የሜርክል ጉብኝት በቱኒዚያ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 05.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የሜርክል ጉብኝት በቱኒዚያ

የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በሰሜን አፍሪቃ ሃገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት ቀጥለዋል። ሀገራቸዉም ለቱኒዚያ የ250 ሚሊየን ዩሮ የልማት ርዳታ እንደምትሰጥ ቃል ገብተዋል።

ዛሬ ቱኒዚያን የጎበኙት ሜርክል በሁለቱ ሃገራት መካከል የኤኮኖሚ ትስስሩን ለማጠናከር እና ቱኒዚያ ወደ አዉሮጳ የሚሻገሩ ተሰዳጆችን እንድትገታ ከመሪዎቿ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል። ከቱኒዚያ ፕሬዝደንት ቤጂ ሳይድ ኤሳብሲ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዩሱፍ ቻዴ ጋር የሚነጋገሩት ሜርክል በመቀጠልም ለሀገሪቱ ምክር ቤት ንግግር እንደሚያደርጉ ተገልጿል። ባለፈዉ ወር ሜርክል ወደ ሀገራቸዉ በፈቃዳቸዉ ለሚመለሱ የቱኒዚያ ተሰዳጆች ማበረታቻ የገንዘብ እና የትምህርት ድጋፍ ለመስጠት ሃሳብ አቅርበዋል። ለተሰዳጆች እጃቸዉን በመዘርጋት የሚተቹት አንጌላ ሜርክል በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በጀርመን የሚካሄደዉ ምርጫ ከመድረሱ አስቀድመዉ ማስተካከያዎች ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ነዉ ዘገባዎች የሚያመለክቱት። 
«ሰዎች በፈቃደኝነት ወደሀገራቸዉ የመመለስ ፍላጎት እንዲኖራቸዉ፤ መማር እንዲችሉም ሆነ ለኑሯቸዉ መቋቋሚያ ቢያገኙ ወይም ደግሞ ቱኒዚያ ዉስጥም ቢሆን ንግድ የሚጀምሩበት አለያም ተመሳሳይ ነገር እንዲሠሩ መነሻ ገንዘብ እንዲያገኙ ማድረግ ከቻልን አጓጊ ልናደርገዉ እንችላለን።»
ሜርክል ለቱኒዚያ ምክር ቤት በሚያደርጉት ንግግር ሀገሪቱ የድንበር ቁጥጥሯን እንድታጠናክር እና ጀርመን ሀገር ተቀባይነት ያላገኙ ጥገኝነት ጠያቂ ዜጎቿን ባፋጣኝ መመለስ እንድትጀምር እንደሚያሳስቡ ተጠቁሟል። ባለፈዉ ታኅሳስ ወር በርሊን ላይ 12 ሰዎችን በከባድ መኪና ገጭቶ በመግደል የሚጠረጠረዉ አኒስ አሚር የጥገኝነት ጥያቄዉ ተቀባይነት ያላገኘ የቱኒዚያ ዜጋ መሆኑ በተደጋጋሚ ይገለጻል። 
 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ