የምርጫ ዘብ በቱርክ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 30.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የምርጫ ዘብ በቱርክ

የፊታችን እሁድ የፓርላማ ምርጫ ለማድረግ እየተዘጋጀች ባለችዉ ቱርክ ፤ሽብርተኝነት፤ ሙስናና የምርጫ ማጭበርበር ድባብ አጥሎባታል። በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎች የእሁዱ ምርጫ እንዳይጭበረበር በገዛ ፈቃደኝነት ጥበቃ ማድረግ ይፈልጋሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:10

የምርጫ ዘብ በቱርክ

የዶይቼ ቬለዎቹ ዩልያን ሃን እና ክርስትያን ሮማን ከኢስታንቡል ከምርጫዉ በፊት ያለዉን የቱርክ ሁኔታ ቃኝተዋል።
ኢስታንቡል ቱርክ ካዲኮይ በተሰኘዉ መንደር የሚገኘዉ ትልቅ አዳራሽ ለወትሮዉ በሰርገኞች ነበር የሚጣበበዉ። ዛሬ ግን ይህ አዳራሽ ዴሞክራሲን በሚሹ ወገኖች ተሞልቷል። የከፍተኛ ትምህርታቸዉን በዩኤስ አሜሪካ ያጠናቀቁት የአንድ ኩባንያ ባለቤት ሴርካን ሴሊቢ «ኦይ ቪ ኦትሲ» ማለትም «ምርጫና ሌሎችም»በተሰኘ ንቅናቄ ዉስጥ ሙሉ ተሳትፎ ከጀመሩ አንድ ወር ሆኗቸዋል። ሴሊቢ በአዳራሹ መድረክ የድምፅ ማጉያዉን ይዘዉ ወደ መድረክ ወጥተዉ ይህን አሉ።


« በተደጋጋሚ የምናወራዉ ምርጫ ተጭበርብሮአል፤ የድምፅ መሰብሰብያ ሙሉ ኮሮጆ የት እንደ ገባ ሳይታወቅ ጠፍቶአል፤ ነዉ። ስለዚህ አሁን የምንለዉ የምርጫዉን ዉጤት ከምንጠብቅ፤ የምርጫዉ እንዴት እየተካሄደ ነዉ በሚለዉ ላይ እናተኩር» ሴሊቢ በሚያራምዱት ንቅናቄ ዉስጥ ቢያንስ 70 ሺህ ያህል ዜጎች የፊታችን እሁድ ቱርክ በምታካሂደዉ የፓርላማ ምርጫ እንዳይጭበረበር የምርጫ ታዛቢ መሆንን ይፈልጋሉ። ይኸዉም ከኢስታንቡል እስከ ምዕራባዊ ኢዝሚር፤ ማላትያናን ጨምሮ እስከ ምስራቅ ዳያቢኪር በአጠቃላይ በሀገሪቱ ካሉት ከገሚስ በላይ በሚሆኑት የምርጫ ጣብያዎች ላይ በመገኘት ለመታዘብ አቅደዋል።


እንዲህ አይነቱ ተነሳሽነት የመታየቱ ምክንያት አገሪትዋን የሚያስተዳድረዉ የፕሬዚዳንት የሬሴፕ ተይፕ ኤርዶኻን «AKP» ፓርቲ ባለፈዉ ሐምሌ ወር ለመጀመርያ ጊዜ በአካባቢያዊ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ካጣ በኋላ በቱርክ ስጋትና አለመረጋጋት በማንዣበቡ ነዉ። የአሸባሪ ጥቃት ሊደርስ ይችላል የሚል ማስጠንቀቅያ፤ ጠብ አጫሪ የትግል እንቅስቃሴ በቱርክ የየዕለት ክስተት ሆንዋል። መንግሥት የሚተቹ ዘገባዎችን የሚያቀርቡ ጋዜጠኞች እና እንዲሁም ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ይገፋሉ፤ ማስፈራርያ ይደርሳቸዋል። ባሪስ ዞል የፊታችን እሁድ በሚደረገዉ ምርጫ «ካዲኮይ » የተሰኘዉን የምርጫ ጣብያ ለመታዘብ ዝግጅት ላይ ናቸዉ።


«በሀገሪቱ ዉስጥ በሚታየዉ ሁኔታ ደስተኛ አይደለሁም፤ ምርጫዉም ሙሉ በሙሉ በትክክል ይከናወናል የሚል እምነት የለኝም» በኢስታንቡሉ የኮስ ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ይፋ ባደረጉት ጥናት፤ በቱርክ የሚካሄደዉ ምርጫ ትክክለኛና ነፃ ነዉ ብሎ የሚያምነዉ ነዋሪ፤ ከሁለት አንዱ ነዉ። በጎርጎረሳዊ 2007 በተካሄደዉ ጥናት 70 በመቶ ነዋሪ የተደረገዉ ምርጫ ነፃና ትክክለኛ ነዉ ብሎ የሚያምን ነበር። ማኅበረሰቡ እምነቱ የተሰረቀዉ፤ ያለ ምክንያት አልነበረም። በጎርጎረሳዊ 2014 ከተካሄደ የአካባቢ ምርጫ በኋላ በድምፅ ቆጠራዉ ሰዓት በሀገሪቱ በርካታ አካባቢዎች መብራት መጥፋቱ

ይታወሳል። መንግስት ለመብራት መጥፋቱ ያቀረበዉ ምክንያት አንዲት ድመት በኤሌትሪክ ማሰራጫዉ ግዙፍ ባልቦላ ላይ ተንጠላጥላ ባደረሰችዉ ብልሽት ነዉ በማለት ነዉ የገለፀዉ። ከዚያ ጊዜ በኋላ በቱርክ የሚገኙ የመንግስት ተቃዋሚዎች «ድመት » የምትለዋ ቃል «ምርጫ ማጭበርበር» የሚለዉን ተክታላቸዋለች። በቱርክ ምርጫዉ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር የሚሰማዉም ትችት እየጠነከረ መጥቶአል። መንግሥትን የሚወግኑ የቱርክ ሚዲያዎች በፈቃደኝነት ምርጫዉን ለመታዘብ የሚንቀሳቀሰዉን «ኦይ ቪ ኦትሲ» ማለትም «ምርጫና ሌሎችም» የተሰኘዉን ቡድን፤ መንግሥት አሸባሪ ብሎ ከፈረጀዉ የኩርድ የሠራተኛ ፓርቲ ከ « PKK» ጋር ንክኪ አለዉ፤ ምርጫዉን ለመታዘብ ሳይሆን፤ ለማጭበርበር የሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ነዉ፤ ሲሉ ትችታቸዉን ያሰማሉ። በዚህም ምክንያት ይላሉ ስጋታቸዉን በመግለፅ ፤ባለኩባንያዉ ቱርካዊ ሴርካን ሴሊቢ፤ ንቅናቂያቸዉ አመኔታን እንዳያጣ።

«በየቀኑ ከእንቅልፌ ስነቃ የማየዉ የሆነ ሰዉ ስለኔ ፍፁም ትክክል ያልሆነ ነገር በድረ-ገጽ በትዊተር መልክትን ሲያሰራጭ ነዉ። ይህ ምናልባት የጀመርነዉን ንቅናቄ እምነት እንዳያሳጣ አስግቶኛል። »
እንድያም ሆኖ «ምርጫና ሌሎችም» የተሰኘዉ ቡድን አባላት የፊታችን እሁድ የሚደረገዉን ምርጫ በገዛ ፈቃደኝነት በታዛቢነት ከቀረቡ በኋላ፤ የምርጫ ድምፁን አብረዉ እንደሚቆጥሩ ነዉ የተመለከተዉ። ከዝያ በኋላ ይላ ሴሊቢ ከምርጫ በኋላ ማንም ስለምርጫ መጭበርበር ካላወራ የዝያን ጊዜ ሰላማችንን እናገኛለን።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic