የምሥራቅ ወለጋ አባገዳ የሰላም ጥሪ
ማክሰኞ፣ ጥር 27 2017የምሥራቅ ወለጋ ዞን የአባዳዎች ሕብረት ሰብሳቢ አባገዳ ደሳለኝ ፈይሳ ውስብስብ እየሆነ የመጣውን የሰላም እጦት ችግር ለመፍታት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሸማቂዎችና መንግሥት የሕዝቡን የሰላም ጥያቄ በመቀበል ወደ እርቅ መምጣት እንደለባቸው አመልክተዋል።ከዚህ ቀደም ተጀመሩ የተባሉ ድርድሮችም በተለያዩ ቦታዎች የተሟላ ሰላም ባለመኖሩ ለተፈጠሩ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ያመጣል ተብሎ እምነት ተጥሎበት እንደነበር በማንሳት አሁንም ለሕዝቡ ሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሁለቱም አካላት ድርድር በመቀመጥ ይሄን ችግር መፍታት አለባቸው ብለዋል።
«ሰላም ሁሉንም የሚቀድም ነው። ሰላም ከሌለ ግን ቤተሰብ ማስተዳደርም ማየትም አይቻልም። ለዚህ ነው ሰላም እንዲወርድ ትልቅ ጥረት ሲናደርግ የነበረው። ሰላም አለ የምንለው ሰው በሰላም ካደረ፣ አንድ ከሆነ፣ ተባብሮ ካመረተ፣ ከተማረና ውሎ ከገባ ነው። በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ ከአንዱ ቀዬ ወደ ሌላው እየሄደ አይደለም። ስለዚህ አሁንም ቢሆን እየተጋጩ ያሉ ኃይሎች ሰላም ማውረድ አለባቸው። ሕዝቡ የሚፈልገው በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ልጆች ደግሞ መማርን ነው። ጫካ ያለውም መንግሥትም ሕዝቡ ያለውን መቀበል አለባቸው።»›
በወለጋ ውስጥ በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ የምርት መጠን ቀንሷል
ግጭት በስፋት በሚስተዋልበት ወለጋ ውስጥ አርሶ አደሩበተለያዩ ስፍራዎች በሚደርሱበት ጥቃቶች ሳቢያ ማሳውን ማረስ እንዳልቻለም አባገዳ ደሳለኝ ፈይሳ አብራርተዋል። ብዙ ምርት የሚገኝባቸው የምሥራቅ ወለጋ አካባቢዎች እንደ ጊዳ አያና፣ ጉትን፣ ኪረሙና ሌሎች ቦታዎች የግብርና ምርት መጠን መቀነሱንና የምርት ዋጋ መጨመሩን ተናግረዋል።
«ኑሮ ውድነትን በተመለከተ ያልጨመረ ነገር የለም። ባለሀብት ተፈናቃይ ሆኖ ጥበቃ ያለው ቦታ ከተማ ውስጥ ቤት ተከራይቶ እየኖረ ነው። ዛሬ የፋብሪካ ምርት የሆነው ዘይት አንድ ሊትር በ300 ብር እየገዛን ነው። ኑሮ ውድነት በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ ሰላም ወርዶ ይሄ ግጭት ቆሞ ሁሉም ወደ የሥራው መመለስ አለበት።»
በግጭት የሚወድመውን ንብረትና እየጠፋ ያለውን የሰው ሕይወት ለማዳንም አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ነዋሪ የነበሩና በአሁኑ ወቅት በነቀምት ከተማ ውስጥ የሚኖሩ አንድ ነዋሪ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት በአካባቢአቸው የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር አርሶ አደሩ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ በመቆየቱ በተለይም አካባቢው የሚታወቅበት በቆሎ ምርት መቀነሱን ጠቁመዋል። ነዋሪው አክለውም ለዓመታት የቆየው ግጭት ዘርፈ ብዙ ችግር ማስከተሉን በመግለጽ ችግሩን ለመፍታት አሁንም ድርድሩ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
በምሥራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ የምርት ዋጋ መጨመሩን አስመልክቶ ለቀረበው ሀሳብ ከዞኑ ንግድ ቢሮ መረጃ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ግጭት ለማስቆም መንግሥትና የኦሮሞ ነጸነት ሠራዊት አመራሮች በሁለት ዙር ታንዛኒያ ላይ ያደረጉት ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ሁለቱም ኃይሎች ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ እንደሆኑ በየፊናቸው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ