1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሜድሮክ ወርቅ ማውጫ የተስማሚነት ሽልማት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 25 2016

የኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢ ድርጅት አንዱ አካል ሆኖ በቅርቡ በአዲስ መስሪያ ቤትነት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዛሬ ለሜድሮክ ወርቅ ማውጫ ኩባንያ የሰጠው ሴርቲፊኬሽን በኢንቫይሮሜንታል ማነጅመንት ሲስተም (የአከባቢ ጥበቃ ስርዓት) በ- ISO 14001 በሚባል የዓለማቀፍ ስርዓት መስፈርት መሆኑን አስረድቷል

https://p.dw.com/p/4hmnK
ለሜድሮክ ኢትዮጵያ የተስማሚነት ማረጋገጪያ የተሰጠዉ ከብዙ ጥናትና ክትትል በኋላ መሆኑ ተነግሯል
የሜድሮክ ወርቅ ማውጫ የተስማሚነት ማረጋገጪያ ሰርቲፊኬት በተቀበለበት ወቅት ምስል Seyoum Getu/DW

የሜድሮክ ወርቅ ማውጫ የተስማሚነት ሽልማት

 

የሜድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካል የሆነው ሜድሮክ ወርቅ ማውጫ ማዕደንበማውጣትና ማምረት ሂደት ለአከባቢ ጥበቃ የሚገባውን የጥንቃቄ መስፈርት አሟልቷል የሚል የእውቅና ሰርተፊኬት ተሰጠው፡፡እውቅናውን የሰጠው የዓለማቀፍ ጥራት እውቅና ፎረም (IEC) አባል የሆነው የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት (ECAE) ነው፡፡ ይህም በዓለማቀፉ ተስማሚነት ድርጅት (ISO) መስፈርት መሰረት ነው ተብሏል፡፡ሜድሮክ ወርቅ ማዉጪያ በውርቅ ማዕድን አካባቢ ላሉ ሰዎችና የተፈጥሮ ሐብት አይጠነቀቅም ተብሎ ሲወቀስ ነበር።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሥዩም ጌቱ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል።
የሽልማቱ አሰጣጥና መስፈርቱ

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ባለስልጣን ወይም የኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢ ድርጅት አንዱ አካል ሆኖ በቅርቡ በአዲስ መስሪያ ቤትነት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዛሬ ለሜድሮክ ወርቅ ማውጫ ኩባንያ የሰጠው ሴርቲፊኬሽን በኢንቫይሮሜንታል ማነጅመንት ሲስተም (የአከባቢ ጥበቃ ስርዓት) በ- ISO 14001 በሚባል የዓለማቀፍ ስርዓት መስፈርት መሆኑን አስረድቷል፡፡ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት (Ethiopian Conformity Assessment Enterprise) አገልግሎቱን እየሰጠ ያለውም በዓለማቀፍ ደረጃ በተሰጠው እውቅና መሰረት በገለልተኝነት ጥልቅ ጥናት በመስራት ነው ተብሏል፡፡ የድርጅቱ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቤል አምበርብር ዛሬ ለሜድሮክ ወርቅ ማውጫ ኩባንያ የተሰጠውን እውቅና በማስመልከት ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ቃለምልልስ እውቅናው የተሰጠው በ- ISO 14001 የተቀመጡ ፕሮቶኮል መሟላት በመረጋገጡ ነው ብለዋል፡፡ 

“በዓለማቀፉ የእውቅና መስፈርቱ ለአከባቢ ተስማሚነትን ስለማሟላቱ ሙሉውን ማረጋገጥ የመጀመሪያው ተግባራችን ነው፡፡ ሌላው ከመንግስት የሚሰጡ የተለያዩ ህግጋትን ማሟላታቸው ይታያል፡፡ የተረፈምርት አወጋገድ፣ የሚጠቀሙባቸው ግብዓቶች፣ የሰራተኞች አያያዝ ብቃት፣ ብሎም አገሪቱ የፈረመቻቸውን የአከባቢ ትበቃ መስፈርቶች ማሟላቱ ተረጋግጦ የተገኙ የኦዲት ግኝቶች እንዲስተካከሉ ምክረሃሳብ ተሰጥቶ ነው እውቅናው የተሰጠው” ብለዋል፡፡ ለዚያም የተለያዩ ናሙናዎች ተወስደው በላቦራቶሪ ተረጋግጠው እውቅናው መሰረቱን አመልክተዋል፡፡
 

ECAE የተባለዉ ተቋም ለሜድሮክ ኢትዮጵያ የወቅርቅ ማዉጪያ ኩባንያ ማረጋገጪያ የሰጠበት ምክንያት ሲዘረዘር
ECAE የተባለዉ ተቋም ለሜድሮክ ኢትዮጵያ የወቅርቅ ማዉጪያ ኩባንያ ማረጋገጪያ የሰጠበት ምክንያት ሲዘረዘር ምስል Seyoum Getu/DW

የተስማሚነት መስፈርቶች እና ኦዲት አደራረግ

እንደ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ገለጻ ሜድሮክ ኢትዮጵያ መስፈርቱን አስጠብቆ መጓዝ ይጠበቅበታል፡፡ ዛሬ የተሰጠው የእውቅና ሰርቲፊኬትም በየሶስት ዓመት የሚታደስ ሆኖ ድንገተኛ ፍተሸዎችና ክትትሎች ግን በያመቱ የሚደረጉበት የአሰራር ስርዓቶች መኖራቸውም ተነግሯል፡፡ አሁን ባለው መስፈርት የተቀመጠውን ዓለማቀፍ የአሰራር ስርዓት በማሟላታቸው የሶስተኛ ወገን የማረጋገጫ ሰርተፊኬት ይሰጥ እንጂ በኦዲት ስርዓት እንዲስተካከል የተሰጠውን የማያስተካክል ከሆነ በየትኛውም ጊዜ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም ተጠቁሟል፡፡ የእስካሁኑ ግኝቶቹ ምንነትን በተመለከተ በዶይቼ ቬለ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አቤል አምበርብር መረጃዎች በሙሉ ተላልፈው እንደማይሰጡ ጠቁመው ኦዲቶቹ ግን መስተካከላቸውን ገልጸዋል፡፡ 

“በተስማሚነት ምዘና የሚሰጡ አገልግሎቶች የሶስተኛ ወገን መረጃ እንደመሆናቸው የደንደኞች መረጃዎችን የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ በመጀመሪያ ግኝቶችን ካስተካከሉና ያ በኦዲት ከተረጋገጠ በኋላ ነው ሰርቲፊኬቱን የሚያገኙት” ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኬንያ የሚገኘው ሌላው ዓለማቀፍ እውቅና ያለው የተስማሚነት ምዘና ተቋም  በኦዲት ስራው ተሳትፎ ማጣራት ሂደቱ  የተለያዩ ደረጃዎች ስር አልፎ እውቅና መሰጠቱን አረጋግጠዋል፡፡
ሜድሮክ ኢትዮጵያ ላይ የሚቀርቡ ክሶችና የኩባንያው ምላሽ

ሜድሮክ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በተለይም በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በሚገኘው የለገደንቢ ወርቅ ማውጫ ላይ ለአከባቢው ማህበረሰብ ያልበጁ የአከባቢ ጥበቃ ጥሰቶችን ከውኗል በሚል ስራ እስከማቆም ያደረሱት ተቃውሞዎች ገጥመውት ያውቃሉ፡፡ ከአንድ ኣመት በፊት የአከባቢውን ማህበረሰብ በማነጋገር ሰብዓዊ ድርጅት የሆነው ሁማን ራይትስ ዎች ተጥሷል ባላቸው አሰራሮች ዙሪያ ሪፖርት አጠናቅሮ ማውጣቱም ይታወሳል፡፡ 

ዛሬ በእውቅና መርሃግብሩ መድረክ ላይ አጠር ያለ ንግግር ያደረጉት የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ እነዚያን ክሶች አጣጥለው ነቅፈዋል፡፡ በአከባቢው ለወርቅ ማጣሪያ የሚውለውን በካይ የሆነውን የሜርኩሪ ንጥረ ነገር የሚጠቀሙ ሌሎች ኩባንያዎች እንጂ ሜድሮክ አይደለም ነው ያሉት፡፡ እነዚያን ኩባንያዎች ግን “መንገስታዊና የግል ተቋማት” ከማለት ውጪ በስም አልጠቀሱዋቸውም፡፡ 

የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በኩባንያቸዉ ላይ የሚሠነዘረዉን ወቀሳ ነቅፈዉታል
የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ማረጋገጪያዉን ከተቀበሉ በኋላምስል Seyoum Getu/DW

“ሜድሮክ ለፖለቲካ ተጋላጭም ሆኖ ስራው እስከመታገት ደርሷል” ያሉት የሜድሮክ ዋና ስራ አስፈጻሚው በፈጠረው የአሰራር ግልጽነትና ከመንግስት ጋር ተነጋግሮ ወደ ስራው መመለሱን፤ በዚህም ከሚጣልበት መደበኛ ታክስ በተጨማሪ ከሚሸጠው ምርት ለኦሮሚያ ክልል 5 በመቶ ድርሻ እንደሚያካፍል፤ ብሎም በአከባቢው ማህበራዊ ሃላፊነቱን  እንደሚወጣም አስረድተዋል፡፡ ይሁንና “እንዲህም ሆኖ ከሀሜት አልዳንም” ያሉት ስራ አስፈታሚው እስከ  ምክር ቤት አባል ውስጥ የሚሰሩ ግለሰቦች ክሱን  ብያቀርቡም ዛሬ በሶስተኛ ወገን በገለለልተኝነት ተረጋግጦ ተሰጣቸው ሰርተፊኬት እፎይታን ሊሰጥ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር