የምርምር ይዞታ በጀርመን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 10.03.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የምርምር ይዞታ በጀርመን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣

በፖለቲካው መስክ፤ ሴቶች፤ የአኩልነት መብታቸውን ለማስከበር ተደራጅተው የተንቀሳቀሱበት 100ኛ ዓመት፣ ትናንት ነው ታስቦ የዋለው። በሳይንስና ሥነ-ቴክኒኩ ዓለምም ፤ ሴቶች ያበረከቱት ድርሻ በ 100 ታሪክ አብሮ ሊዳሰስ የሚችል ነው።

default

ተማሪዎች፣ በአኸኑ የሥነ ቴክኒክ ዩኒቨርስቲ፣ የጥናት ውጤታቸውን ሲያቀርቡ፣

ለምሳሌ ያህል ፣ የፖላንድ የታሪክ ቤተ-መዘክር ፤ በኢንተርኔት ባካሄደው መጠይቅ በተሳታፊዎችዘንድ የፖላንዷ ተወላጅ፣ ማሪ ኩሪ እስክሎዶቭስካ፤ በአገሪቱ ታሪክ «እጅግ ታላቋ ፖላንዳዊት» መሰኘቷን አስታውቋል። የዘመናዊው ፊዚክስ እናት የምትባለው ማሪ ኩሪ እስክሎዶቭስካ፣ እ ጎ አ በ 1867 ዓ ም፣ በፖላንድ መዲና በወርሶ የተወለደች ሲሆን፤ በፊዚክስና ሂሳብ ትምህርቷን ለመቀጠል በ 1891 ወደ ፓሪስ ፣ፈረንሳይ ተጓዘች። በዚያም ነበረ፣ በ 1895 ፒዬር ኩሪ የተባለውን ፈረንሳዊ ያገባች። ማሪ ኩሪ የፖሎኒዬም እና ሬዲየም ንጥሮችን በመነጠል፣ በተለይ ሬዲዬም ፣ ለህክምና አገልግሎት እንዲውል ያደረገች ሳይንቲስት ናት። በአቶም ጨረር(ራዲየሽን) ባደረገችው ምርምርም እ ጎ አ

በ1903 በፊዚክስ የኖበል ሽልማት ከተቀበለች በኋላ፣ በሥነ ቅመማ 2ኛ የኖቤል ሽልማት አገኘች። በመሆኑም ይኸው መቶኛ ዓመት ፣ በዓለም አቀፍ የሥነቅመማ መታሰቢያ ዘመን በተሰኘው ዓመት (ዘንድሮ) እንዲታሰብ የፖላንድ ህግ-መወሰኛ ም/ቤት ደንግጓል። በመሆኑም በፖላንድና በፈረናሳይ የተለያዩ የጥናት ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ታቅዷል።

በዘንድሮው የሥነ-ቅመማ መታሰቢያ ዘመን፤ ከፍተኛ ትምህርትና ምርምር፤ ጀርመን ውስጥ በሰፊው በማነጋገር ላይ ነው ፤ ለአንዴትነቱ በቀጣዩ ርእሰ ጉዳይ እንመለከታለን።

ለኤኮኖሚ ዕድገታቸው በሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ምርምር እጅግ ከሚመኩትና ተጠቃሚዎችም ከሆኑት ግንባር ቀደም ሀገራት መካከል አንዷ ጀርመን መሆኗ እሙን ነው። ጀርመን ፣ ለሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ለሌሎችም የትምህርት ዘርፎች ትልቅ ትርጉም የምትሰጥ ሀገር ሆና ሳለ፣ የመከላከያ ሚንስትር የነበሩት ካርል ቴዎዶር ትሱ ጉተንበርግ ፤ የዶክትርነት ማዕረግ ያገኙበት ሳይንሳዊ መርኅን ያልተከተለ ፤ የመመረቂያ ጽሑፋቸው በአመዛኙ የሌላ ሰው ሥራ ቅጂ ሆኖ መገኘቱ በምርመራ ተደርሶበት ፣ በቅርቡ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው የሚታወስ ነው። የእኒህን የቀድሞ ባለሥልጣን ፣ ሥልጣን መልቀቅ ተክትሎ፣ ጉዳዩ ፤ በተለይም የትምህርትን አያያዝና የፕሮፌሰሮችን አሠራር በተመለከተ ማወያየቱ አልቀረም። በሌላ በኩል ፤ ማንም ሰው ፣ ትምህርት በትጋት በመከታታል፣ ችሎታን በማስመሥከር ፤መደበኛ ፈተናንም በማለፍ እንጂ፣ የመኳንንት ልጅ ስለሆነ ፤ በቸልታ ሊታለፍ እንደማይችል ነው፤ ህጉ ያረጋገጠው።

የመማርና የመመራመር ነጻነት በጀርመን ህገ-መንግሥት የሠፈረ ጠቃሚ ጉዳይ ነው። አንድ ፕሮፌሰር፣ በሚያደርገው ምርምር ፣ ምን መከተል፤ ምን መተው እንዳለበት፣ ለተማሪዎቹ የሚያቀርበው ትምህርትም ምን መምሰል እንዳለበት ማንም ማዘዝ አይኖርበትም። ግን አንድ ፕሮፌሰር፤ ከክፍለሀገራዊ አስተዳደር መሆኑ ቀርቶ ደመወዙን ከአንድ ኩባንያ የሚያገኝ ከሆነስ ? ብዙዎች የኢንዱስትሪ ኩባንያዎች፤ ፕሮፌሰሮችን የሚደግፉበት የበጎ አድራጎት ድርጅት አላቸው። እንዲህ ዓይነቱ የበጎ አድራጎት ድርጅት እንዲበረታታ ፈቃድ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው እ ጎ አ በ 1985 ዓ ም ነው።

ሐሳቡ ወይም የዚህ አካሄድ ዓላማ፤ ኩባንያዎች፤ በዩኒቨርስቲዎችና በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንድን ፕሮፌሰርና ተባባሪ ሠራተኞቹን ቢያንስ ለ 5 ዓመታት እንዲደግፉ ነበር። የፊዚክስ ምሁር ካርስተን ቡዘ፣ በቦን ዩኒቨርስቲ፤ የጀርመን «ቴሌኮም»በሚደግፈው የ Heinrich-Hertz በጎ አድራጎት ተቀጥረው ቦታውን የያዙ ናቸው።

(1)«በጎ አድራጊው፣ በአመዛኙ አንድ ኢንዱስትሪ ሲሆን፤ እርሱም ያላንዳች ጥርጣሬ የሚፈልገው ጥቅም ይኖራል፤ አዲስ የፈጠራ ውጤት እንዲገኝ ይሻል። በተለይ ዩኒቨርስቲውን የፈጠራ ውጤት ባለቤት ለማድረግ የሚያበቃና በከፊልም የዚህን የፈጠራ ውጤት ባለቤትነት መብት ገንዘብ ለጋሺው በከፊል ማግኘት ዓላማው ነው። »

በበጎ አድራጎት የሚደጎሙት ፕሮፌሰር፣ ዩንቨርስቲ ውስጥ፣ የዩንቨርስቲ ተማሪዎችንና በዶክተርነት ለመመረቅ የሚዘጋጁትን፣ ማስተማር ማማከር ብቻ ሳይሆን፤ ለ ደጓሚው ኩባንያ ተስማሚ አዲስ የፈጠራ ውጤት መታወቂያ ደንብም ያዘጋጃሉ። እናም ካርስተን ቡዘ፤ እንደሚሉት ፣ በትብብሩ ፣ ሁለቱም ወገኖች ናቸው የሚጠቀሙት። በጀርመን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ ከ 650 በላይ ፕሮፌሰሮች፤ በኢንዱስትሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጎማ ተቀባዮች ናቸው። ከ650 ገደማው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በኤኮኖሚና በምህንድስናው ሳይንስ የተሰለፉ ናቸው። በሥነ ልቡና ፤ መንፈሳዊም ሆነ በማኅበራዊ ጉዳዮች ሳይንስ ረገድ ከኢንዱስትሪዎች ከሞላ ጎደል ድጋፍ አይገኝም ማለት ይቻላል።

ታዲያ፤ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች ምርምር ማካሄድ የሚኖርባቸው ፤ ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመዋዋል ሳይሆን ፤ ነጻ ሆነው አርእስትም ራሳቸው በመምረጥ፤ ሳይንሳዊ መርኆዎችን ተከትለው መሆን አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ። የዴሞክራሲያዊ ሳይንቲስቶች ፌደሬሽን የተሰኘው ማኅበር ባልደረባ ቶርስተን ቡልትማን ግን ይህ አባባል አይጥማቸውም።

(2)«በሳይንሳዊ ዘዴ በመሥራት ረገድ፣ እነዚሁ ፕሮፌሰሮች፣ እያንዳንዳቸው፣ ነጻ ሆነው መሥራት ፣ በተወሰነ ደረጃም ነጻ ሳይንሳዊ ምርምር ለማካሄድ ፣ ራሳቸውን ማዘጋጀት ማስተማር ይችላሉ። ነገር ግን፤ ጠቃሚውና ወሳኙ ጉዳይ፤ በአእምሮ ውስጥ ያለው መቀስ ነው። ምክንያቱም ፣ አጠቃላዩ ፍለጋ፤ የአሠራር ዘዴውና የርእስ አመራረጡ፤ በሚመለከተው ፕሮፌሰር የሚወሰኑ ናቸውና!»።

Wissenschaftlerin Marie Curie

ሳይንቲስቷ ማሪ ኩሪ

በኢንዱስትሪ በጎ አድራጎት የሚደጎሙት ካርስተን ቡዘ ግን ይህ አባባል ትክክል አይደለም ባይ ናቸው። ለምርምር ሲባል፣ ከግለሰብም ሆነ ከአንዱስትሪ ፣ የገንዘብ ድጎማ ቢገኝ፣ የሚሳስብ አይደለም ነው የሚሉት።

(3)«እዚህ ቦን ውስጥ ስላለው ሁኔታ መናገር ይቻላል፤ በተለይ እኔ ወደአዚህ ከመጣሁበት ጊዜ አንስቶ፣ ሰፊ ግልጽነትና መቻቻል ይንጸባረቃሉ። ምናልባት አንድ ሰው ተነስቶ አዎ ይህ ነፍስን መሸጥ ማለት ነው ምክንያቱም፤ ዩኒቨርስቲው ከኢንዱስትሪ ኩባንያ ጋር ተባብሮ ይሠራል ፣ የሚል ትችት መሠንዘሩ ፣ ሌላውን ዝቅ አድርጎ ሊመለከት ይችል ይሆናል የሚለው ሥጋት እንደ ማለፊያ ዕድል ሆኖ እስካሁን በፍጹም አላጋጠመም። ትብብሩ ደግሞ፤ ሁሉም የሚያተርፍበት መንገድ ነው። ለሁለቱም ወገን ጠቀሜታ አለው።»

እርግጥ ነው፣ ሁሉም የዩንቨርስቲው ማኅበረሰብ አይደለም ከኤኮኖሚ ነክ ኢንዱስትሪዎች ጋር የሚደረገውን ትብብር የሚደግፍ። ውጤቱ አዎንታዊነት አይኖረውም በማለት!የኮሎኝ ዩኒቨርስቲ፣ ከታወቀው የመድኃኒት ፋብሪካ ፤ ቫየር አክሲዮን ማኅበር ጋር ተባብሮ ይሠራል። የዩንቨርስቲው ተማሪዎች ማኅበር ተወካይ ፓትሪክ ሽኔፐር፣ ትብብሩ፣ ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳል ባይ ነው።

4,«እኛ በቀጥታ ማወቅ የምንፈልገው፤ ባየር እዚህ ዩንቨርስቲ ውስጥ ምን ያደረጋል? ዩንቨርስቲውስ ለባየር ምን ያደርግለታል? ምንድ ነው የሚካሄደው? ይህ በፍጹም ከሳይንስ ነጻነት ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም። ስለሆነም ግልጽ አሠራር ሊኖር ይገባል። ምን ዓይነት አቋም መያዝ እንደሚኖርብን ፣ የተቸገርንበት ሁኔታ ስላለ አለ፣ ምን መደረግ እንደሚገባን አናውቅም።»

በመሠረቱ፤ መምህራኑና ኢንዱስትሪዎቹ ፣ እንዲሁም ተማሪዎቹ አንድ ግልጽ ሆኖ የሚታያቸው ጉዳይ አለ ይባላል። እርሱም፤ የመንግሥት በጀት እየቀነሰ በሚሄድበት በአሁኑ ወቅት ፤ ፕሮፌሰሮች፣ በኢንዱስትሪዎች መደጎማቸው በጎ ነገር ሊባል የሚችል ነው። አንድ ዩኒቨርስቲ ፣ ለ 5 ዓመት ለአንድ የኮምፒዩተር ሳይንስ ፕሮፌሰር የሚከፍለውን በአማካዩ 1,5 ሚልዮን ዩውሮ ያተርፋል ማለት ነው።

ይህ በአንዲህ እንዳለ፣ የጀርመን የምርምርና የፈጠራ ሥራ የጠበብት ኮሚሽን ፤ ለወደፊቱ ምርምር የግል ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ያደርግ ዘንድ መንግሥትን አሳሰበ።

የዚሁ ኮሚሽን ሊቀመንበር ፕሮፌሰር፣ ዲትማር ሃርሆፍ እንዲያውም በጀርመን የምርምር ተግባር ብዙ ሳንኮች አሉበት በማለት እ ጎ አ ከ 1989 ዓ ም ወዲህ የተከናወኑትን ከቀሪዎቹ የአውሮፓው ኅብረት አባል ሃገራት ጋር በማነጻጸር አብራርተዋል። የአውሮፓው ኅብረት አባል አገሮች፣ ካልተጣራ ብሔራዊ ገቢአቸው 3 ከመቶውን ለምርምር ለማዋል መስማማታቸውን የገለጡት ሃርሆፍ፣ ጀርመን ይህን ደንብ አላከበረችም ፣ በቤኔሉክስ አገሮች(ቤልጅግ፣ ሉክሰምበርግና ኔደርላንድ)ግን የተከበረ ነው ብለዋል።

በድሬሰደን የሥነ-ቴክኒክ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ፣ የባዮ-ፊዚክስ ምሁር፣ ፔትራ ሽቪሊ አዲስ የምርምር ይዞ መንቀሳቀሱን የሚፈሩ አሉ። አዳዲስ ሐሳብ ፣ ለዚህ ተስማሚ የሆኑ ድፍረት ያላቸው ሰዎች ያስፈልጉናል። በዩናይትድ እስቴትስ የማይቻል ነገር የሚመስለውን መሞከር የሚቻልበትን ምርምር ለማካሄድ ፍርሃት የለም ሲሉ ተናግረዋል።

ይም ሆነ ይህ፣ ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር የተቀየሰውን Hightec-Strategy 202o እ ጎ አ እስከ 2020 የተነደፈው የከፍተኛ ሥነ-ቴክኒክዊ ስልት ብሩኅ ተስፋን የሚያስጨብጥ መሆኑን የምርመር ጠበብቱ ኮሚሽን ገልጾአል። ጀርመን፤ በአየር ንብረት ጥበቃ፤ በኃይል ምንጭ፤ በጤና፤ በሰብል፣ በፀጥታ ፤ በመገናኛና በማጓጓዣ ሥነ-ትክኒክ ጥንካሬ ያላት አገር ናት። ስለሆነም የምርምር ውጤቷ ለውጭ ገበያም እንዲስማማ ማድረግ ያለባት መሆኑን ነው ጠበብቱ አያይዘው የገለጡት።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ