የሜርክል የ«እንወጣዋለን»መርህ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 30.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የሜርክል የ«እንወጣዋለን»መርህ

የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጦርነት እና ጨቋኝ መንግሥታትን ሸሽተው ለመጡ ስደተኞች የጀርመን ድንበር እንዲከፈት ከፈቀዱ አንድ ዓመት አለፈ ። ይህ የሜርክል ውሳኔ በወቅቱ ቢያስመሰግናቸውም ከሀገር ውስጥ ስጋትም ተቃውሞም አስነስቶባቸው ነበር ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:31

የሜርክል የ«እንወጣዋለን»መርህ

ሜርክል ግን ያኔም አሁንም አያቅተንም «እንወጣዋለን »በሚለው አቋማቸው ፀንተዋል ። ይህ የሜርክል የስደተኞች መርህ ምን ውጤት አስገኘ ? ያስከተላቸው ችግሮችስ ምንድን ናቸው ? ውሳኔያቸውስ በመጪው የጀርመን ምክር ቤት ምርጫ ላይስ ምን ዓይነት ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል?

«እንወጣዋለን »

በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 2015 የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ስደተኞች በብዛት ወደ ጀርመን መምጣታቸው እንደማይቀር ሲታወቅ ህዝባቸውን ለማረጋጋት የተናገሩት ቃል ነበር ። ሜርክል ይህን ያሉት ያኔ ብቻ አልነበረም ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በሃገሪቱ ታሪክ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የተባለ በርካታ ስደተኛ ወደ ጀርመን መግባቱ ችግሮችን አስከትሏል በተባለበት ጊዜ ሁሉ ደጋግመውታል ። ባለፈው እሁድ ARD የተባለው የጀርመን ቴሌዢዥን ጣቢያ ባካሄደላቸው ቃለ መጠይቅ ይህን ለማለት ያበቃቸው ምን እንደሆነ ተጠይቀው ነበር ። ይህን ያልኩት ሲሉ ነበር ሜርክል መልስ መስጠት የጀመሩት

«ይህን ያልኩት ከፊታችን የሚጠብቀንን ትልቅ ሥራ ታሳቢ በማድረግ ነበር ። ነሐሴ 19 ፣ ጀርመን ሊመጡ ይችላሉ ተብሎ የታሰቡት ስደተኞች ቁጥር ወደ 800 ሺህ ተገመተ ። ከዚያ በኋላ በድንበር ከተማዋ በሃይድኖፍ የውጭ ዜጎች ጥላቻ ተሰማ ። ከዚያም እኛ ከባዱን ሥራችንን መሥራት መቀጠል አለብን ብዬ እንወጣዋለን በሚል ማበረታቻ ከፊታችን የሚጋረጡብንን መወጣት አለብን አልኩኝ ።ካለፈው ነሐሴ አንስቶ አበክረን ሰርተናል ፤ በርግጥ ተጨማሪ ሥራዎች መሥራት ይኖርብናል ።» ካለፈው ዓመት ነሐሴ አንስቶም በጥቂት ወራት ውስጥ ጀርመን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ስታስገባ ውሳኔያቸው በውጭው ዓለምም ሆነ በአገር ውስጥ ቢያስመሰግናቸውም ተቃውሞም አስነስቶባቸው ነበር ። ሜርክል ግን ለተቃዋሚዎቻቸው እና ስጋት ላደረባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ደጋግመው « ማድረግ እንችላለን » « እንወጣዋለን » በሚለው አባባላቸው ነው የፀኑት ። ሜርክል ከዛሬ ዓመት አንስቶ በዚህ ጉዳይ ላይ ከእህት ፓርቲያቸው ከክርስቲያን ሶሻል ህብረት በምህፃሩ CSU ፓርቲ ከራሳቸው ከክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት በጀርመንኛው ምህጻር CDU ፓርቲ አባላት እንዲሁም የመንግሥቱ ተጣማሪ ከሆኑት ከሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ እና ከምሁራን በኩል ወቀሳዎች ይሰነዘሩባቸዋል ። የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደሚለው ከሚቀርቡባቸው ትችቶች መካከል ዋና ዋናዎቹን የሚከተሉት ናቸው።

ከዚህ ሌላ ካለ በቂ ዝግጅት እና የስደተኞችም ማንነት ሳይጣራ ስደተኞች ጀርመን እንዲገቡ መደረጉ የሃገሪቱን ደህንነት ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል የሚሉ እና የመሳሰሉት ትችቶች ቢሰነዘሩም ሜርክል ግን አሁንም እንችለዋለን እንወጣዋለን በሚለው አቋማቸው ነው የፀኑት ። ውሳኔያቸው መጀመሪያ ላይ የብዙዎችን አድናቆት ቢያገኝም በቅርቡ በተካሄደ መጠይቅ መሠረት አሁን ሃሳባቸውን የሚደግፈው ከህዝቡ 42 በመቶ ብቻ መሆኑ ነው የተነገረው ።ሜርክል ARD ከተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ በአከራካሪው የስደተኞች ጉዳይ ላይ መንግሥት ባለፈው አንድ

ዓመት ብዙ ማከናወኑን ነው የተናገሩት ።

«ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር አሁን ፍፁም የተለየ ሁኔታ ላይ ነው የምንገኘው ። የፌደራል የስደት እና የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ አዳዲስ ስደተኞችን የሚከታተሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ሠራተኞች አሉት ። ችግሩን ለመውጣት የበርሊን መንግሥት ለአካባቢ አስተዳደሮችን እና ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እያደረገ ነው ። ጀርመን መቆየት ለማይችሉ ስደተኞች አዳዲስ እና ጥብቅ ደንቦች ወጥተዋል ። ስደተኞችም ከህብረተሰቡ ጋር መዋሃድ እና ጀርመንኛ ቋንቋ መማር የግድ ይላቸዋል ።»

የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንዳለውም ጀርመን ስደተኞችን በብዛት ካስገባች በኋላ የተሰራው ጥቂት የሚባል አይደለም ። በተለይ ይላል ይልማ የስደተኞችን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት እና ወደፊትም ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህደው እንዲኖሩ ለማስቻል መንግሥት የመደበው ገንዘብ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል ።

ምንም እንኳን በአንድ ዓመት ውስጥ እነዚህ ውጤቶች በስኬት ቢመዘገቡም ያልተሳኩም አሉ እንደገና ይልማ ።ከመካከላቸው ጀርመን የገቡትን ስደተኞች ሌሎች የአውሮጳ ህብረት እንዲከፋፈሉ የቀረበው ጥሪ አንዱ ነው ። ሜርክል በእሁዱ ቃለ መጠይቅ የአውሮፓ ህብረት ለስደተኞች ቀውስ የጋራ መፍትሄ እንዲፈልግ ዳግም ጠይቀዋል ። አንዳንድ

የአውሮጳ ሃገራትም ሙስሊሞች ስለሆኑ ብቻ ስደተኞችን አናስገባም ማለት እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል ።በሌላ በኩል አወዛጋቢው የስደተኞች ቀውስ በመጪው ዓመት በሚካሄደው የጀርመን ምክር ቤት ምርጫ ውጤት ላይ ተፅእኖ ማሳደሩ እንደማይቀር ከወዲሁ ፍንጮች እየታዩ ነው ። ስደተኞች በብዛት ጀርመን መግባት ከጀመሩ ወዲህ በሚካሄዱ የአካባቢ ምርጫዎች ፀረ የውጭ ዜጋ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች አብላጫ ድምፅ ያገኙባቸው እና ከቀድሞው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡባቸው ቦታዎች ጥቂት አይደሉም ።ይህ አዝማሚያ ሜርክል ለ4 ተኛ የሥልጣን ዘመን የሚወዳደሩ ከሆነ ምን ዓይነት ተጽእኖ ያሳድር ይሆን ?

በእሁዱ ቃለ ምልልስ ላይ ለ4ተኛ የሥልጣን ዘመን ይወዳደሩ እንደሆነ የተጠየቁት ሜርክል ትክክለኛው ጊዜ ሲደርስ አሳውቃለሁ ሲሉ ነበር የመለሱት ። ሜርክል አሁን ለምን በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጠቡ።

ቀጣዩ የጀርመን ምክር ቤት ምርጫ በጎርጎሮሳዊው 2017በቅርቡ የተካሄደ መጠይቅ ሜርክል ለተጨማሪ የሥልጣን ዘመን መቆየታቸውን ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ጀርመናውያን መቃወማቸውን አሳይቷል ። በመስከረም ውር ይካሄዳል ። ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መናገር ቢያዳግትም ከቀደሙት ምርጫዎች የተለየ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች