የምስራቁ ቀውስ | ኤኮኖሚ | DW | 08.08.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የምስራቁ ቀውስ

ጅጅጋ፣ ቀብሪ ደሐር እና ደጋሐቡርን በመሳሰሉ ከተሞች የመገበያያ ማዕከላት፣ ሱቆች እና ባንኮች ተዘርፈዋል፤ ንብረቶቻቸውም ወድሟል። የመጓጓዣ አገልግሎቱም እንደተቋረጠ ነው። ሔጎ ተብለው የሚጠሩት እና በቀድሞው የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር እንደተደራጁ የሚነገርላቸው ወጣቶች በዘረፋው ዋና ሚና ነበራቸው የሚል ክስ ይሰማል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:03
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:03 ደቂቃ

በቀውሱ ሔጎ ተብሎ የሚጠራው የወጣቶች አደረጃጀት ከፍ ያለ ሚና ነበረው

ቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ለልብስ ቅድ ባለሙያው የጅጅጋ ወጣት እንደ ወትሮው የሥራ ቀን ነበር። ከሱቁ አራት የልብስ ስፌት መኪኖቹ ይጠብቁታል፤ ከመደርደሪያው ላይ በአይነት በአይነት የተሰቀሉት ጨርቆች ተቆርጠው፣ ተሰፍተው ልብስ ሊሆኑ የተዘጋጁ ናቸው። በዕለቱ ወደ ሱቁ ሲገባ ግን ሁሉንም እንደነበረው አላገኘውም። "የወሰዱትን ወስደው መውሰድ ያቃታቸውን ሰብረውታል፤ የጫኑትን ጭነው አፈራርሰውታል። ቢያንስ ወደ 50,000 ጥሬ ብር ነበር። እሱን ወስደውታል። ሱቁ ውስጥ ስትገባ ምድረ በዳ ነው የሆነው" የሚለው የልብስ ቅድ ባለሙያ ወደ 200,000 ብር የሚገመት ንብረት እንደወደመበት ይናገራል።

ስሙን መግለጽ የማይፈልገው የልብስ ቅድ ባለሙያው ሱቅ ተዘርፎ በተቃጠለበት ቅዳሜ ዕለት ላለፉት 12 አመታት በጅጅጋ የኖሩት አቶ ደበበ ግርማ ወደ መሐል ከተማ ለግብይት አቅንተው ነበር። አቶ ደበበ በነበሩበት የገበያ አካባቢ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ያገኙትን ሁሉ ሲደበድቡ ተመልክተዋል። ያስደነገጣቸው ግን ሕግ የማስከበር ኃላፊነት በተጣለባቸው ጸጥታ አስከባሪዎች ፊት የተፈጸመው ድርጊት ነው። "አንድ ትልቅ ፎቅ አለ። ውስጡ የመዋቢያ እቃ መሸጫ፣ ምግብ ቤት እና ሱቆች ነበሩ። በአካባቢው የነበሩ ወጣቶች ግር ብለው ገቡ። ከዚያ ዘረፋ ተጀመረ። እሱን ሲያዩ በየቦታው ሁሉም መዝረፍ ጀመረ" ሲሉ የዕለተ-ቅዳሜውን ኩነት ያስታውሳሉ።

በዕለተ-ቅዳሜው ኹከት ከተዘረፉት መካከል የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ይገኝበታል። የባንኩ የጥናት እና ኮምዩንኬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ በለጠ ዋቅቤካ በደረሰው የጸጥታ ችግር ጠባቂዎች ተደብድበው አሁን ሆስፒታል ናቸው። ሰራተኛ ቢሮ ውስጥ የለም። በጥበቃ እየተጠበቀ ነው። ሥራ እየተሰራ አይደለም። የተወሰኑ እቃዎች እና የቅርንጫፉ ንብረቶች ተሰባብረዋል፤ ተወስደዋል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በዕለቱ ባንኮች፣ ሱቆች፣ የመገበያያ አዳራሾች፣ ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል። ሰኞ እና ማክሰኞ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስራ አልጀመሩም። በጊዜያዊነት የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መሥተዳድር ሆነው የተሾሙት አቶ አሕመድ አብዲ በዛሬው ዕለት የመንግሥት ሰራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ማስተላለፋቸው ተሰምቷል። ከሐረር እና ድሬዳዋ ወደ ከጅጅጋ ይሰሩ የነበሩ የሕዝብ መጓጓዣዎች ሥራቸውን አቋርጠዋል። የንግድ እንቅስቃሴው ፈፅሞ ተገቷል፤ ከጅጅጋ ወደ ቶጎውጫሌ፤ ሶማሌላንድ እና ሐርጌሳ የሚያመሩ መንገዶች ዝግ ናቸው።

ዘግይቶም ቢሆን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጠው የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቱ "በጥቂት የአመራር ቡድን" የተፈጸመ እና  "የአገሪቱን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል" ያለመ ነበር ብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሕመድ ሽዴ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ "ሥልጣን እነጠቃለሁ" የሚል ሥጋት በቀሰቀሰው አለመረጋጋት ሰዎች መገደላቸውን፣ የገንዘብ እና የሐይማኖት ተቋማት መዘረፋቸውን እና መንገዶች መዘጋታቸውን ተናግረዋል።

የጅጅጋው ቀውስ ግን በዚያው አልተገታም። የፋፈን ወንዝን ተንተርሳ በተመሰረተችው ቀብሪ ደሐር ተመሳሳይ ድርጊቶች ተፈጽመዋል። ሱቆች፤ የመገበያያ ማዕከላት፣ የመንግሥት ሰራተኞች የሚያዘወትሯቸው ምግብ ቤቶች የዘረፋው ሰለባ ሆነዋል። ቀላፎ፣ ጎዴ እና ደገሐቡርን የመሳሰሉ ከተሞች ዛሬም እንቅስቃሴዎቻቸው እንደተገታ ነው። ነዋሪዎቻቸው ምግብ እና ውሐን ጨምሮ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን እንኳ ማሟላት እንደተሳናቸው ይናገራሉ። ሥጋትም ተጭኗቸዋል።

ሔጎ ማነው?

በጅጅጋ ከተማ የመገበያያ ሥፍራ በተፈጸመው ዘረፋ ሔጎ ተብለው የሚጠሩት እና በቀድሞው የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር እንደተደራጁ የሚነገርላቸው ወጣቶች ፊት አውራሪ እንደነበሩ አቶ ደበበ ግርማ ታዝበዋል። አቶ ደበበ "ሔጎ የሚባል የወጣቶች ድርጅት አለ። የክልሉ ወጣቶች እንዲደራጁ ያደረገው አብዲ ነው። ዘረፋውን የጀመሩት እነሱ ናቸው" ሲሉ ያስረዳሉ። የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መሥተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር የክልሉን ተቋማት አዳክመው ለጥቅም ተካፋዮቻቸው የሚመች ሥርዓት አቁመዋል ሲሉ ከሚተቿቸው መካከል አቶ አብዱልፈታ አቡበከር አንዱ ናቸው። አቶ አብዱልፈታ "የፕሬዝዳንቱን አካሔድ የሚደግፍ የተደራጁ ወጣቶች ቡድን ነው። ብርም ያከፋፍላቸዋል። በጣም ትስስር አላቸው" ሲሉ ሔጎ ስለሚባለው የወጣቶች አደረጃጀት ያስረዳሉ።  

ልዩ ኃይል እና የሕግ የበላይነት

ጅጅጋን ጨምሮ ተለያዩ የሶማሌ ክልል ከተሞች በተፈጸሙት ጥቃቶች ሰለባ የሆኑት  በአጥቂዎቹ መጤ የተባሉት ናቸው። ሕግ የማስከበር ኃላፊነት የተጣለባቸው፤ ሰልጥነው፣ ቃል ገብተው መሳሪያ የታጠቁት የልዩ ኃይል አባላት ግን በዝርፊያ የተሰማሩ ወጣቶችን በርቱ ባይ ሆነዋል እየተባሉ ይወቀሳሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች "ቆመው አዘርፈውናል" ሲሉ ይከሷቸዋል። አቶ አብዱልፈታ የልዩ ኃይሉ አባላት "ታማኝነታቸው ለህዝብ እና ለሕግ ሳይሆን ቀጥታ ለፕሬዝዳንቱ ነው። እነሱ ከሕግ በላይ ናቸው። ያገር ሽማግሌ፣ የክልሉ ምክር ቤት ምናምን ተውእና ከፕሬዝዳንቱ ውጪ ሊናገራቸው የሚችል በኢትዮጵያ ምድር ላይ የለም" ሲሉ ይናገራሉ።

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ድሬዳዋ፤ሐረር እና መላው የሶማሌ ክልል የነበራቸው የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል። ስልክም ቢሆን በአግባቡ እየሰራ እንዳልሆነ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ቀውሱ መቼ እና እንዴት እንደሚፈታ እርግጠኛ ሆኖ መናገርም ቸግሯቸዋል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

 

 

Audios and videos on the topic