የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦችና አፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 07.11.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦችና አፍሪቃ

የአፍሪቃ ምጣኔ ሀብት ያማልላል ። ይህ ደግሞ ቻይናና ህንድ ሳይቀሩ በአህጉሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕንቅስቃሴ ውስጥ ትልቁን ድርሻ በመያዛቸው ብቻ የሚገለፅ አይደለም ።

የመኪና መለዋወጫ ኢንዱስትሪ ሰራተኛ በደቡብ አፍሪቃ

የመኪና መለዋወጫ ኢንዱስትሪ ሰራተኛ በደቡብ አፍሪቃ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአዳጊ አገራት ልዩ ልዩ ች ግሮች በመፍትሄነት ያስቀመጣቸው የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች የተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ወደ ስምንት ዓመት ገደማ ነው የቀረው ። አንዳንድ የእስያና የላቲን አሜሪካ ሀገራት እነዚህን የልማት ግቦች በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ የማድረግ ዕድላቸው የሰፋ መሆኑ ይነገራል ። ይሁንና አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ አገራት ይህ የሚሳካላቸው እንደማይመስል ነው ከነባራዊው ሁኔታ መረዳት የሚቻለው ። የዶይቼቬለው ቶማስ መሽ እንደዘገበው ሰኞና ማክሰኞ እዚህ ቦን ውስጥ በልማት ጉዳዮች ላይ በተነጋገረው ስብሰባ ላይ አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ አገራት በዚህ ረገድ ብዙም ዕድገት ባያሳዩም ትክክለኛውን አቅጣጫ በመከተል ላይ ያሉ አንዳንድ አገራት መኖራቸው ተጠቁሟል ።
የአፍሪቃ ምጣኔ ሀብት ያማልላል ። ይህ ደግሞ ቻይናና ህንድ ሳይቀሩ በአህጉሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕንቅስቃሴ ውስጥ ትልቁን ድርሻ በመያዛቸው ብቻ የሚገለፅ አይደለም ይላሉ በጀርመንኛው ምህፃር ዴ.ኤ.ጌ የተባለው የጀርመን መንግስት የውጭ መዋዕለ ንዋይ ፍሰትና የልማት ጉዳዮችን የሚከታተለው መስሪያ ቤት ባልደረባ ዮሀንስ ዩርገን ቤርንሰን ። ቤርንሰን እንደሚሉት መስሪያ ቤታቸው ለአዳጊ አገራት ምጣኔ ሀብት ዕድገት ትልቅ ተስፋ ከሆኑት የግል ኩባንያዎች ጋር ይሰራል ። ለዓመታት ከዴ.ኤ.ጌ ጋር ከሚሰሩት ድርጅቶች አንዱ ወጣቱ አፍሪቃዊ የማባይል ስልክ ኩባንያ ሴልቴል ነው ። ኩባንያው በአህጉሪቱ በርካታ ቅርንጫፎች አሉት ። ሴልተንን እንደ ጥሩ ምሳሌ ያነሱት ቤርንሰን በአህጉሪቱ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ዕውን ለማድረግ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ነው የሚናገሩት ።
« የግሉ ዘርፍ ማደጉ ለምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች መሳካት እጅግ አስፈላጊ ነው ። በአንድ አገር ውስጥ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ሲጨምር ለኩባንያዎችም ሆነ ለአገሪቱ ዕድገት እንደሚያመጣና ድህነትንን ለመቀነስ እንደሚረዳ የዓለም ባንክ አስታውቋል ። ሆኖም በአንዳንድ አዳጊ አገራት እንደታየው የኢኮኖሚ ዕድገት በቀጥታ ወደ ድህነት ቅነሳ አይወስድም ። »
የመዋዕለ ንዋይን ፍሰት ለማበረታታት ደግሞ ቤርንሰን እንዳስገነዘቡት አዳጊዎቹ አገራት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር አለባቸው ። ለምሳሌ ህጋዊ ዋስትና መስጠት ይኖርባቸዋል ። በዚህ ረገድ ጋና እንደ ምሳሌ ትወሰዳለች ። የአለም ባንክ በተሀድሶ ተግባራቸው በዚህ ዓመት ካወደሳቸው አስር አገራት ውስጥ ጋና አንዷ ናት ። እንደ ቤርንሰን ለዕቅዱ መሳካት በሌላ በኩል ዓለም ዓቀፉ
ማህበረሰብም የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል ። ሌሎች የቦኑ የልማት ጉባኤ ተሳታፊዎች እንዳከሉትም የዓለም የንግድ ድርጅት በዶሀው ንግግሩ ለአዳጊ አገራት የሚጠቅም ውጤት ላይ መድረስ አለበት ። የቦኑ ጉባኤ ተሳታፊ ሞዛምቢካዊትዋ ማርያ ግራሳ ሶሞ ደግሞ የጉባኤውን ትኩረት ወደ ሌላ አቅጣጫ ነበር የወሰዱት ። እርሳቸው እንደሚሉት በሀገራቸው የድህነት ቅነሳ ዕውን ሆኗል ። ሆኖም በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ አልታየም ። በተለይ ሴቶች በሚመሩት ቤተሰብ ውስጥ የታየው ለውጥ አናሳ ነው ።
« ከሞዛቢክ ቤተሰብ ሰላሳ በመቶው የሚመራው በሴቶች ነው ። በቅርቡ የተካሄደ ጥናት ያሳየው በሀገሪቱ ድህነት በሀያ ስድስት በመቶ ቀንሶ የተገኘው አባወራዎች በሚመሩት ቤተሰብ ነው ። ሴቶች በሚመሩት ቤተሰብ ውስጥ የታየው ለውጥ ግን ስድስት በመቶ ብቻ ነው ። »
ግራሳ እንዳሉት ወቀሳው የሚያርፈው በዓለም ዓቀፉ የገበያ ፉክክር ላይ ነው ። በሞዛምቢክ የስክዋር ኢንዱስትሪ ውስጥ በርካታ ሴቶች ይሰራሉ ። በመጀመሪያ ደረጃ በተለያዩ ምክንያቶች ስራቸውን ሊያጡ የሚችሉት ሴቶች ናቸው ። ምቹ ባልሆኑ የስራ ሁኔታዎች እና በአስተኛ ደሞዝ የሚሰቃዩትም እንዲሁ ሴቶች ናቸው ። በሞዛምቢክ ሙስናን ለመዋጋት የተወሰደው ዕርምጃ ውጤት አምጥቷል ። በመልካም አስተዳደር ውስጥ ፀረ ሙስናው ትግል እጅግ አስፈላጊው ነው ። በተባበሩት መንግስታት የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች የአፍሪቃ አስተባባሪ ናይጀሪያዊው ታጁዲን አብዱልራሄምም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ ። ለጉባኤእውም የሀገራቸውን የናይጀሪያን ተሞክሮ አስረድተዋል ።
« ሙስና የህብረተሰባችንን ዕድገት ይጎትታል ። ሆስፒታሎችን መልካም አስተዳደርን ትምህርት ቤቶችን እንደነጠቀን ጥያቄ የለውም ። ዲሞክራሲን ለማስረፅ በምናደርገው ጥረት ከአፍሪቃዊትዋ አገር ናይጀሪያ በሙስና ወንጀል ምክትል ፕሬዝዳንት ከስልጣን ተወግዷል ። የሀገሪቱ ፖሊስ ዋና አዛዥም በተመሳሳይ ክስ ወህኒ ወርደዋል ። በርካታ አገረ ገዥዎችም በተመሳሳይ ሂደት ውስጥ ነው ያሉት ። »