የምሥራቅ አውሮፓ የኤኮኖሚ ይዞታና የዓለም ባንክ ዘገባ | ኤኮኖሚ | DW | 02.11.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የምሥራቅ አውሮፓ የኤኮኖሚ ይዞታና የዓለም ባንክ ዘገባ

የዓለም ባንክ ጠበብት ጥናቱን ያካሄዱት በማዕከላዊና ምሥራቅ አውሮፓ የቀድሞ ሶሻሊስት አገሮች ይሠራበት የነበረው በማዕከላዊ ዕቅድ ላይ የተመሠረተ የኤኮኖሚ ስርዓት ከወደቀ ወዲህ ወደ ገበያው ኤኮኖሚ የተደረገው ሽግግር በሥራው ገበያ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ለይቶ ለማወቅ ነበር። ለዚሁ ተግባር ከቀድሞይቱ የሶቪየት እሢያ ሬፑብሊክ ከኪርጊዚያ የአውሮፓን ሕብረት እስከተቀላቀሎት እስከ ፖላንድና ቼክ ሬፑብሊክ ከ 27 አገሮች የተገኙ መረጃ ዳታዎች ተሰብስበው ተጠንተዋል።

ውጤቱ እምብዛም ተሥፋን የሚያዳብር ሆኖ አልተገኘም። ምንም እንኳ በዓለምአቀፍ ንጽጽር፤ የተፋጠነ ዕርምጃ በማድረግ ላይ ከሚገኙት የእሢያ አገሮች ከቻይናና ከሕንድ ብቻ ዝቅ ያለ በከፊል ከፍተኛ የሆነ የኤኮኖሚ ዕድገት ቢከሰትም በሥራ ገበያው ላይ ከዚህ የተጣጣመ ስኬት አለመታየቱ ነው የተገለጸው። ከሞላ ጎደል በሁሉም ጥናቱ ባተኮረባቸው አገሮች የሥራ-አጡ ቁጥር ከፍተኛ ነው። ሥራ ከተገኘም ክፍያው በአብዛኛው ዝቅተኛ ነው፤ የዓለም ባንክ የሥራ ገበያ ጉዳይ ተመራማሪና ከተቋሙ ዘገባ አጠናቃሪ ጠበብት አንዱ የሆኑት ስቴፋኖ ስካርፔታ እንደሚሉት።

በግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ የሥራ መስኮችን በሰፊው በመክፈት በጅምሩ የነበረው ከፍተኛ የሥራ-አጥ ቁጥር ይቀንሳል የሚል ታላቅ ተሥፋ ነበር የተጣለው። ችግሩ ይሁንና ሽግግሩ ከጀመረ ከ 15 ዓመታት በኋላም በአብዛኞቹ አገሮች የሥራ-አጡ ቁጥር ከአሥር በመቶ በበለጠ መጠን ጸንቶ መቀጠሉ ነው። ከዚሁ ሌላ በማዕከላዊው አውሮፓ ቢያንስ 50 በመቶው ሥራ-አጥ ከአንድ ዓመት በላይ የቦዘነ ሆኖ ይገኛል ሲሉ ስቴፋኖ ስካርፔታ አስረድተዋል።

ለምሳሌ ያህል በፖላንድና በስሎቫኪያ የሥራ-አጡ ብዛት ባለፈው ዓመት 19 በመቶ ገደማ በመጠጋት ከዕድገቱ መጠን ሲነጻጸር እጅግ ከፍ ያለ ነበር። ሁንጋሪያን በመሳሰሉ አንዳንድ የአካባቢው አገሮች ደግሞ ብዙዎች ሥራ-አጦች ከናካቴው በምዝገባው ሰንጠረዥ ውስጥ ተጠቃለው አይገኙም። ሥራ ፍለጋውን ተሥፋ ቆርጠው ትተውታል ማለት ነው። እርግጥ ይህን መሰሉ ሁኔታ በሌሎች የገበያ ኤኮኖሚ ስርዓት በሰፈነባቸው አገሮች ባይታጣም በምሥራቃዊው አውሮፓ ችግሩን ይበልጥ የሚያከብደው የማሕበራዊው ዋስትና ጉድለት መባባስ ነው።

የዓለም ባንኩ ባለሙያ ስካርፔታ እንደሚሉት ብዙዎች የሚሠሩት በውል በተቀመጠ የቀጣሪ-ተቀጣሪ ግንኙነት አይደለም። በመሆኑም ማሕበራዊ ዋስትናም ሆነ በሥራ ዘመናቸው ለሰጡት አገልግሎት የሚያገኙት የጡረታ መብትም የላቸውም። አብዛኛውን ጊዜ ግብር አይከፍሉም፤ የሚሠትም በትናንሽ ፋብሪካዎች ነው። በጠቅላላው የሥራ ሁኔታው የሚታይበት ችግር ለስጋት መንስዔ ሆኗል።

ይህ ደግሞ በተለይ ጎልቶ የሚታየው ከሥራ-አጡ ብዛት ይልቅ የሥራ ሁኔታው ጥራት አሳሳቢ ሆኖ በሚገኝባቸው በቀድሞዎቹ የሶቪየት ሬፑብሊኮች ነው። የዓለም ባንክ በምሥራቅ አውሮፓ ድህነትን በመታገሉ በኩል ባለፉት ዓመታት የታየው ስኬት በመካከለኛ ጊዜ የሥራ ገበያው ሁኔታ ካልተሻሻለ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችልም በዘገባው አመልክቷል። ተቋሙ የተለያዩት አገሮች ተጨባጭ ሁኔታ የተለያየ መሆኑን በማጤን አጠቃላይ የመፍትሄ ሃሣብ ለመሰንዘር አልፈለገም። ቢሆንም ኩባንያዎችን መሳቡና የሥራ-መስኮችን ማስፋፋቱ፤ እንዲሁም የማሕበራዊ ዋስትና መረቦችን በሰፊው መዘርጋቱ ግድ መሆኑን ሳያስገነዝብ አላለፈም። መሰናክል የሆነው ቢሮክራሲ መወገዱንም እንዲሁ!