የማገገም ጭላንችል በኤውሮ-ዞን | ኤኮኖሚ | DW | 21.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የማገገም ጭላንችል በኤውሮ-ዞን

የ 17ቱ የኤውሮ ዞን ዓባል ሃገራት የኤኮኖሚ ይዞታ ካለፉት የቀውስ ዓመታት አንጻር በወቅቱ ከሚጠበቀው በላይ ሻል ብሎ ተገኝቷል።

ሆኖም የማገገሙ ሂደት የማይታጠፍ ቀጣይ ነገር መሆኑን ለማረጋገጥ በወቅቱ በጣሙን የሚያዳግት ነው። በአውሮፓ ሕብረት መቀመጫ በብራስልስ የምጣኔ-ሐብት ጉዳይ ተመራማሪ የሆኑትን ጉንትራም ቮልፍን የመሳሰሉ ባለሙያዎችም በመሻሻሉ ሂደት አውሮፓ ገና ከማጡ ጨርሳ እንዳልወጣች ነው የሚያስገነዝቡት።

ኤውሮስታት በመባል የሚታወቀው የአውሮፓ የሰንጠረዥ ተቋም ባቀረበው አዲስ መረጃ መሠረት የኤውሮ ዞን አካባቢ ቢቀር በወቅቱ ከቀውስ መስፈርቱ ተላቆ ወጥቷል። የ 17ቱ የኤውሮ ዞን ሃገራት ኤኮኖሚ በያዝነው ዓመት ሁለተኛ ሩብ ከመጀመሪያው ሲነጻጸር 0,3 ከመቶ ከፍ ማለቱን ነው የኤውሮሳት መረጃ ያመለከተው። ከዚሁ ሌላ ዕድገቱ ቀጣይነት እንደሚኖረውና ጥሩ የንግድ ሁኔታ እንደሚከሰት የሚጠቁሙ አንዳንድ ምልክቶች ከወዲሁ እየታዩ መሆናቸውም ተጠቅሷል።

ይሁን እንጂ በብራስልስ «ብሩግል» በመባል የሚታወቀው የኤኮኖሚ ጠበብት የምርምር ተቋም ሃላፊ የሆኑት ጉንትራም ቮልፍ እንደሚሉት ሁኔታው ቀውሱ አልፏል፤እፎይ ብላችሁ ተጋደሙ የሚያሰኝ አይደለም። ባለሙያው የአውሮፓ ሕብረትና የኤውሮ-ዞን ጉዳይ አዋቂ፤ የጀርመን ቡንደስባንክና የፈረንሣይ ፕሬዚደንት አማካሪም የነበሩ፤ እንዲሁም በርከት ባሉ ዩኑቨርሲቲዎች የሚያስተምሩ ጠቢብ ሲሆኑ በጉዳዩ የሰከነ ዕውቀት ያላቸው ኤክስፐርት ናቸው። በመሆኑም ገና ከማጡ አልተወጣም የሚል አስተያየታቸው በዚህ በአውሮፓ ከፍተኛ ተሰሚነት አለው።

«በወቅቱ የሚቀርቡት አበረታች አሃዞች ጥቂትም ቢሆን እፎይ የሚያሰኙ መሆናቸውን ለመናገር እወዳለሁ። በዕውነትም ሂደቱ የሚያስደንቅ ነው። በተለይም የጀርመንና የፈረንሣይ የዕድገት አሃዞች ግሩም ሲሆኑ ፖርቱጋልም በዓመቱ ሁለተኛ ሩብ ጥሩ ዕድገት አሳይታለች። ሆኖም ግን ገና ከአሁኑ በሆታ ሶፋን አመቻችቶ መቀመጥ እንዳይኖር ለማስገንዘብ እሻለሁ። መፍትሄ የሚጠይቁት ችግሮች ገና ብዙዎች ናቸው። እነዚህን ለመፍታትም በመጪዎቹ ወራትና በሚቀጥለው ዓመት ቀጣይ ጥረት መደረግ ይኖርበታል»

በተለይ የኤውሮ ዞን የበጀት ቀውስ ክፉኛ የመታቸው ሃገራት የፖርቱጋል የዕድገት አዝማሚያ መያዝ፤ የግሪክ ሁኔታ ቢቀር አለመባባስና ችግር ላይ ወድቃ የነበረችው የፈረንሣይም ኤኮኖሚ የማገገም ሂደት ምናልባትም ብዙዎች በዚህ መልክ የጠበቁት አልነበረም። በነገራችን ላይ የፖርቱጋል ኤኮኖሚ የቁጠባ ግፊት በጠነከረበት ሁኔታ 1,1 ከመቶ ዕድገት ማሣየቱ እጅግ አስደናቂ ነው።

ከዚህ አንጻር ሁኔታው ተሥፋ ሰጭ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ሆኖም ጥያቄው እንዲያው ጊዜያዊ የብርሃን ጭላንጭል? ወይስ የዘላቂ ፈውስ ምልክት? የሚል ይሆናል። እርግጥ ፈረንሣይም ሆነች ሌሎቹ ከችግሩ ጨርሶ ለመላቀቅ ገና ብዙ ነው የሚቀራቸው።

«ለፈረንሣይ ኤኮኖሚ ማገገም ትልቅ ሚና የነበረው በአስተማማኝ ሁኔታ በኩባንያዎች ግብር ላይ የተደረገው የጥገና ለውጥ ነው። ይሄው የፉክክር ብቃትን ለማጠንከር በጅቷል። ሆኖም ይህ በኔ ዕምነት የፈረንሣይን ኤኮኖሚ የፉክክር ብቃት ሙሉ በሙሉ መልሶ ለማስፈን በቂ አይደለም። በሁለተኛ ደረጃ የኤኮኖሚ ማረጋጊያው ዕርምጃ ፍጥነት ጋብ እንዲል መደረጉ ጠቃሚ ነገር ነበር። ግን ፈረንሣይ ውስጥ ሁኔታውን ለማሻሻል ገና ታላላቅ ተግባራት ይጠብቃሉ። በተለይም የጡረታው ስርዓት መጠገን የአገሪቱን የፊናንስ ሁኔታ ለዘለቄታው ብቁ ለማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው»

የጡረታው ስርዓት መጠገን ጉዳይ የተጧሪው ሕዝብ ብዛት እየጨመረ በሚሄድባቸው በአብዛኞቹ የአውሮፓ ሃገራት የማሕበራዊ ዋስትና ብቃትን ለዘለቄታው ለማረጋገጥ በጣሙን አጣዳፊ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው። ያለፉት ዓመታት የኤኮኖሚ ችግር ደግሞ ሁኔታውን ይብስ ማክበዱ አልቀረም። አሁን የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሢዮን እንደሚተነብየው ከሆነ ኤውሮ-ዞን ውስጥ በመጪው ዓመት የ 1,4 ከመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት ይጠበቃል። ግን ታዲያ ይሄው ዕድገት በተለይ በደቡባዊው አውሮፓ የተስፋፋውን የስራ አጥ ብዛት ለመቀነስ በቂ ይሆናል ወይ? ጉዳዩ ማጠያየቁ አልቀረም።

«የለም፤ አይበቃም። በአጠቃላይ በአውሮፓ የሚቀርበው የኤኮኖሚ ዕድገት መረጃ አሃዝ በስራ ገበዮች ላይ ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ ገና ሲበዛ ዝቅተኛ ነው። በደቡባዊው አውሮፓ ከፍተኛ ሆኖ የሚገኘው የስራ አጥ ብዛት በሚቀጥለው ዓመትም ባለበት የሚቀጥል ይሆናል። እንግዲህ ችግሩ እስኪቃለል ገና የተወሰነ ጊዜ ይፈጃል ማለት ነው»

በኤውሮ-ዞን ውስጥ ከፍተኛውን የዕድገት አሃዝ በማስመስገብ የአካባቢው ኤኮኖሚ መንኮራኩር ሆና የምትገኘው አገር ጀርመን ናት። በዓለም ላይ በውጭ ንግድ ከቻይና ቀጥላ ሁለተኛዋ ታላቅ አገር የሆነችው ጀርመን ዓለምአቀፉን የፊናንስ ቀውስ በመቋቋሙ ረገድም ከአውሮፓ አጋሮቿ ተሽላና የኤኮኖሚ ጥንካሬዋንም ጠብቃ መቆየቷ የሚታወቅ ጉዳይ ነው።

ታዲያ የጀርመን ኩባንያዎች ምርቶችና አገልግሎቶች ፍላጎት በዓለም ላይ ዛሬም ጠንክሮ ቀጥሏል። የኩባንያዎቹ የኮንትራት ደብተሮች ደከም ካለው የዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ በኋላ እንደገና በምዝገባ መጣበብ ይዘዋል። እናም በውጭ ንግድ ላይ ያለመው የአገሪቱ ኢንዱስትሪ ብዙ እያመረተና ወደ ውጭ እየላከ ነው። መዋዕለ-ነዋይም እየጨመረ ሲሆን ኤኮኖሚው በወቅቱ ከአንድ ዓመት ወዲህ ባልታየ መጠን ማደጉ ታይቷል።

እርግጥ ዕድገቱ የተቀሩትን የኤውሮ-ዞን ሃገራት ይዞ ወደፊት ለማራመድ ገና ዝቅተኛ መሆኑም ሃቅ ነው። በኤውሮ ዞን ዕድገቱን ዘላቂ አድርጎ ለማጣጣም የጀርመን ዕድገት የዋጋ ንረት ታክሎበት በጥቅሉ ወደ አምሥት ከመቶ መዝለቅ ይኖርበታል። የኤውሮ ዞንን ሁኔታ ለማጣጣም እንግዲህ የወቅቱ ከሁለት ከመቶ ያነሰ ዕድገት በቂ አይሆንም ነው።

ሁኔታውን ለመለወጥ የወቅቱ ጨቅላ ዕድገት እያበበ እንዲሄድ መደረግ ይኖርበታል። ግን እዚህ ላይ መንግሥት የኤኮኖሚ ዕድገትን ለማንቀሳቀስ ቁጠባን በመቀነስ የበለጠ መዋዕለ-ነዋይ ማድረጉ ነው የሚበጀው? ወይስ የበጀት ኪሣራን ለማስወገድ ጠንካራ ቁጠባ ማድረግ? የአውሮፓው የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ ጉንትራም ቮልፍ በበኩላቸው የመጀመሪያውን ያስቀድማሉ።

«መንግሥታዊው መዋዕለ-ነዋይ መዳበሩ በተለይም ለጀርመን ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ። በጠቅላላው በአውሮፓ ሕብረት ደረጃ ሲታይ መንግሥታዊው መዋዕለ-ነዋይ በንጽጽር በጀርመን ዝቅተኛው ነው። ታዲያ በቀላሉ ገንዘብ መበደር በሚቻልባት አገር ውስጥ መዋዕለ-ነዋዩ ዝቅተኛ መሆኑ ማስገረሙ አይቀርም። ለነገሩ በጀርመን መንግሥታዊው መዋቅራዊ ይዞታ ብዙ ጉድለት የሚታይበት ነው። ለምሳሌ ሩህር-ገቢት በመባል የሚታወቀውን ምዕራባዊ የቀድሞ የማዕድን አካባቢ ከተመለከትን መዋዕለ-ነዋዩ ከሚገባው ብዙ ኋላ መቅረቱን ለመታዘብ እንችላለን»

ቮልፍ የሚመክሩት ጀርመን በዚህ አኳያ የበለጠ ጥረት እንድታደርግ ነው። ከዚሁ ተያይዞ እርግጥ መዋቅራዊ ለውጥ መደረጉም መረሣት የለበትም። ከየአገሩ ሁኔታ፤ በደቡባዊው አውሮፓም ሆነ በጀርመን፤ እንዲሁም በጥቅሉ በኤውሮ ዞን ከሁኔታው የተጣጣመ መዋቅራዊ ጥገና መካሄዱ መቀጠል ይገባዋል። የኤውሮው አካባቢ ገና የተሟላ የምንዛሪ ሕብረት የሰመረበት አይደለም። የባንኮች ሕብረትም ወደፊት ገና እየተጠቃለለ መሄድ የሚኖርበት ጉዳይ ነው።

ወደ ኤውሮው ዞን የበጀት ቀውስ አንዴ መለስ እንበልና በችግሩ የግሪክን ያህል ከለየለት የሕልውና ፈተና ላይ የወደቀ ሌላ ዓባል ሃገር አልነበረም። እርግጥ የተፈራው መንግሥታዊ ኪሣራ እስካሁን ቢሰወርም የአገሪቱ ኤኮኖሚ በአቆልቋይ ሂደቱ እንደቀጠለ ነው። ሆኖም ጊዜ ይፈጅ እንደሆን እንጂ ግሪክም ተሥፋ ሰጭ ዕርምጃ ማድረጓ ምናልባትም የሚቀር አይመስልም። እርግጥ ይህንንም አስተማማኝ ነው ማለቱ ለጊዜው ይከብዳል።

«የአገሪቱ ብሄራዊ አጠቃላይ ምርት በጥቂቱም ቢሆን ከተጠበቀው በልይ ሻል ብሎ ተገኝቷል። እርግጥ እዚህ ላይ ምናልባት መንግሥት ያቀረበው መረጃ የተሳሳተ ይሆን? ወይስ በዕውነቱ የተሥፋ ጭላንጭል እየያተ ነው? ሁሌም በአዕምሮ የሚንሸራሸር ነገር ነው። እኔ በበኩሌ የሂደት ለውጥ አለ ብዬ ለመናገር አልደፍርም፤ እጠራጠራለሁ። የግሪክ ሁኔታ አሁንም ገና አስቸጋሪ ነው። ኤኮኖሚው እየመነመነ ሲሆን በሁለት እግር ለመቆም ገና ጊዜ የሚጠይቅ ይመስለኛል»

ይህ የብራስልሱ የኤኮኖሚ ባለሙያ የጉንትራም ቮልፍ አመለካከት ነው። ለማጠቃለል የኤውሮ-ዞን ማገገም በዓለምአቀፉ ኤኮኖሚና ንግድ ላይም ገንቢ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል የሚጠበቅ ነው። በፊናንስ ገበዮች ላይ እንደገና የተሻለ አመኔታን ለማስፈንና መዋዕለ-ነዋይን ከፍ ለማድረግ እንደሚበጅም አያጠራጥርም። እርግጥ ከረጅም ጊዜ ክስረት በኋላ በኤውሮ-ዞን የታየው የኤኮኖሚ ዕድገት ተረጋግቶ ወደፊት መቀጠሉ ለሁሉም ወሣኝ ይሆናል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic