓለም አቀፍ መፍትኄ፣

ከምድር ወደሰማይ አንጋጠን ስንመለከት አንድም የጠራ ሰማያዊ ቀለም ያለውን ኅዋ ፣ አለበለዚያም የተለያዩ የደመና ዓይነቶች ወይም አንድ ዓይነት ደመና ማየታችን አይቀርም።

default

እ ጎ አ ከ 1900 ዓ ም ወዲህ፣ዐቢይ ለውጥ እያሳየ ያለው የዓለም የአየር ንብረት ይዞታ፣

ደመናዎች ፣ እንዲሁ የተባዘተ ጥጥ አለያም ጥላሸት መስለው ፣ ባለቡት በመርጋት ሰማዩን ሸፍነው፣ ወይም ሰማዩን እንደባህር እየቀዘፉ ሲጓዙ እናያለን። በቀላሉ የሚበተኑ ቀለል ያሉ ጋዞችም ይመስሉናል። ግን አይደሉም። ክብደታቸው ፍጹም ከምንገምተው በላይ የገዘፈ ነው። የተባዘተ ጥጥ ወይም ነጭ የበግ ፀጉር የሚመስሉት ክፍልፋይ ደመናዎች ፣ በአንደኛው ጉማጅ ደመና ውስጥ ብቻ የሚቋር ውሃ 550 ቶና ያህል የሚመዝን ነው። ይህም ከሞላ ጎደል የ 100 ዝሆኖች ክብደት ያለው ነው ማለት ነው። ዶፍ የሚያስከትለው ጠቆር ያለው ደመና ደግሞ ክብደቱ ከ 200,000 ያህል ዝሆነች ክብደት የማያንስ ነው። ከውቅያኖስ ተነስቶ በአየር የሚከንፍ ማዕበል ደግሞ ፣ 250 ሚሊዮን ቶን ያህል ወይም የ 45 ሚልዮን ያህል የዝሆኖች ክብደት እንዳለው ጠበብት ይናገራሉ ። ሲያስቡት የማይመስል፣ ግን ሳይንስ ያረጋገጠው ሐቅ ነው።

ውሃ የቋጠሩና ሰማዩን እያቋረጡ የሚጓዙ ደመናዎች፣ በቀን፣ የፀሐይን ብርሃንና ሙቀት መልሰው ወደ ኅዋ በማንጸባረቅ፣ በየብስም ሆነ በውቅያኖስ ሙቀቱ መለስተኛ እንዲሆን ያግዛሉ። በቀን ፣ በተን አማካኝነት ያገኙትንና ያጠራቀሙትን ሙቀት በሌሊት መልሰው ወደ ምድር በማንጸበረቅ ለምድሪቱ ሙቀት ይሰጣሉ። ይህን የአየር ንብረት ተመራማሪዎች ጠንቅቀው የሚያውቁት ጉዳይ ነው። አስቸጋሪው፣ ምዝን የአየር ርጥበት፣ በምድራችን ዙሪያ እንዴት እንደሚከፋፈልና ፣ በዕለታዊና ወቅታዊ የአየር ጠባይ ላይ የሚያስከተለውን ተጽእኖ በትክክል የማወቁና የመተንበዩ ሁኔታ ነው። ለዚህም ነው፣ የአየር ንብረት ጠበብት፣ ከሙቀት መጠን ያልቅ፣ ስለዝናብ ለመተነበይ በእጅጉ የሚቸገሩት። በከባቢ አየር የውሃን ዝውውር ማወቅ ቢቻልም፣ በስፋት ሂደቱን ለክቶ ማውቅ የሚቻልበት ብልሃት ሲገኝ ብቻ ይሆናል ፣ ስለዝናብ ፣ ከሞላ ጎደል ትክክለኛነት ያለው ትንበያ ማቅረብ የሚቻለው።

የምድራችን የአየር ንብረት ይዞታም ሆነ ጠባይ በተለያዩ ምክንያቶች እየተለወጠ፣ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ በየጊዜው ይነገራል። አደጋው በኢንዱስትሪ የገሠገሡትንም በመልማት ላይ ያሉትንም ሁሉንም ይመለከታል። የዓለም የአየር ጠባይ መዛባት የሁሉ ችግር ነው። ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ማዕበል፣ የበረዶ መቅለጥ ፣ የደን መመንጠር የአፈር መሸርሸር ፣ በዓለም ዙሪያ የአደጋ በር በማንኳኳት ላይ ሲሆኑ፣ በጊዜም ባይሆን መለስተኛ ጥፋት ከደረሰ ወዲህ የዓለም ኅብረተሰብ ፣ ከኪዮቶ ወዲህ ምናልባት የላቀ አስተዋጽዖ ማድረግ የሚቻልበትን የአየር ንብረት ጥበቃ ነክ ውል ፣ ከኅዳር 28 እስከ ታኅሳስ 9 ቀን 2002 ዓ ም፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚያዘጋጀው፣ በደንማርክ መዲና ፣ በኮፐንሄገን በሚካሄደው የዓለም መሪዎች ጉባዔ ላይ ይፈርማሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው። የዓለምን የአየር ንብረት በጋራ መንከባከብ ፣ ለፕላኔታችን ህይወት ደጋፊነት ፣ አማራጭ የሌለው መፍትኄ ነው። ምድራችን ቀስ-በቀስ ከዓመት- ዓመት ፣ እየጋለች በመሄድዋ፣ በከባቢ አየር፣ በየብስና በውቅያኖስ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ፣ የተፈጥሮ በሚመስሉ ሆኖም የሰው ዐቢይ አስተዋጽዖ በታከለባቸው በተለያዩ አደጋዎች ሲገለጥ የምንሰማውና የምናየው ጉዳይ ነው። ሳይንቲስቶች፣ በምድር ግለት መጨመር ሳቢያ የሚደርሰው የአየር ንብረት ለውጥ፣ በምድር ዋልታዎች የበረዶ ኮረብታዎች እንዲናዱ፣ በረዶ እየቀለጠ ወደሚያጥለቀልቅ ጎርፍነት በመለወጥ ፤ ብርቱ ማዕበል በማስነሣትና ድርቅ በማስከትል ብርቱ ጉዳት እንደሚያደርስ ከማስጠንቀቅ የቦዘኑበት ጊዜ የለም።

ለምድር ግለት መጨምር ሰበብ የሁኑት ፣ ዋንኞቹ ጋዞች፣ የውሃ እንፋሎት፣ የተቃጠለ አየር (CO2) ፣ ሜቴን ጋዝ፣ ሳቅ-በሳቅ የሚያደርገው ፣ ናይትረስ ኦክሳይድ( N2O)፣ ኦዞንና ክሎሮ-ፍሉዎሮ-ካርበን ናቸው።

መጠናቸውም፣የውሃ እንፋሎት፣ ከ36-70 ከመቶ፣ የተቃጠለ አየር፣ ከ 9-26 ከመቶ፣ ሜቴን ጋዝ ከ 4-9 ከመቶ፣ እንዲሁም ኦዞን ከ 3-7 ከመቶ ድርሻ አለው።

ምድራችን ፤ ለሰውና እንስሳት ፤ በአጠቃላይ ህይወት ላላቸው ፍጡራን ሁሉ ተስማሚ መኖሪያ እንደሆነች እንድትቀጥል ከተፈለገ ፣ ለዚህ፣ ዐቢይ አስተዋጽዖ የሚያደርገው የተፈጥሮ አካባቢም እንዲጠበቅ ለማድረግ፣ የብሪታንያው ጋዜጣ The Times በዛሬው እትሙ ላይ እንዳስገነዘበው፣ ለምድራችን ግለት አስተዋጽዖ የሚያደረጉትን ጋዞች ለመቀነስ ውል መፈራረሙ ከመፍትኄዎቹ መካከል አንደኛው ብቻ ነው። በዘመናችን ዐቢዩ ጉዳይ፣ ኑሮአችን ጥሩና ቅጥ ያለው እንዲሆን ሳይንሳዊ መላ መሻት ነው ብሏል።

የኖቤል የሰላም ሽልማት ያገኘው የዓለም የአየር ንብረት ጥበቃ ጉዳይ ም/ቤት ፣ የፕላኔታችን የሙቀት መጠን ከ 2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ በፍጹም እንዳይንር ፣ እንዲያውም በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ከኢንዱስትሪው አብዮት በፊት በነበረው ደረጃ ላይ እንዲገኝ ጥረት ሊደረግ ይገባል በማለት ማሳሰቢያ እስከማቅረብ ደርሷል። በኮፐንሄገን ይፈረማል ተብሎ የሚጠበቀው የውል ሰነድ፣ እ ጎ አ በ 1997 ዓ ም፣ በኪዮቶ ፣ ጃፓን የተፈረመውንና እ ጎ አ እስከ 2012 ዓ ም ጸንቶ የሚቆየውን የስምምነት ሰነድ የሚተካ ነው። 37 በኢንዱስትሪ የገሠገሡ አገሮች፤ ከየፋብሪካዎቻቸው የሚትጎለጎለውን የተቃጠለ አየር እንዲቀንሱ፣ የኮፐንሄገኑ ውል ያሥራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። የአሜሪካ ም/ር ቤት፣ የኪዮቶውን ውል አላጸደቀውም። ግዙፎቹ አገሮች፣ ቻይናና ህንድ ደግሞ በድርድሩ እንዳልነበሩበት የሚታወስ ነው።

በኮፐንሄገኑ ስብሰባ የሆነው ሆኖ አዎንታዊ ሚና ይይዛሉ ተብሎ ነው የሚታሰበው። ጉባዔው ከመድረሱ በፊት፣ 4 ዐበይት ጥያቄዎች በማነታረክ ላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው። እነርሱም፣

(1) በኢንዱስትሪ የገሠገሡት አገሮች፣ የተቃጠለ አየርን ፣ በምን ያህል መጠን ይቀንሱ?

(2) በማደግ ላይ ያሉት አገሮች፤ ከኢንዱስትሪዎቻቸው የሚወጣውን የተቃጠለ አየር በምን ያህል መጠን ይጨምሩ?

(3) የበለጸጉት መንግሥታት፣ ታዳጊዎቹን፣ የተቃጠለ አየርን በመቀነሱ ረገድና የአየር ንብረት መዛባትን ለመቋቋም እንዴት ሊያግዙ ይችላሉ?

(4) እንዲሁም፣ ለአየር ንብረት ጥበቃ የሚመደበው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ፣ እንዴት ይያዛል? የሚሉት ናቸው።

ጥያቄዎቹ አጥጋቢ መልስ ማግኘት የሚችሉ መሆናቸውንም ሆነ በአጠቃላይ ውሉ በተሟላ ሁኔታ ፣ ዘንድሮ ማለትም በቅርቡ ኮፐንሃገን ውስጥ መፈረም መቻሉን፣ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉዳይ ተመልካች ባለሥልጣን Yvo de Boer በእጅጉ ነው የሚጠራጠሩት። De Boer የአውሮፓው ኅብረት መንግሥታት ፣ የአዳጊ አገሮች ለተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ይቆሙ ዘንድ በገንዘብ እንዲረዱ፣ የገንዘቡንም መጠን እንዲያሳውቁ አስገንዝበዋል። እርሳቸው በበኩላቸው ድሆች አገሮች ከአሁን ጀምሮ በያመቱ ፣ ቢያንስ 10 ቢሊዮን ዶላር ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያሉት።

የኮፐንሄገኑ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት፣ ቅድመ-ዝግጅት በተደረገባት የእስፓኝ ከተማ ባርትሴሎና በተካሄደ ጉባዔ የተሳተፉት ከጀርመን ታዋቂ የአየር ንብረት ጉዳይ ጠበብት መካከል ሞጂብ ላቲፍ፣

«ጠቃሚው ጉዳይ፤ በአጠቃላይ ፣ በዓለም ዙሪያ፣ የተቃጠለ አየርን በተለይም CO2 ን እስከ ምዕተ-ዓመቱ አጋማሽ ፣ ግማሽ- በግማሽ፣ እስከ ምዕተ-ዓመቱ ፍጻሜ ደግሞ 80% መቀነስ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ፣ የደረጁት መንግሥታት፣ አዳጊዎችን ለመርዳት፣ የላቀ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።»

ተክሌ የኋላ/አርያም ተክሌ