1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራብ ኦሮሚያ ተፈናቃዮች የርዳታ ጥሪ

ዓርብ፣ መስከረም 18 2016

በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ከተለያዩ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በሚያጋጥማቸው የርዳታ እጥረት መማረራቸውን ገለጹ ። ተፈናቃዮቹ በአካባቢው በሰፈነው የጸጥታ ሥጋት ምክንያት ወደ ቀዬያቸው ተመልሰው ሕይወታቸውን መግፋት ፈታኝ እንደሆነባቸው ገልጸዋል ።

https://p.dw.com/p/4Wx9s
የርዳታ እህል ፦ ፎቶ ከማኅደር
የምግብ ርዳታው መቋረጡ ተፈናቃዮችን ለብርቱ ችግር መዳረጉ ይነገራል፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Ashraf Shazly/AFP

ተፈናቃዮች በምግብ እጥረት እያማረሩ ነው

በኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች የምግብ ርዳታ እያገኙ እናዳልሆነ በመግለጽ አማረሩ ። በክልሉ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ከተለያዩ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በሚያጋጥማቸው የርዳታ እጥረት እጅግ መቸገራቸውን ገጸዋል ። ተፈናቃዮቹ በአካባቢው በሰፈነው የጸጥታ ሥጋት ምክንያት ወደ ቀዬያቸው ተመልሰው ሕይወታቸውን መግፋት ፈታኝ እንደሆነባቸው ጠቁመዋል ።ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎችበተከሰተው የምግብ እጥረት ሰዎች በረሐብ መሞታቸውን ሰሞኑን ዘግበናል ። 

የሚቆራረጥ ያሉት የርዳታ አቅርቦት ኑሮዋችን እጅግ  አክብዶብናል ሲሉም አማረዋል ። መንግስት በበኩሉ የዓለማቀፍ ረጂ ድርጅቶች የድጋፍ አቅርቦት ማቋረጣቸው ክፍተቶችን ከፈጠሩ ጉዳዮች መካከል ናቸው ሲል ያማርራል ።

«እኛ ማረስ ማንደፋረስ የለመድን ሰዎች» በፀጥታው ችግር ከቀዬያችን ተፈናቅለን ልጆቻችንን ማስተማር አንችል፤ ሁሉን ነገር አጥተን ቀኑም ጨልሞብን በወር 15 ኪ.ግ. እህል ከመንግስት ርዳታ እንጠባበቃለን ሲሉም አማረዋል ።

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ተፈናቃዮች ሮሮ

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ውስጥ ለዘመናት ሃብት ንብረትና ቤተሰብ አፍርተው ሲኖሩ የነበሩ ሁሴን የተባሉ ተፈናቃይ በፀጥታ ችግር ከተፈናቀሉ በኋላ ስላጋጠማቸው የርዳታ እጥረት በምሬትት የገለጹት ነው፡፡ በርካታ ተፈናቃዮች ርዳታ አጣን በማለት እያማረሩ ነው።  የያነው አርሶ አደር የአሁኑ ተፈናቃ አቶ ሁሴን ከድፍን ቤተሰቦቻቸው ጋር ከተፈናቀሉ አሁን ሦስት ኣመታት ነጎዱ፡፡ አቶ ሁሴን አሁን ንብረታቸው በግጭት ከወደመበት አሙሩ ወረዳ ወጥተው በሌላ አከባቢ በተፈናቃይነት ተጠልለዋል፡፡ ወደ ቀዬያቸው ተመልሰው መደበኛውን ሕይወታቸውን መምራት የሚናፍቁት ተፈናቃዩ አሁንም ድረስ አልተፈታም ያሉት የጸጥታ ችግሩ ግን ያሰጋቸዋል፡፡

ርዳታ መቋረጡ ችግሩን አባብሷል ይባላል
የርዳታ እህል አቅርቦት መቋረጥ ብርቱ ፈተና ደቅኗል ምስል Million Haileselassie/DW

«ከኛ ጋር አከባቢውን ለቀው ያልወጡ ወገኖቻችን በዚያ ያሉም አሉ፡፡ በዚያው አሁን ሁሉም መሰረተ ልማቶች ከተቋረጠባቸው ሦስት ዓመታት ሆኗቸዋል ። ሦስት ዓመታት ሙሉ ትምሕርት፣ ሕክምና መንገድ እና ገቢያ አያገኙም፡፡ አሁን በቅርብ ጊዜ፤ ነሐሴ 29 ቀን እዛ አካባቢ በጣም ተኩስ ፈጥሮባቸው ብዙ ወገኖቻችን ናቸው ያለቁት ። አሁንም በጣም እየተሳቀቁ ነው ያሉት ። እና እንደው መንግሥት ቢደርስላቸው እና ምናልባት ሠረተ ልማቱንም እንዲያገኙ ከኦሮሞ ኅብረተሰብ ጋርም እርቅ እንዲፈጥሩ ድምፅ እንድትሆኑኝ ብዬ ነው በዚህ አጋጣሚ ።»

የምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ተፈናቃዮች ሮሮ

ሌላው አስረተያየት ሰጪ የምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ተፈናቃይ ናቸው፡፡ እኚህ አስተያየት ሰጪም የጸጥታ ስጋቱ አሁንም ድረስ በአከባቢው አለማባራቱንና ግድያ እና መፈናቀሉ አለመቆሙን በመግለጽ ነበር አስተያየታቸውን የጀመሩት፡፡ አስተያየት ሰጪው ከምንም በላይ ግን የርዳታ እጥረቱ እሳቸውን ጨምሮ ተፈናቃይ ማኅበረሰቡን ማማረሩን ነው ያነሱልን፡፡ 

«ድጋፉ አሁን ክረምቱ ከገባ ወዲህ ቆሟል፡፡ መንገዱ ጭቃ ስለሆነ አላሳልፍ ብሏቸው ይሆን ርዳታው ከላይም ባለመኖሩ አናውቅም፡፡ አሁን ርዳታ እየመጣልን አይደለም፡፡ እዚህ ኪረሙ ሰው ተፈናቅሎ ከተማ ከተሰበሰበ ሦስት ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ አርሶ አደሩ ወጥቶ ማረስ ባለመቻሉ መንግስት ከስንት አንዴ የሚያቀርብላቸውን ርዳታ ነው የሚጠባበቁት፡፡ የአርሶአደር ቤት ተቃጥሎ ማሳውም ጦም አድሯልና መሬት ባለመታረሱ ደን ሆኗል፡፡ ሁሉም እዚህ ይንከራተታል የሚሠራ ግን የለም፡፡ አከባቢው ተስፋ ያለበት ባለመሆኑ እዚህ ልማትም የሚሰራ የለም፡፡ ርዳታ ከስንት ጊዜ አንዴ ሲመጣ ስድስትም ይሁን አስር ቤተሰብ ብኖርህ 25 ኪሎ ብቻ ታገኛለህ፡፡ አሁን እሱም ጠፋ፡፡”

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ በመንዲ ከተማ ተፈናቃዮችምስል Negassa Dessalegen/DW

እንደ እኚህ አስተያየት ሰጪ በወረዳው ገጠራማ አከባቢ በብዛት መሬት አልታረሰም፡፡ ከ50 ሺህ በላይ የገጠር ቀበሌያት ነዋሪም ተፈናቅለው ወደ ወረዳዋ ከተማ ተሰደው የመከራ ጊዜውን ያሳልፋሉ፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪም ይህንኑን አስተያየት ያጠናክራሉ፡፡ «ተፈናቃይ ነን ። በብዛት እዚህ ሰው በረንዳ ነው የሚያድረው፡፡ ጾሙን ሚያድር ሰው አለ፡፡” 

ዶይቼ ቬለ ስለ ተፈናቃዮቹ አቤቱታ አስተያየትና ማብራሪያ ለመጠየቅ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ለተባሉ ለኦሮሚያ አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ ወይም (ቡሳ ጎኖፋ) የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ማሊቻ ሎጄ በመደወል የጽሑፍ መልእክትም ብጽፍላቸውም ለዛሬ ምላሻቸውን ባለማግኘቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡ 

ለምግብ ርዳታው እጦት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ አታለል አቦሃይ ግን በሰጡን አስተያየት የርዳታ ተቋማት ለወራቶች ድጋፋቸውን ማቋረጥ የአቅም ውስንነት መፍጠሩን አውስተዋል፡፡ «እንደሚታወቀው ርዳታ ሰጪ ተቋማት ከእና ጋ በተለያዩ ምክንያቶች  ርዳታ መስጠት አንችልም ብለው ካቆሙ [ርዳታ ተቋማቱ ድጋፍ ካቆሙ] 8 ወራት ሆኗቸዋል ። ያን መንግስት ክፍተት ለመሙላት መንግሥት ከመጠባበቂያ ምግብ ክምችት መጋዘኖቹ ባለፈው ለአራት ሚሊየን የሚሆን ዜጎች በድርቅ፤ በጎርፍ እና አፋጣኝ የምግብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው እና እንዲሁም በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ለአራት ሚሊየን ዜጎች ርዳታ ለግሷል ። አሁን ሁለተኛ ዙር ልንለግስ ነው።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ በመንዲ ከተማ ተፈናቃዮች፤ አብዛኞቹ ህጻናት እና ሴቶች ይበልጥ ተጎጂዎች ናቸውምስል Negassa Dessalegen/DW

እንደሚታወቀው በእየ 45 ቀኑ ነው የሚሰጠው ። ስለዚህ መንግሥት ከምግብ መጠባበቂያ ክምችትቶቹ አውጥቶ ከሚቀጥለው ሰኞ ጀምሮ ቀጣይ የድጋፍ ሂደቱን ለመቀጠል መንግስት ሙሉ ዝግጅቱን ጨርሷል ርዳታዎቹን ለመስጠት ። ስለዚህ እነሱም [ቅሬታ ያቀረቡ ተፈናቃዮች]የርዳታው ተጠቃሚ ይሆናሉየሚል ሐሳብ አለኝ ።»

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ሚሊየን በላይ ዜጎች በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 8 ሚሊየን ያህል የሚገመቱቱ በግጭት የተፈናቀሉ መሆናቸውም ይነሳል፡ ።»

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር