የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት የጋዜጠኞች ደህንነት ጉባዔ | አፍሪቃ | DW | 16.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት የጋዜጠኞች ደህንነት ጉባዔ

የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት የጋዜጠኞችን ደህንነት ለማረጋገጥ ሊወስዷቸው ስለሚገቡ አገር አቀፍ  መላዎች የመከረ የሁለት ቀን ጉባዔ በኬንያ ናይሮቢ ተካሄዷል፡፡ ጉባዔው የተካሄደው በኢትዮጵያ የዘመን ቀመር ህዳር አራት እና አምስት ፣ 2010 ዓመተምህረት ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:42

የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት የጋዜጠኞች ደህንነት ጉባዔ

በጉባዔው ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ  ከ7 የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት የመጡ ጠቅላላ ብዛታቸው 120  የሆኑ ጋዜጠኞች ፣በጋዜጠኞች መብት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ተወካዮች ፣በየሀገራቱ የመገናኛ ብዙሃንን ቁጥጥር የሚከውኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተወካዮች እና ሌሎች ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ወገኖች ተሳትፈውበታል፡፡
ለጉባዔው የገንዘብ እና የሙያ ደጋፊ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣የሳይንስ፣እና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ የምስራቅ አፍረቃ ቀጠና ዳይሬክተር   አን ቴሬስ ዶንግ ጄታ  ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጋዜጠኞች ላይ እየደረሱ ያለ ጥቃቶች ከዕለት ተዕለት እየተባባሱ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ባለፉት 11 ዓመታት 930 ጋዜጠኞች መገደላቸውን ድርጅታቸው በጥናት እንዳረጋገጠም ለታዳሚው አጋርተዋል፡፡በሚያስቆጭ መልኩ  ከጥቃት አድራሾቹ መካከል ብዙሃኑ ለወንጀላቸው ተጠያቂ ሳይሆኑ እየቀሩ እንደሆነ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
‹‹የዩኔስኮ ምዘና እንደሚያመላክተው በአሁኑ ወቅት   ከ10 ሁነቶች(የጋዜጠኞችን ጥቃት የሚያሳዩ ክስተቶችን ማለታቸው ነው) በዘጠኙ ገዳዮች ሳይቀጡ ይታለፋሉ፡፡›› ብለዋል፡፡
 ዳይሬክተሯ እንዲህ ያለው መድረክ ሀገራት የጋዜጠኞችን ደህንነት ለመጠበቅ ሊያደርጓቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ለማሳወቅ ያለውን ሚና ዘርዝረዋል፡፡
በኮንፍረንሱ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች በየግዛቶቻቸው እየገጠሟቸው ያሉ ከደህንት ጋር የተገናኙ ተግዳሮቶችን አጋርተዋል፡፡ግድያ፣እስር፣መሰደድ፣የተለያዩ አካላት ዛቻ እና ጣልቃ ገብነት የቀጠናው ጋዜጠኞች የደህንነት ስጋት እንደሆኑ  ተዘርዝሯል፡፡
 ጋዜጠኞችን በመግደል ባይሆንም በእስር፣ማሰደድ እና እንግልት ሲፒጄን በመሰሉ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ስትወቀስ በባጀችው ኢትዮጵያ ያለው የመገናኛ ብዙሃን እና ጋዜጠኞች ደህነት ሁኔታ በጋዜጠኛ ታምራት ወልደጊዮጊስ በኩል ቀርቧል፡፡ 
 አዲስ ፎርቹን የተሰኘው የንግድ እና ስነ-ነዋይ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ታምራት ወልደ ጊዮርጊስ  የኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙሃን እና ጋዜጠኞች ደህንነት ሁኔታ ከቀጠናው ሀገራት ጋር አወዳድሮ እንዲህ ይላል፡፡
‹‹ከአንዳንዶቹ ሀገራት የተሻለ ነው ፤ከአንዳንዶቹ ደግሞ የባሰ ነው፡፡ለምሳሌ ከሱዳን ከጂቡቲ እና ሶማሊያ ጋር የምታወዳድረው ከሆነ የተሻለ ነው፡፡ከኬንያ፣ዮጋንዳ፣ከታንዛኒያ ጋር የምታወዳድረው ደግሞ ከሆነ እጅግ በጣም ያነሰ ነው፡፡››
 በዚህ ጉባዔ ላይ ከችግሮች ባለፈ የተሻለ መፍትሄ እየተገበርን ነው ያሉ ሀገራት ተወካዮች ልምዳቸውን አጋርተዋል፡፡ጋዜጠኛ ታምራት ከሰማቸው የሀገራት ልምዶች መካከል የየትኛው ሀገር ትኩረቱን እንደሳበው ጠይቄው ነበር፡፡ታምራት ሲመልስ ይሄንን ብሏል፡፡
‹‹የሩዋንዳ ስሜቴን ይዞታል ፡፡ምክንያቱም የሩዋንዳ ብዙሃን መገናኛ ምክር ቤት ለፍርድ ቤት ዳኞች ፣ለዐቃቢያነ ህግ፣ለፖሊሶች ሚድያ ሊትረሲ የሚባለውን ስለሚዲያ አሰራር ስለጋዜጠኞች መብት ፣ኃላፊነት ተከታታይ  ስልጠና እንዲያገኙ ያደርጋል።

በጉባዔው መጨረሻ የአቋም መግለጫ ተሰምቷል፡፡በመግለጫው ላይ ተሳታፊዎች  የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የየሀገራቸውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገር አቀፍ የጋዜጠኞችን ደህንነቶችን የሚያስጠብቁ አሰራሮችን መፍጠር እንዳለባቸው፤ አጽንኦት ተሰጥቷል፡፡
 ሀብታሙ ስዩም 
አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic