የምያንማር የሥልጣን ሽግግር | ዓለም | DW | 30.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የምያንማር የሥልጣን ሽግግር

ፕሬዝደንቷ «ወንበር ጠባቂ» ናቸዉ።ከምክትል ፕሬዝደንቷ አንዱ ጡረተኛ ጄኔራል ናቸዉ።ከዋና ዋና ሚንስትሮቹ ሁለቱ ጄኔራሎች ናቸዉ።ከምክር ቤት አባላት 25 በመቶዉ የጦር መኮንኖች ናቸዉ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:59
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:59 ደቂቃ

የምያንማር የሥልጣን ሽግግር

ምያንማር ከረጅም ዘመን ወታደራዊ አገዛዝ በኋላ ከሐገሪቱ ጦር ሐይል ያልወገኑ የመጀመሪያዉ ፕሬዝደንት ዛሬ ቃለ መሐላ ፈፅመዉ ሥልጣን ያዙ።በቅርቡ በተደረገዉ ምርጫ ብሔራዊ ሊግ ለዴሞክራሲ (NLD) የተባለዉን የፖለቲካ ማሕበር ለድል ያበቁት እዉቋ ፖለቲከኛ አዉንግ ሳን ሱቺ ቢሆኑም የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን የያዙት የቅርብ ታማኛቸዉ ሕቲን ክያዉ ናቸዉ።ሳን ሱቺ ከዉጪ ዜጋ ልጅ በመዉለዳቸዉ እና ልጆቻቸዉ ብሪታንያዊ በመሆናቸዉ የመሪነቱን ሥልጣን ለመያዝ የሐገሪቱ ሕግ አይፈቅድላቸዉም።ያም ሆኖ ከጀርባ ሆነዉ ሐገሪቱን የሚመሩት የሰባ ዓመቷ ባልቴት ሳን ሱቺ ናቸዉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ

ለወይዘሮ ኦዉንግ ሳን ሱ ቺ የዕድሜ ልክ ምኞት ስኬት፤ ለሕቲን ክያዉ የታማኝነታቸዉ መመዘኛ፤ ለሐገሪቱ የጦር ጄኔራሎች የበጎ ፈቃዳቸዉ ምልክት ነዉ-ዛሬ የሆነዉ።ለምያንማር የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ጅምር።በርማ።ያሁኗ ምያንማር በ1962 (እጎአ) የያኔዉ የጦር ሐይሎች አዛዥ ጁኔራል ኔ ዊን የሐገሪቱን

ሲቢላዊ መንግሥት በሐይል አስወግደዉ ሥልጣን ከያዙ ወዲሕ ከጦር ጄኔራሎች ወይም በጄኔራሎች ከሚሾም ታማኛቸዉ ዉጪ ሲቢል ፖለቲከኛ ሥልጣን ሲይዝባት የዛሬዉ የመጀመሪያዉ ናቸዉ።

ዛሬ ቃለ መሐላ የፈፀሙት የሰባ ዓመቱ አዛዉንት ሕቲን ክያዉ የታዋቂ ገጣሚ ልጅ፤ እራሳቸዉም ገጣሚ፤ ጎበዝ ተማሪ፤ በሳል ፖለቲከኛም ናቸዉ።ለፕሬዝደትነት ያበቃቸዉ ግን ከጥረት፤ ብስለት ዕዉቀታቸዉ ይልቅ ለአዉንግ ሳን ሱቺ ታማኝ መሆናቸዉ ነዉ።ቃላ መሐላ ከፈፀሙ በኋላ ባደረጉት ንግግርም እሳቸዉን ለፕሬዝደትነት፤ ፓርቲያቸዉን ለምርጫ ድል ያበቁት ኖቤል ተሸላሚዋ ፖለቲከኛ ሳን ሱቺ መሆናቸዉን ደጋግመዉ ገልፀዋል።እንደ ፕሬዝደንቱ ሁሉ ዘንድሮ ሰበኛ ዓመታቸዉን የደፈኑት ኦዉንግ ሳን ሱቺ የምያንምር የነፃነት ታጋይ፤ የጦር ሠራዊቱ መሥራችና ብሔራዊ ጀግና የአዉንግ ሳን ልጅ ናቸዉ።ዝንባሌያቸዉ ከአባታቸዉ ታሪክ፤ ሥምና ዝና ጋር ተዳምሮ እንደ ጎርጎርያያኑ አቆጣጠር በ1988 በብሔራዎ ሊግ ለዲሞክራሲ (NLD) ፓርቲ በኩል ፖለቲካዊን ተቀላቀሉ።ጉዞዉ፦ አደገኛ፤ አስፈሪ፤ ፈታኝም ነበር።

አባታቸዉ የመሠረቱት ጦር ጄኔራሎች ሴትዮዋን ለአስራ-ዓምስት ዓመታት በቁም እስረኝነት አግተዋቸዋል።ብሪታንያዊ ባለቤታቸዉ ሲሞቱም

እስረኛ ነበሩ።ብሪታንያዊ ሁለት ወንድ ልጆቻቸዉን ማየት የቻሉትም ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነዉ።የረጅም ጊዜ ትግላቸዉ አሁን በርግጥ ለዉጤት በቅቷል።ይሁንና ከዉጪ ሐገር ዜጋ የተጋባ ወይም የዉጪ ዜጋ የሆነ ልጅ ያለዉ ፖለቲከኛ በምያንማር ሕገ-መንግሥት መሠረት ምያንማርን መምራት ክልክል ነዉ።በዚም ምክንያት ሳን ሱቺ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ይዘዉ ፕሬዝደትነቱን ለረጅም ጊዜ ታማኛዉ መስጠት ግድነበረባቸዉ።

የጦር ጄኔራሎቹ ከብዙ ግፊትና ዓለም አቀፉ ጫና በኋላ ሳን ሱቺን ለቅቀዉ በቅርቡ የተደረገዉን ምርጫ ሲፈቅዱ በምርጫዉ የትኛዉም ፓርቲ ቢያሸንፍም ከሁለቱ ምክትል ፕሬዝደንቶች አንዱ ከጦሩ እንዲወከል ሕግ አፅድቀዉ ነዉ።የሐገር ዉስጥ እና የመከላከያ ሚንስትርነቱ ሥልጣን ሁል ጊዜ በጦር ሰራዊቱ እጅ ነዉ።ከሐገሪቱ ምክር ቤቶች መቀመጫዎች 25 ከመቶዉን የሚይዙት የጦር መኮንኖች ናቸዉ።

ምያንማር በርግጥ ከጦር ጄኔራሎች ቀጥታ አገዛዝ ተላቃለች።ይሁንና ፕሬዝደንቷ «ወንበር ጠባቂ» ናቸዉ።ከምክትል ፕሬዝደንቷ አንዱ ጡረተኛ ጄኔራል ናቸዉ።ከዋና ዋና ሚንስትሮቹ ሁለቱ ጄኔራሎች ናቸዉ።ከምክር ቤት አባላት 25 በመቶዉ የጦር መኮንኖች ናቸዉ።ምያንማር ዴሞክራሲን ጀምራዋለች።ግን ብዙ ይቀራታል።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች