የምሥራቅ ኮንጎ አማጽያን ግሥጋሤ | አፍሪቃ | DW | 21.11.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የምሥራቅ ኮንጎ አማጽያን ግሥጋሤ

ጎማ ውስጥ በሺ የሚቆጠሩ የመንግሥት ወታደሮችና የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች እንደሚገኙ የታወቀ ሲሆን ፤ የጎማ መያዝ በፕሬዚዳንት ጆሰፍ ካቢላ ለሚመራው የኪንሻሳ አስተዳደር እንደ አንድ ድቀት ነው የሚታየው።ጎማ ከተያዘች በኋላ በአገሪቱ በመላ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል ።

M 23 በሚል መጠሪያ የታውቁት የምሥራቅ ኮንጎ አማጽያን፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኑዋሪዎች ያሏትን የክፍለ ሀገሩን ርእሰ ከተማ ጎማን በቁጥጥራቸው ሥር አውለዋል። ለወራት ያህል ይህን እንደሚያደርጉ የዛቱት አማጽያን፤ በ 4 ቀናት የተፋፋመ ውጊያ ነው ከተማይቱን ለመያዝ የቻሉት። ጎማ ውስጥ በሺ የሚቆጠሩ የመንግሥት ወታደሮችና የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች እንደሚገኙ የታወቀ ሲሆን ፤ የጎማ መያዝ በፕሬዚዳንት ጆሰፍ ካቢላ ለሚመራው የኪንሻሳ አስተዳደር እንደ አንድ ድቀት ነው የሚታየው። ጎማ ከተያዘች በኋላ በአገሪቱ በመላ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል ። ስለአማጽያኑ ግሥጋሴና የጎማ ይዞታ የዶቸ ቨለ የአፍሪቃው ክፍል ባልደረባ ዚሞነ ሽሊንድቫይን ያቀረበችውን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አቀናብሮታል።

የዩጋንዳ፣ ኮንጎና ሩዋንዳ መሪዎች ፤ የምሥራዊቷን ኮንጎ ርእሰ-ከተማ ጎማን፣ በአማጽያን መያዝ አስመልክተው ካምፓላ ውስጥ መክረዋል። ውዝግቡ ይበልጥ እንዳይስፋፋ ሥጋት አለ። በጎማ መዳረሻ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በሚገኙበት ማዕከል የኑዋሪዎች አሳዛኝ ጉስቁልና እንደሚታይ ተመልክቷል። 500 ያህል እናቶች በዛ ያሉ ጨቅላዎች፤ በአሸዋ በተሞሉ

ዶንያዎች በታጠረ ሥፍራ ተኮልኩለው ይገኛሉ። በተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች ሠፈር የደኅንነት ዋስትና ይኖራል ብለው በማሰብ ከባልተቤታቸውና 6 ልጆቻቸው ጋር የተጠለሉት Antoine Bwenge -«ምግብና መድኃኒት የለም። የኅጻናቱ ይዞታ ሥጋት ላይ ጥሎናል። ካለፈው እሁድ አንስቶ እህል አልቀመሱም። ትናንት ማታ አማጽያኑ ወደ ከተማይቱ ሲጠጉ ፣ ከመንግሥት ወታደሮች ጋር በተደረገው ፍልሚያ፣ ጥይቱ በላያችን ላይ ሲያፏጭ መድፉም ሲያጓራ ነበረ። ሽብር በሽብር ነበረ የሆነው። ሌሊቱን ሜዳ ላይ ነው ያነጋነው። ሁኔታው እጅግ አስከፊ ነው።»
ዓለም አቀፉ የውዝግቦች አጥኚና ተንታኝ ድርጅት (ICG)ትናንት ከለንደን እናዳስታወቀው ከሆነ የጎማ በአማጽያን መያዝ ፣ በኮንጎና በሩዋንዳ መካከል ጦርነት እንዳያስነሳ ያሠጋል። ዩጋንዳ ፣ ማዕራባዊውን ወሰኗን በጥብቅ ከመቆጣጠሯም ሌላ፤ ውጊያው ከድንበሯ እንዳያልፍ ዋናውን የወሰን ጎዳና ባለፈው ሳምንት መዝጋቷ የሚታወስ ነው። ሩዋንዳና ዩጋንዳ፤ ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መርማሪና ብይን ሰጪ ፍርድ ቤት በወንጀል የሚፈልጋቸው የጦር ሠራዊት ጀኔራል ቦስኮ እንታንጋንዳ የሚመሩትን የአማጽያን ቡድን ነው የሚደግፉ በማለት ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ የሠነዘረችውን ክስ ሐሰት ሲሉ አስተባብለዋል።


የምሥራቅ ኮንጎ አማጽያን ጎማን በዛሬው ዕለት ሲቆጣጠሩ ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ወታደሮችና ፖሊሶች፤ እየከዱ ከእነርሱ ጋር መቀላቀላቸው የታወቀ ሲሆን፤ እነዚሁ M 23 በመባል የታወቁት አማጽያንም ፤ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክን በመላ«ነጻ እናወጣለን » የሚል ዛቻም ሆነ መግለጫ በማሰማት ላይ ናቸው። በሺ የሚቆጠሩ የጎማ ኑዋሪዎች፤ በ M 23 ኮሎኔል ቪያኒ ካዛራማ መግለጫው ሲሰጥ ደስታቸውን በጭብጨባ መግለጣቸው ነው የተነገረው። ካዛራማ፤ የደቡብ ኪቩ ጠ/ግዛት ርእሰ ከተማ ቡካቩ ቀጣይ ዒላማ መደረጓን አያይዘው ነው የገለጡት። ህዝቡም ሰላምና ፀጥታ እስከምን ድረስ እንደሚሠፍኑ ሳያውቅ በመፈንጠዝ ላይ ነው።
በጎማ መያዝ ሁሉም አይደለም የተደሰተው የተናደዱ ፣ ብርቱ ቅሬታ ያደረባቸው ጥቂቶች አይደሉም።
«መንግሥታችን አሳልፎ እንደሰጠን ነው የሚሰማን። ምን እንደምናደርግ ግራ ገብቶናል። የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች፤ ሰላም እንደሌለ እያወቁ ሁሉንም ነገር ችላ ብለውታል። ምንም ሳይከላከሉ ነው አማጽያኑ ጎማን ገብተው የያዟት። እንደተታለልን ነው የሚሰማን!»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic