የምርጫ ክርክር በኬንያ | አፍሪቃ | DW | 27.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የምርጫ ክርክር በኬንያ

የፊታችን ሰኞ ኬንያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ታካሂዳለች። ለዚህ ዝግጅትም በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዝደንታዊ እጩዎችን በምርጫ ክርክር ፊት ለፊት አሟግታለች። ከሁለት ሳምንታት በፊት የመጀመሪያዉ ዙር ሰኞ ምሽት ደግሞ የመጨረሻዉ እና ሁለተኛዉ ክርክር ተካሂዷል።

ኬንያ ዉስጥ በጎርጎሮሳዊዉ 2007ዓ,ም የተካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በአመፅ ታጅቦ ቢያንስ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት አሳጥቶ ተጠናቋል። የያኔዉ ግጭትና አመፅ ያሳሰባቸዉ ዜጎች ከአሁኑ ሰላም ጋባዥ መልዕክቶችን በየስፍራዉ መለጠፋቸዉን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘግቧል። «ቤቶቻችንን ልታቃጥሉ አይገባም» «ጎሰኞች መሆን አይኖርብንም» «ህዝቦች ሊተባበሩ ይገባል» እና የመሳሰሉትን መልዕክቶች በየመንደሩ ማየት እንደሚቻል ዘገባዉ ይጠቅሳል። ኬንያ ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀች ወዲህ ባለፈዉ የምርጫ ወቅት የገጠማት አይነት አመፅ ታይቶባት እንደማይታወቅም ተገልጿል።ለዚያን ጊዜዉ አመፅና ደም መፋሰስ ተጠያቂ ናቸዉ ሲል ዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ፍድር ቤት የከሰሳቸዉ ሰዎች በዚህ በዘንድሮዉ የኬንያ ምርጫ ይሳተፋሉ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዑሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞዉ የትምህርት ሚኒስትር ዊሊያም ሩቶ።

እነዚህ ተወዳዳሪዎች የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ጊዜም ከህዝቡ ተደጋግሞ የቀረበላቸዉ ጥያቄ ቢኖር ይኸዉ ነዉ፤ እንዴት በዓለም ዓቀፉ ችሎት ጉዳያችሁ እየታየ ለእጩነት ቀረባችሁ የሚል። ዘገባዎች እንደሚሉት ግን በዘንድሮዉ ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነዉ ከቀረቡት መካከል አንዱ ዑሁሩ ኬንያታ ናቸዉ ሌላኛዉ ጠቅላይ ሚኒትር ራይላ ኦዲንጋ። እጩዎቹ ክርክር ባካሄዱበት ወቅት በተለይ የመሬት ይዞታ ማሻሻያ ሃሳብ ብዙ እንዳነጋገረ ነዉ የተገለፀዉ። ባለፈዉ ምርጫ ጊዜም ሆነ ከዚያ በፊት የመሬት ጉዳይ ኬንያ ዉስጥ ለደም አፋሳሽ የጎሳ ግጭት ምክንያት መሆኑ ይነገራል። የሀገሪቱን የመሬት ሃብት በስፋት ከያዙት መካከል የኬንያታ ቤተሰብ ይጠቀሳል። የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት እስከ202 ሺህ ሄክታር ይገመታል። በፕሬዝደንታዊ ክርክሩ ወቅት ዑሁሩ ኬንያታን አጣብቂኝ ዉስጥ የከተተ ሌላ ጉዳይ ሆኖም ተነስቷል።

እሳቸዉ ግን ቤተሰባቸዉ የያዘዉ መሬት በህጋዊ መንገድ ስለመገኘቱ በመሞገት መጠኑንም ለማሳነስ ሞክረዋል። የመሬት ይዞታ ጉዳይ እጅግ አነጋጋሪ እንደሆነ በሚነገርባት የኬንያ የዉሃ ድንበር ግዛት ሞምባሳ ፕሬዝደንታዊ የምርጫ ክርክሩን ከተከታተሉ ወገኖች አንዱ እንዲህ ይላሉ፤

«በክርክሩ ዋነኛ ጉዳይ ከነበሩት መካከል በኬንያያታ ቤተሰቦች የተያዘዉን መሬት ይመለከታል። ዑሁሩ ኬንያታ በቤተሰቦቻቸዉ የተያዘዉን መሬት መጠን በቀጥታ ለመግለጽ አልቻሉም። እሳቸዉ የጠቀሱት ታይታ ታቬታ የሚገኘዉን መሬታቸዉን ብቻ ነዉ። ነገር ግን ሁላችንም እጅግ ሰፊ መሬት እንዳላቸዉ እናዉቃለን። ሌላዉ መሬቶቻቸዉን ሁሉ በፈቃደኝነት የመሸጥና የመግዛት ሂደት እንደያዙ ተናግረዋል ያ ሀሰት ነዉ። አባታቸዉ ፕሬዝደንት ነበሩ፤ እናም መሬቱን ለመግዛት ያን ያህል ባለፀጋ አልነበሩም፤ የተቃረመቱት መሬት ነዉ።»     

በእጩ ፕሬዝደንትነት ኬንያ ዉስጥ የቀረቡት ስምንት ሰዎች፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ፤ ምክትላቸዉ ዑሁሩ ኬንያታ፤ ፒተር ኬኔዝ፤ ማርታ ካሩዋ፤ ጄምስ ኦሌ ኪያፒ፤ ፓዉል ሙቲ፤ ሙሳሊያ ሙዳያዲ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ መምህር የሆኑት ሞሐመድ አብዱባ ዲዳ ናቸዉ።

የምርጫ ክርክሩን የተከታተሉት ፍራንሲስ ዑማ ክርክሩ የተፎካካሪዎቹን ማንነት አጋልጦ በማዉጣቱ እንደ እሳቸዉ እምነት ሀገሪቱን ለመምራት ብቁ እንደሌለ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል። 

«የትናንቱ ክርክር የኬንያን ያልተሳካ ፖለቲካና ፖለቲከኞች አጋልጧል። አንዱ ስላለዉ መሬት ተጠይቆ ነበር፤ ግን በቀጥታ ሊመልስ አልቻለም ዙሪያ ጥምጥም ሲዞር አስተዉለናል። ፖለቲከኞቻችን ዉሸታሞችና ሙሰኞች መሆናቸዉ ግልፅ ነዉ። አንዱ ሌላኛዉን ያጠቃ ነበር እናም አንዳቸዉም ይህችን ሀገር የመምራት ብቃት እንደሌላቸዉ የታወቀ ነዉ።»

የሞምባሳ አካባቢ ኗሪ የሆኑት ሌላዋ የክርክሩ ታዛቢ ሙፓ ካህሊፋም ከእሳቸዉ ያልተለየ ሃሳብ ነዉ ያላቸዉ።

«በክርክሩ ላይ ከተነሱት ዋነኛዉ ጉዳይ የመሬት ባለቤትነት ነዉ። በእኔ አመለካከት በአግባቡ የተስተናገደ ጉዳይ ነዉ፤ መሪዎቻችን ዙሪያ ዙሪያዉን

እየተሽከረከሩ ተካሰሱ እንጂ። ይህም መንግስታችን በአንድነት እንዳልቆመ ማረጋገጫ ነዉ፤ እናም ኃላፊነት የጎደለዉና የአመራር ብቃት ማነስን መኖሩን ያመላክታል።»

ከወዲሁ የተካሄዱ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረቡት ሴቷ እጩ ተወዳዳሪ የሚያገኙት ድምፅ እጅግ አናሳ እንደሆነ አመላክቷል ቢባልም ማርታ ካሩዋ ግን አልተቀበሉትም። ራይላ ኦዲንጋና ዑሁሩ ኬንያታ በአስተያየት መመዘኛዉ መሠረት ግንባር ቀደሙን መስመር ይዘዋል። እንደታሰበዉ ከሄደም የፊታችን ሰኞ ኬንያ ሀገራዊ ምርጫዋን ታካሂዳለች። በዚህ ምርጫም ኬንያዉያን ፕሬዝደንታቸዉን ብቻ ሳይሆን፤ አገረ ገዢዎች፤ ሴናተሮች፤ የየአካባቢ ተወካዮችና የምክር ቤት አባላትን ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic