የምርጫ ዝግጅትና ተቃዉሞ በኮንጎ | የጋዜጦች አምድ | DW | 13.06.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የምርጫ ዝግጅትና ተቃዉሞ በኮንጎ

የተመድ: የፀጥታዉ ምክር ቤት አባላት፤ ትናንት፤ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ መሪዎች፤ የምርጫ ቅስቀሳና ዝግጅታቸዉን፤ በእርጋታ እንዲይዙት አሳሰቡ።

የተ.መ.ድ. ወታደሮች በኮንጎ

የተ.መ.ድ. ወታደሮች በኮንጎጨምረዉም፤ በሚቀጥለዉ ወር መጨረሻ ለሚካሄደዉ ምርጫ፣ የዝግጅት ሂደቱ፤ የጎሳ ግጭት፣ ሊጪሩ የሚችሉ ዉጥረቶችን እንዳይፈጥር፣ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።

በአገሪቱ የሚካሄደዉ፤ ታሪካዊ ምርጫ ሲቃረብም፤ በተለይ፤ ኪንሻሳን ለማረጋጋት የሚገባዉን የዉጪ ኃይል፤ በመቃወም፣ እንቅስቃሴዎች መታየት ጀምረዋል። ዋነኛ የተባሉት የተቃዋሚ ፓርቲዎችም፤ በምርጫዉ አንካፈልም ማለታቸዉ ዉጥረቱን አባብሶታል።

ፖሊስ አስለቃሽ ጭስና፤ ጥይት፤ ወደሰማይ በመቶኮስ ነዉ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል፤ ዉይይት መካሄድ አለበት፤ በኮንጎ የዉስጥ ጉዳይ፤ የዉጪ ጣልቃ ገብነት ይቁም፤ በማለት በኪንሻሳ ጎዳና፤ የተሰለፉትን የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች፣ ለመበተን የሞከረዉ።

መጀመሪያ ላይ የተቃዉሞ ሰልፈኞቹ መፈክርና ባንዲራቸዉን እያዉለበለቡ በተዳከመችዉ ኪንሻሳ ከተማ ማዕከል ሲንቀሳቀሱ ፖሊስ አልከለከለም ነበር። ኋላ ላይ ግን ለመበተን እርምጃዉን ወሰደ።

ከሰልፈኞቹ መካከል አንድ መምህር እንደተናገሩት እስከ ሰኔ 23ቀን 1998ዓ.ም ድረስ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ መካከል የጠየቁት ዉይይት ካልተካሄደ ዕለቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ነዉ ከወዲሁ የተነበዩት።

የተቃዉሞ ሰልፉ የተካሄደዉ የመንግስታቲቱ ድርጅት የፀጥታዉ ምክር ቤት ልዑካን የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ሲያነጋግሩ ነዉ።

ፕሬዝደንት ጆሴፍ ካቢላን ካነጋገሩ በኋላ በመንግስታቱ ድርጅት የፈረንሳይ አምባሳደር ዣን ማርክ ዴ ላ ሳብሊረ እንደገለፁት ዝግጅቱ መስመር የያዘ ቢሆንም በዜግነት ጉዳይ የተነሳዉ ክርክር ችግር ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

ከምርጫዉ በፊት እየተካሄደ በሚገኘዉ የቅስቀሳ ዉይይት ማን ነዉ የኮንጎ ዜጋ የሚለዉ ክርክር አደጋ ይጋብዛል ባይ ናቸዉ ዲፕሎማቶቹ። ካቢላም ይህን ችግር ተገብዝበዋል ሲሉም ይገልጻሉ።

ለፕሬዝደንታዊዉ ምርጫ 33፤ ለምክር ቤት ደግሞ 10,000 እጩ ተወዳዳሪዎች የቀረቡ ሲሆን 26ሚሊዮን ህጋዊ መራጭም ተመዝግቧል። ለተወዳዳሪዎቹ የዜግነት ጥያቄዉ የችግር መስቀሻ ሆኗል።

ከትናንት በስተያ የኮንጎ የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊ ሞደስት ሙቲንጋ በየመገናኛ ብዙሃኑ የሚተላለፉት መልዕክቶች በሩዋንዳና በአይቮሪኮስት የተከሰተዉን ዓይነት ችግር እንዳያስከትሉ ስሉ አስጠንቅቀዋል።

ምንም እንኳን አገሪቱ በይፋ ሰላም ሰፍኖባታል ተብሎ ለምርጫ ዝግጅቱ ቢቀጥልም ወደ17,000 የሚገመተዉ የመንግሳቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል በሰፈረበት ምስራቃዊ የኮንጎ ግዛት የአማፅያን ዉጊያ ቀጥሏል።

ያም ማለት ምርጫዉ በሚሊዮን የሚቆጠሩት የአገሪቱ ዜጎች ለደህንነት በሚያሰጋ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ነዉ የሚካሄደዉ። የግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደሚሉት በየዕለቱ ጦርነቱ ባስከተለዉ ርሃብና በሽታ የ1,000 ሰዎች ህይወት ያልፋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የአዉሮፓዉ ህብረት የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሐምሌ ወር መገባደጃ በኮንጎ የሚካሄደዉ ምርጫ ምናልባት ሊያስከትል ይችላል የተባለዉን ግጭት ለማረጋጋት ያደራጁት የሰላም አስከባሪ ኃይሉን ለማነቃነቅ ተስማምተዋል።

ትናንት በበርሊን በኮንጎ ተልዕኮ ዙሪያ በተካሄደዉ ስብሰባ ላይም የጋናዉ ፕሬዝደንት ጆን ኩፎር ተልዕኮዉን በተመለከተ ሃሳብ ሰጥተዋል፣

«ተግባራዊ እንቅስቃሴዉ አሁን እየታየ ነዉ፤ በአግባቡ ተረድቸዉ ከሆነ እዚያ ባለዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃይል ላይ የአዉሮፓ ኃይል ይጨመራል። መርሳት የሌለብን ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ የራሷ የጦር ኃይል ያላት ሉዓላዊ አገር መሆኗን ነዉ። የመንግስታቱ ድርጅት ኃይል እዚያ አለ፤ የአዉሮፓ ህብረት ኃይል ደግሞ በኮንጎ ዲሞክራቲክ መንግስት ፈቃድ ወደዚያዉ ሊጓዝ ነዉ። ይህን ኃይል ከየሀገራቱ አሰባስባችኋል፤ የአዉሮፓን ወታደራዊ ኃይል ወደስፍራዉ የመላክ ዓላማዉም ተግባራዊ ይሆናል።»

ከተባበሩት መንግስታት ጋር በተደረሰዉ ስምምነት መሰረትም የአዉሮፓ ህብረት አስፈላጊ ከሆነ ብቻ በግዳጁ እንዲተባበሩ በኮንጎ ጎረቤት ሀገራት የሚቆዩ 450 የሚሆኑ ወታደሮችን ያዋጣል።

ወደኪንሻሳ ህብረቱ ከሚልካቸዉ 2,000 የሰላም አስከባሪ ኃይል መካከልም ጀርመን 780 ፈረንሳይ ደግሞ 800 ወታደሮችን ነዉ የሚልኩት።

ሌሎች 16 የአዉሮፓ ሀገራትም ቱርክን ጨምሮ በዚህ ይሳተፋሉ። ፖላንድና ስፓኝ እያንዳንዳቸዉ 100 ወታደሮችን፤ በተጨማሪም ስዊድን 50 እና ኔዘርላንድስ 40 ወታደሮችን እንደሚልኩ ዲፕሎማቶች ገልፀዋል።

የአዉሮፓ ህብረት ቀዳሚዉ ኃይል ኮንጎ መግባት የጀመረ ሲሆን ትናንት በተደረሰበት ዉሳኔ መሰረትም ምርጫዉ ከመካሄዱ 10ቀናት በፊትም ሁሉም ወታደሮች እዚያ ይገባሉ።


ተዛማጅ ዘገባዎች