1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምስራቅ አፍሪቃው ድርቅ መዘዝ

ሐሙስ፣ መጋቢት 21 2015

ደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ተንሰራፍቶ የከፋ ጉዳት ያስከተለው የተራዘመው የምስራቅ አፍሪቃ ድርቅ በኢትዮጵያ የባሰውን ጉዳት ካደረሰባቸው አከባቢዎች የሶማሌ ክልል ሌላ ተጠቃሽ አከባቢ ነው፡፡ በክልሉ የዳዋ ዞን የቤት እንስሳትን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የጨረሰው ድርቅ አሁን ደግሞ በጎርፍ ስጋት ተተክቷል፡፡

https://p.dw.com/p/4PVzu
Dürre und Trockenheit am Horn von Afrika
ምስል Mulugeta Ayene/AP Photo/picture alliance

በምስራቅ አፍሪቃ የተራዘመው አስከፊ ድርቅ ከ1 ሚሊየን በላይ ህዝብ ማፈናቀሉና ከ10 ሺህ የሚበልጡ እንስሳትን መግደሉ እየተነገረ ነው፡፡በደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በበቂ ሁኔታ የጣለው የድርቁ ማብቂያ የመሰለው ዝናብ ተስፋን ቢያጭርም እየጣለ ያለው ዝናብ ከባድ በመሆኑ የጎርፍ እና ተጨማሪ የእንስሳት እልቂትን አስከትሏል ተብሏል፡፡በቀጣይም በድርቁ የተፈናቀሉ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለማቋቋም ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያሻ ተነግሯል፡፡
ሥዩም ጌቱ ዝርዝር ዘገባ አለው።
“አሁን እኛ ጋ ያለው ተጨባጭ እውነታ ዝናብ ከዘነበ ገና ሁለት ሳምንታት ብቻ እያለፈ በመሆኑ በቂ ሳር አልበቀለም፡፡ የጣለው ከባድ ዝናብ እንዳውም የከብቶች እልቂት እንዲባባስ ነው ያደረገው፡፡ ይህ  የሆነውም በተራዘመው ድርቅ ሳቢያ የተጎዱ ከብቶች ይህን መቋቋም ባለመቻላቸው ነው፡፡ የሰው ህይወትም እስካሁን የቆየው በመንግስት እና የተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ ነው እንጂ እኛ እንደሆን ያለንን ከእጃችን ከጨረስን ሰነባብተናል፡፡ አሁን ተስፋችን በቂ ዝናብ ማግኘታችን ነው፡፡ ነገር ግን ባገኘነው በቂ ዝናብ አርሰን ዘር ለመዝራት የምናርስበትም በሬ የምንዘራውም ዘር የለንም፡፡ መንግስት ማዳረስ ብከብደውም የተወሰነ ጥረት ጀምሯል፡፡ ለተወሰኑ ሰዎች በትራክተር አርሶ እየዘራላቸው ነው፡፡ አሁን እኔ እንደምኖርበት ቀበሌ እንኳ 500 አባወራዎች ቢኖሩም እድሉን ያገኙ 10 ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ አሁንም ተቀምጠን ድጋፍ ብቻ አንጠብቅም ብለን እየተደጋገፍን በሰው በቁፋሮም በምንም ለማረስ እየጣርን ነው፡፡ የዘንድሮ ዝናብ ከወትሮም ቀድሞ ከመጋቢት 05 ጀምሮ በመጣሉ አሁን ሳርም እያበቀለ ነውና ይህ ተስፋ ቢሆነንም እስካሁን ብዙ ከብቶች ዝናብ ባለመቋቋም ማለቃቸው ስጋታችንን ከፍ አድርጓል፡፡”
የቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ የቡሌዳንዲ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት የሰባት ቤተሰብ አስተዳዳሪ አቶ ሃልካኖ ዱባ እሳቸውን ጨምሮ የአከባቢው ማህበረሰብ ላይ አሁን ስላለው ተስፋ እና ስጋት ለዶይቼ ቬለ ያጋሩት አስተያየት ነው፡፡ 
ሌላው የዞኑ ነዋሪና በመምህርነት ሙያ የተሰማሩት ዱባ ቡራ እንደሚሉት፤ አሁን ላይ በደቡብ ኢትዮጵያ በአስከፊ ድርቅ ከተመቱት አከባቢዎች በዋነኛነት በሚጠቀሰው ቦረና ዞን በቂ ሊባል የሚችል ዝናብ ተዳርሷል፡፡ አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት የጣለው በቂ ዝናብ ግን የማህበረሰቡን ችግር በአንድ ጀንበር የሚፈታ አይደለም፡፡ “አሁን እውነት ለመናገር የጣለው ዝናብ ሁሉንም አከባቢ አዳርሷል፡፡ ያው ዝናቡ ውሃ እንጂ እህል ስለማይዘንብ አሁንም ህብረተሰቡ መልሶ እራሱን እስኪያቋቁም ድረስ ድጋፍ ያሻዋል፡፡ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና ይድረሰውና በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብዙ ድጋፍም እየመጣ ለህብረተሰቡ እየተከፋፈለ ነው፡፡ ስጋታችን ግን ከዝናቡ መዝነብ ጋር ተያይዞ ድጋፉ እንዳይቋረጥ ነው፡፡ አሁንም የምግብ ድጋፍ መቀጠል አለበት፡፡ ከዚያን ዝናብ በመዝነቡ ህብረተሰቡ የሚያርስበትና የሚዘራ ዘር ያስፈልገዋል፡፡ አሁን ሰው በእጁ እያረሰ የከረመበትን ችግር እንዴት ልቋቋም ይችላል፡፡ መንግስት በትራክተር የማረስ ውስን ጥረት ብጀምርም ይህም ሰፍቶ በርካቶች ጋ ካልደረሰ ችግራችን አይቀረፍም፡፡ ዝናብ ግን አሁን ለምሳሌ እንደ ሞያሌ፣ ዋጪሌ እና አልወዬ ባሉ ወረዳዎች ከመጠን በላይም በመጣሉ በርካታ የቤት እንስሳትን ገድሏል በጎርፍም ወስዷል፡፡ በዱብሉቅም ተፈናቃዮች የተጠለሉበት መጠለያ እንኳ በጎርፍ በመጎዳቱ ለዚህም ትኩረት ያስፈልጋል፡፡”
ደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ተንሰራፍቶ የከፋ ጉዳት ያስከተለው የተራዘመው የምስራቅ አፍሪቃ ድርቅ በኢትዮጵያ የባሰውን ጉዳት ካደረሰባቸው አከባቢዎች የሶማሌ ክልል ሌላ ተጠቃሽ አከባቢ ነው፡፡ በክልሉ የዳዋ ዞን አደጋ ስጋት መከላከል አስተባባሪ አቶ አብዱረሺድ ኢብራሂም በተለይም ለጣቢያችን እንደገለጹት የቤት እንስሳትን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የጨረሰው ድርቅ አሁን ደግሞ በጎርፍ ስጋት ተተክቷል፡፡ “መጀመሪያ ላይ የነበረብን ችግር የምግብ፣ የውሃ እና መጠለያ ነው፡፡ ድርቁ ለአራት ዓመታት የተራዘመ ስለነበር አርብቶ አደሩ መጠለያ አልባ ሆነዋል፡፡ አሁን ቢያንስ በጣለው በቂ ዝናብ የውሃው ችግር ተቀርፎልናል፡፡ ነገር ግን የበዛው ዝናብ የጎርፍ አደጋን እያስከተለ የሰው ህይወት ላይም አደጋ አድርሷል፡፡ በድርቅ የተጎዱ የቤት እንስሳትም ከባዱን ዝናብ ባለመቋቋም በገፍ አልቀዋል፡፡ ጎርፉ በየትምህርት ቤቶች እና ጤና ጣቢያዎችም ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ የኑሮ ዘይቤው የተመሰቃቀለበት አርብቶ አደር አሁን ላይ የመጠለያ ጉዳይም ስጋት ሆኖበታል፡፡”
በዳዋ ዞን ብቻ ከ31 ሺህ በላይ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታና መጠለያ እንደሚያስፈልገው እና ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በድርቅ ሳቢያ በዚሁ ዞን ከ334 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት ማለቃቸውን ያብራሩት የአደጋ ስጋት መከላከል አስተባባሪው አሁን ለአከባቢው ማህበረሰብ አንገብጋቢ ነው ያሉትንም ዘርዝረዋል፡፡ “ምግብ፣ መጠለያ እና የውሃ ማጣሪ አሁን በአንገብጋቢነት የሚያስፈልጉን ድጋፎች ናቸው፡፡ ይህ አከባቢ አስቀድሞም ኮሌራ ስጋት ያለበት ስለሆነ አሁን ደግሞ ይህ ጎርፍ ያንኑን ስጋት እንዳያባብስ አስግቶናል፡፡ አሁን ከ31 ሺህ ገደማ ተፈናቃዮች ለአንድ ሺህ ሰው ብቻ ነው መጠለያ ማቅረብ የቻልነው፡፡”
አሁንም በክልሉ እና በፌዴራል መንግስት የተለያዩ የእርዳታ ቁሳቁሶች ወደ አከባቢው እየተላኩ መሆኑንም የገለጹት አስተባባሪው በቀጣይም ድጋፉ በመንግስት አቅም ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ ይመለከተኛል የሚል አካል እንዲረባረብ ጠይቀዋል፡፡ 
ደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደ ሶማሊያ እና ሰሜን ኬንያ ባሉ የአፍሪቃ ቀንድ በተከሰተው አስከፊ ድርቅ ለተጎጂዎች አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልግ በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ IGAD ከሰሞኑ መጠየቁ ይታወሳል። ድርጅቱ እንደገለጸው በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው 47 ሚሊየን ሕዝብ በከፍተኛ የምግብ ዋስትና ስጋት ላይ ሲሆን፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ በተራዘመው ከባድ ድርቅ ምክንያት ታይቶ የማይታወቅ ተግዳሮት ገጥሟልም። 
በድርቁ መዘዝ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ሲፈናቀል ከ10 ሚሊየን በላይ ከብቶች እና የዱር እንስሳት ማለቃቸውንም ኢጋድ አመለክቷል። በቀጣይ አራት ወራት ውስጥ በድርቅ ለችግር የተጋለጡ አካባቢዎችን ለመርዳትም ኢትዮጵያ 710 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ኢጋድ አመልክቷል። ኬንያም ድርቁ ላጠቃቸው አካባቢዎች እስከመጪው ጥቅምት ወር ድረስ ምግብ፤ ውኃ እና ክትባት ለማቅረብ 378 ዶላር፤ ሶማሊያ ደግሞ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ነገሮችን በድርቅ በተጎዳው አካባቢ ለሚኖረው እና በሀገር ውስጥ ለተፈናቀለው ማኅበረሰብ ለማቅረብ የ1,6 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንደምትፈልግ ተገልጿል። 
ስዩም ጌቱ 
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
 

Ätrhiopien Dürre in der Guji-Zone
ምስል DW
Äthiopien | Folgen von Dürre - Totes Vieh
ምስል Hamar Woreda Government Communication Affairs Office
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ