የምሥራቅ ኮንጎ ውጊያ ማብቃት | አፍሪቃ | DW | 06.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የምሥራቅ ኮንጎ ውጊያ ማብቃት

የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ መንግሥት እና አማፅያኑ «ኤም 23» ቡድን በምሥራቃዊ የሀገሪቱ አካባቢ የሚያካሂዱትን ውጊያ ለማብቃት በካምፓላ ዩጋንዳ ከብዙ ወራት ወዲህ የጀመሩት ድርድር ካለውጤት በተበተነበት ባሁኑ ጊዜ የኮንጎ ጦር በአማፅያኑ ላይ ሙሉ ድል ተቀዳጅቶዋል።

ጦሩ « ኤም 23 » በሰሜን ኪቩ ግዛት ይዟቸው የነበሩትን የመጨረሻ ሰፈሮች ባለፈው ሰኞ ሌሊት መልሶ ተቆጣጥሮዋል። ይህን ተከተሎም አማፅያኑ መሸነፋቸውን እና 18 ወራት የዘለቀውን ውጊያ ማብቃታቸውን በማረጋገጥ፣ የጦር መሣሪያ ትጥቃቸውን ለመፍታት እና ለውዝግቡም የፖለቲካ መፍትሔ ለማፈላለግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከኮንጎ ጦር ያመፁ የቱትሲ ጎሣ አባላት ያቋቋሙት እና በምሥራቃዊ ኮንጎ የሚንቀሳቀሰው «ኤም 23» የተባለው ቡድን እርግጥ በወቅቱ እጅግ ተዳክሞዋል።

ይሁንና፣ ቡድኑ አንድ ሚልዮን ሕዝብ የሚኖርባትን የምሥራቅ ኮንጎ ከተማ፣ ጎማን እአአ ኅዳር፣ 2012 ዓም ለአጭር ጊዜ ተቆጣጥሮ እንደነበር ይታወሳል። የኮንጎ ጦር በሀገሩ ከተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ፣ ሞንዩስኮ ድጋፍ በማግኘት ከጥቂት ሳምንታት በፊት በ « ኤም 23 » ላይ ባካሄደው ጠንካራ የጥቃት ዘመቻ ሩንዮኒን እና ቻንዙን ከዓማፅያኑ ማስለቀቅ መቻሉን የጦሩ ቃል አቀባይ ኦሊቭየ ሀሙሊ አስታውቀው፣ ጦሩ ባካባቢው በሚንቀሳቀሱ ሌሎች ቡድኖች ዘመቻውን እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
« ቀጣዩ ርምጃ ማይ ማይንን እና የ« ኤፍ ዲ ኤል አር »ን የመሳሰሉ የኮንጎ እና ሌሎች የውጭ ሀገር ታጣቂ ቡድኖችን ትጥቅ ማስፈታት ይሆናል። ቡድኖቹ ትጥቃቸውን መፍታት ካልፈለጉ ልክ በ « ኤም 23 » ላይ ባካሄድነው ዓይነት ዘመቻ እናስፈታቸዋለን። »
ባለፉት ጊዚያት የተመድ በተደጋጋሚ ከርዋንዳ የጦር እና የገንዘብ ርዳታ ያገኛል ያለው «ኤም 23» እአአ ለ1994 ዓም የርዋንዳ ጎሳ ጭፍጨፋ ተጠያቂ የሆኑት ሁሉ ሚሊሺያዎች ካቋቋሙት የርዋንዳ ነፃነት ዴሞክራሲያዊ ኃይላት፣ የ« ኤፍ ዲ ኤል አር » ሁቱ ዓማፅያንም ጋ ውጊያ ሲያካሂድ ቆይቷል። የኮንጎ መንግሥት አሁን በ« ኤፍ ዲ ኤል አር » አንፃር ርምጃ ለመውሰድ መወሰኑን የ «ኤም 23» ዓማፅያን እንደ ጥሩ ክስተት ሊመለከቱት ይችላሉ።
የኮንጎ ጦር አሁን ወታደራዊ ድል ማስመዝገቡ እና « ኤም 23 »ም ሽንፈቱን አምኖ መቀበሉ ብቻውን ግን አካባቢውን ማረጋጋቱን ብዙዎች ተጠራጥረውታል። ምንም እንኳን ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች 18 ወራት የዘለቀው ውጊያ እንዲያበቃ ካለፉት አንድ ዓመት ገደማ ወዲህ በካምፓላ ዩጋንዳ ቢደራደሩ እና እስካሁንም ይህ ነው የሚባል አሰተማማኝ የፖለቲካ መፍትሔ ላይ ባይደርሱም፣ በዚህ ሳምንት መጨረሻ አንድ የሰላም ውል ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል። እርግጥ፣ በድርድሩ ወቅት የኮንጎ መንግሥት ለ «ኤም 23 » ከገባው ቃል መካከል ለዓማፅያኑ ምሕረት ማድረግ የተሰኘው ይገኝበታል። መንግሥት የገባውን ቃል ካላከበረ በምሥራቃዊ ኮንጎ ዘላቂ ሰላም እንደማይወርድ ዩጋንዳዊው የምጣኔ ሀብት ምሁር እና ጋዜጠኛ አሊ ሙታሳ አስጠንቅቀዋል።

« እንደ « ኤም 23 » ተደራዳሪዎች ዘላቂ ሰላም የሚወርደው በካምፓላው ውይይት ላይ የተደረሱት ስምምምነቶች ሙሉ በሙሉ በተግባር ከተተረጎሙ ብቻ ነው። እና መንግሥት ስምምነቶቹን በተግባር ላለመተርጎም ከወሰነ፣ ይህ ለ«ኤም 23» ዓማፅያን የጦር መሣሪያቸውን እንደገና ለማንሳት እና ውጊያውን ለመቀጠል ምክንያት ይፈጥርላቸዋል።»
እንደ አሊ ሙታሳ ግምት፣ የኮንጎ መንግሥት ጦሩ አሁን ባስመዘገበው ወታደራዊ ርምጃ በመተማመን ስምምነቶቹን ሊያፈርስ ይችላል። የኮንጎ መንግሥት ወደ ካምፓላው ድርድር ጠረጴዛ እንደሚመለስ፣ ግን የድርድሩ አቅጣጫ እንደሚቀየር የመንግሥቱ ቃል አቀባይ ላምቤር ሜንዴ ትናንት ምሽት የሰጡት መግለጫ፣ የሁኔታውን አደገኛነት የሚጠቁም ነው፣ ምንም እንኳን ውጊያው አሁን ቢያበቃም።
በኮንጎ የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ተልዕኮ፣ የሞንዩስኮ መሪ ማርቲን ኮብለር ባካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች በጠቅላላ፣ «ኤፍ ዲ ኤል አር» ጭምር፣ ገና አስተማማኝ ያልሆነውን የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት በማድረግ ወደ ኃይሉ ተግባር እንዳይገቡ ጥሪ አቅርበዋል። ይህን ካደረጉ ግን ሞኑስኮ በአንፃራቸው ርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።


የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት ባልደረባ ወይዘሮ ሉሲ ቤክ እንዳመለከቱት፣ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር የምሥራቅ ኮንጎ ሕዝብ በ«ኤም 23» እና በመንግሥቱ ጦር መካከል ባለፉት በርካታ ወራት በቀጠለው ከባድ ውጊያ አካባቢውን እየለቀቀ ሸሽቶዋል። ውጊያው እአአ በ2012 ዓም የመፀው ወራት ከተጀመረ ወዲህ 800,000 ሰው ሲሸሽ፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውጊያ ብቻ 19,000 ወደ ጎረቤት ዩጋንዳ ተሰዶዋል።
«ብዙ ሰዎች ከባድ የቦምብ ድብደባ መካሄዱን ገልጸውልናል፣ እኛም የቆሰሉ ሰዎች አይተናል። ብዙዎችም የሞቱ ሰዎች እንዳዩ፣ አንዳንድ የሚያውቋቸው ሰዎች አስከሬን መመልከታቸውን ነግረውናል። አንድ ያነጋገርኩት ሰውየ ድንበር ተሻግረው ሲሸሱ የተገደሉ አምስት ወይም ስድስት የሚያውቃቸው ሰዎች ማየቱን ገልጾልኛል።»
ስደተኞቹ አሁን ከ «ኤም 23 » ድል መሆን በኋላ እፎይ ማለት መቻል አለመቻላቸው የኮንጎ መንግስት እና «ኤም 23 » ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሔ በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ጥገኛ ይሆናል።

ፊሊፕ ዛንድነር/አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic