የማይክሮሶፍት ተቋም በኮምቦልቻ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 21.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የማይክሮሶፍት ተቋም በኮምቦልቻ

ማይክሮሶፍት የተሰኘው የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ በወሎ ዩኒቨርስቲ ስር ባለው የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አንድ የትምህርት ተቋም በቅርቡ ከፍቷል፡፡ በተቋሙ የሚሰጠውን ስልጠና የሚከታተሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተማሪዎች በፍጥነት ከሚለዋወጠው የዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር እኩል የሚያራምዳቸውን ዕውቀት ይቀስማሉ ተብሏል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:07

ሶፍትዌሮችንና መተግበሪያ ሰሪዎችን ያሰለጥናል

የ24 ዓመቱ ሰለሞን አይዳኝ ብርቱ ተማሪ ነው፡፡ አራት ዓመት የፈጀ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቱን አጠናቅቆ ባለፈው ዓመት ሲመረቅ በማዕረግ ነበር፡፡ የትምህርት ውጤቱን ያየ አንድ የህንድ የጨርቅ ጨርቅ ፋብሪካ በተመረቀበት ሙያ ሲቀጥረው አፍታም አልወሰደበት፡፡ በአንጻራዊነት ጥሩ ክፍያ በሚያገኝበት ስራው ላይ ግን አስር ወር እንኳ አልቆየም፡፡ የቀድሞ ትምህርት ቤቱ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከአሜሪካው ግዙፍ ኩባንያ ማይክሮሶፍት ጋር በመሆን አንድ ተቋም አቋቁሞ ለተማሪዎች ጥሪ ሲያደርግ ለማመልከት አላቅማም፡፡

“ይህን አጋጣሚ ለእኔ በጣም የተለየ አድርጌ ነው የማስበው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዘርፍ የተማርን ማናችንም ብንሆን ማይክሮሶፍት በሚባል ኩባንያ የተመሰከረለት መሆን የማንፈልግ የለንም፡፡ ለመመልመል የወጡት መስፈርቶች ለእኔ በጣም ምቹ ነበሩ፡፡በዚያ ምክንያት ነው ስራዬን ልተው የቻልኩት” ሲል ሰለሞን ምክንያቱን ይናገራል፡፡ 

ሰለሞንን እንደገና ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለስ ካማለለው መመልመያ መስፈርት ውስጥ የመጀመሪያውን በቀጥታ ያሟላል፡፡ የማይክሮሶፍት “የመተግበሪያ ማምረቻ” (APP-Factory) የሚል ስያሜ በተሰጠው በዚህ ተቋም ለመማር እንዲያመልክቱ የተጋበዙት ባለፉት ሶስት ዓመታት ከወሎ ዩኒቨርስቲ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ተዛማጅ ዘርፎች የተመረቁ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ተመራጭ ተማሪዎች በሙያው በተካኑ ባለሙያዎች ቅርብ ክትትል እየታገዙ ስድስት ወር የሚፈጅ ስልጠና ይወስዳሉ፡፡ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አህመዲን ሞሀመድ ተማሪዎቹ በተቋሙ ስለሚያገኙት ስልጠና ምንነት ያስረዳሉ፡፡

“የማይክሮሶፍት APP-Factory አካዳሚ ዋና አላማ አፕልኬሽን መስራት ነው፡፡ [ተማሪዎቹ] ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ አፕልኬሽኖችን እንዲያለሙ ነው የሚፈለገው፡፡ እነዚህ አፕልኬሽኖች በሁሉም ዘርፎች ውስጥ አሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው የሚወጡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እና ኢንዱስትሪው የሚፈልገው ላይ ክፍተት አለ ይባላል፡፡ ስለዚህ ይህን ክፍተት ለመሙላት የእዚህ አይነት ተቋም ከፍቶ በአጭር ጊዜ ማሰልጠን አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው ዓላማው እነዚህን ልጆች አዳዲስ ከሚባሉ የኮዲንግ ወይም የፕሮግራሚንግ አሰራሮች ጋር አለማምዶ ጥሩ የሆነ፣ መሬት ላይ የሚወርድ አፕልኬሽኖችን እንዲሰሩ ነው የሚፈለገው” ይላሉ ዶ/ር አህመዲን፡፡

ዶ/ር አህመዲን “መሬት ላይ የሚወርድ” የሚሉትን ሶፍትዌር እና አፕልኬሽን በቀላሉ ለመረዳት ለዚህ ዙር ስልጠና የተመረጠውን የጤና ዘርፍ መመልከት ይበቃል፡፡ በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የባለሙያዎች ከፍተኛ እጥረት እንዳለ ቀደምት ሙከራዎች ይጠቁማሉ፡፡ መቀመጫውን በአሜሪካ ኒው ኦርሊያንስ ያደረገው ቱሌን ዩኒቨርስቲ እንዲህ አይነት ችግር ከገጠማቸው ተቋማት አንዱ ነው፡፡ ለኮምቦልቻው ተቋም መጠንሰስ ምክንያት የሆነውም ቱሌን ዩኒቨርስቲ በወሎ አቻው ቴክኖሎጂን ከጤና ጋር ለማስተሳሰር ሲሞክር ያጋጠመው እንቅፋት ነው፡፡ በዩኒቨርስቲው ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት እና የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ኃላፊ ዶ/ር ውለታ ለማ ስለ አጀማመሩ ይህን ይላሉ፡፡  

“እኛ ከ40 ዓመት በላይ በትምህርት ጤና ላይ ከኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ጋር ጎንደር፣ ጅማ፣ መቀሌ ሰርተናልም፣ እየሰራንም ነው፡፡ ግን ላለፈው 10 ዓመት ከጤና ጥበቃ [ሚኒስቴር] እና ከ24 ኮሌጆች ጋር ጤናን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሚችሉ ወጣቶችን በተለየ መስክ እያስተማርን ነው፡፡ ግን አንዱ ትልቁ ያስቸገረን ምንድነው? በኮምፒውተር ተመርቀው ከዩኒቨርስቲዎቹ የሚወጡት ልጆች የጤናስ ሶፍትዌር ለመስራት ልምድ የላቸውም፡፡ እና ከወሎ ዩኒቨርስቲ ጋር በጤና ትምህርት ዙሪያ በጣም እንሰራለን፡፡ ከማይክሮሶፍት ጋር በጣም ስለምንሰራ እነሱ ከእኛ ጋር አብረው መጥተው ከኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት ጋር ተነጋገርን፡፡ ያለውን የኮምቦልቻ ፍላጎት አዩ፡፡ በተጨማሪ ኮምቦልቻ በባችለር ዲግሪ በሶፍትዌር ልጆች ያስመርቃሉ፡

ማይክሮሶፍት ከእኛ ጋር በዚህ በሶፍትዌርም በሐርድዌርም ስለሚሰራ ከኮምቦልቻ ጋራ የእነርሱን ተማሪዎች ይዘን ለምን ወደ አንድ ደረጃ አናወጣቸውም? [በሚል ተነጋገርን]፡፡ በተጨማሪም ወጣቶቹ ከኮሌጅ ሲወጡ ጥሩ ተምረው ይወጣሉ ግን [የሚሰሩበትን] ዘርፍ አያውቁትም፡፡ ዘርፉን ብቻ ሳይሆን አዳዲስ የፕሮግራሚንግ ቴክኖሎጂዎችን ስለማያውቁ ለገበያው እንዲሆኑ ለምን አንጀምርም ብለን ማይክሮሶፍትም ተስማማ፡፡ ኮምቦልቻ ተማሪዎችን እያወጣ ስለሆነ እንደ ስራ ላይ ልምምድ ሆኖ ቢጀመር አሁን በጤና ዘርፍ ይሆናል ወደፊት ደግሞ ገበያው እየታየ እርሻ ላይም ሌላ ነገር ላይም ልጆቹ ዘርፎቹን እያወቁ ፕሮግራመር ሲሆኑ የበለጠ ለሀገሪቷ ጥቅም ያላቸው ልጆች እንዲወጡ ነው የጀመርነው” ሲሉ ዶ/ር ውለታ ስለአጠቃላይ ሂደቱ ያስረዳሉ፡፡ 

የማይክሮሶፍት እንዲህ አይነት ተቋም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በአፍሪካ ደግሞ ዘጠነኛው ነው፡፡ ኩባንያው “ማይክሮሶፍት ፎር አፍሪካ” በተሰኘው አቅዱ ከአራት ዓመት ወዲህ አፍሪቃ ዉስጥ በከፈታቸው  ተቋማት 300 የሶፍትዌር ሰሪዎችን አስመርቋል፡፡ በኢትዮጵያም ሰለሞንን ጨምሮ 25 ወጣቶች ስልጠናቸውን ከሶስት ሳምንት በፊት ጀምረዋል፡፡ 

“ትምህርቱን እየሰጡን ያሉት የማይክሮሶፍት ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በፕሮግራሚንግ የተሻለ ደረጃ የደረሱ ናቸው፡፡ ብዙ የማናውቃቸውን ነገሮች አሁን እየመጡ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለምሳሌ azure፣  አሁን ዌብ ሳይት እየተሰራበት ስላለው asp.net እና ራሱን መቀያየር የሚችል ገጽ የመስራት አይነት ነገር እየተማርን ነው፡፡ ከትምህርቱ አኳያ የጠበቅነውን ነው እያገኘን ያለነው” ይላል ሰለሞን፡፡

ሠልጣኞቹ ትምህርቶቹን የሚከታተሉት በኢንተርኔት ነው፡፡ ለየግሎቻቸው በተሰጧቸው ልዩ ማለፊያዎች ተጠቅመው ወደ ማይክሮሶፍት ድረ-ገጾች በመግባት የመማሪያ ቪዲዮዎችን እና ሰነዶችን ወደ ኮምፒውተሮቻቸው ይገለብጣሉ፡፡በየጊዜው የሚያዳብሯቸውን ስራዎች በጋራ የሚያስቀምጡበት ሰርቨርም ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ በየቀኑ በርካታ ሰዓታትን የኢንተርኔት ግንኙነት ባላቸው ኮምፒውተሮች ማሳለፍ ለሚገባቸው ለእነሰለሞን በቅጡ የተደራጀ ቤተ-ሙከራ ግድ ይላል፡፡ ይህ ተሞልቶላቸው እንደው ሰለሞንን ጠይቄው ነበር፡፡

“በጣም የተደራጀ ቤተ-ሙከራ ነው፡፡ ሃያ አምስታችንም በቋሚነት የራሳችን መቀመጫ አለን፡፡ የየራሳችን ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች አሉን፡፡ ወደ ዶርም ሲሄዱ መስራት ለሚፈልጉ ደግሞ ከቱሌን ዩኒቨርስቲ የተገኙ ላፕቶፖች አሉ፡፡ ላፕቶፕ የሌላቸው እነርሱን ይጠቀማሉ፡፡ በተጨማሪ ለማንበቢያ ብቻ የምንገለገልባቸው ኖትቡኮች አሉን፡፡ የኢንተርኔት ግንኙነትም ከግቢው በተለየ ሁኔታ ለሃያ አምስታችንም ብቻ ሌላ ዓይነት ኔትወርክ ተዘርግቶልናል፡፡ መብራት እንኳ አይጠፋብንም” ሲል ያደንቃል፡፡

እነ ሰለሞን መብራት ቢቋረጥ በራሱ ጊዜ በሚነሳ ጄነሬተር ችግሩን ይፈቱታል፡፡ በቅርብ ጊዜ ደጋግሞ እንደታየው ግን የኢንተርኔት ግንኙነት በሰበብ አስባቡ ካናካቴው ይዘጋል፡፡ እንዲህ አይነት የኢንተርኔት መቆራራጥ በስልጠናው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ሰለሞንም ስጋት ያለው ይመስላል።

“ከውጭ በኦንላይን የሚያስተምሩ ሲኖሩ እነርሱን የምንማርባቸው ቪዲዮ ኮንፍረንስ ክፍሎችም አሉን፡፡ ካሜራ የተገጠመለት ጥሩ አዳራሽም ተዘጋጅቶልናል፡፡ ከቴሌ ኔትወርክ መቆራረጥ ካልገጠመ በስተቀር ሁሉም ነገር ተሟልቷል፡፡ የተሻለ የትምህርት ድባብ ሊፈጥሩልን ሞክረዋል፡፡ ምናልባትም ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ቤተ-ሙከራ ላይ ነው ያለነው” ሲል ስለ ኢንስቲትዩቱ አቅርቦት ምስክርነቱን ይሰጣል።

ማይክሮሶፍትን የመሠለ ዓለም አቀፍ  ተቀባይነት ያለው ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቋም መክፈቱ ጥቅሙ ምንድነው? ሶፍትዌር ሰሪዎችን የሚደግፈዉ “አይስ አዲስ” የተሰኘው ድርጅት ስራ አስኪያጅ እና መስራች ማርቆስ ለማ አጭር መልስ አለዉ።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ዩኒቨርስቲዎች የግሎቹን ጨምሮ አይተሃቸው ከሆነ መጀመሪያ ላይ ገና አዲስ የትምህርት ክፍል ሲከፈት ብዙ ጊዜ ኮምፒውተር ሳይንስ የትምህርት ክፍል ነው የሚከፈተው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ከሚጠይቀው ግብዓት አንጻር ኮምፒውተር ሳይንስ ማስተማር ቀላል ከሚባሉ ሳይንሶች ውስጥ አንደኛው ስለሆነ ነው፡፡ ግን ከኮምፒውተር ሳይንስ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተዛማጅ በሆኑ ዘርፎች ከሚማረው እና ከሚመረቀው አንጻር ስታየው ስራው ላይ ያለው ተጽእኖ [አነስተኛ ነው]፡፡ ካለው የሰው ኃይል አንጻር ከኢትዮጵያ የሚወጡ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው፣ ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ ምርቶች በጣም ውስን ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁን እንደዚህ የማይክሮሶፍት APP-Factory አይነት ወይም ከጎግል ጋር የተገናኘ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ከዩኒቨርስቲ የሚወጣው ክህሎት እንዲጨምር እና ገበያ ላይ ያለውን ደረጃ የሚያሟሉ ልጆችን ለማግኘት ይረዳናል” ሲል በዘርፉ የታዘበውን ያካፍላል።

በጎረቤት ኬንያ እንደ M-Pesa እና Ushahidi አይነት ዓለም አቀፍ ደረጃን ጠብቀው የተሰሩ የሶፍትዌር ምርቶች እንዳሉ በምሳሌነት የሚያነሳው ማርቆስ ከእነርሱ ጋር የሚስተካከሉ ከኢትዮጵያ የወጡ ምርቶች እንደሌሉ ያስረዳል፡፡ ዋናው ችግሩ ጥራት እንደሆነም ይገልጻል፡፡ የእንደዚህ አይነት ተቋማት መከፈት ከብዛት ይልቅ ለጥራት ትኩረት ለመስጠት ያግዛል ይላል፡፡ የማርቆስን አባባል የኮምቦልቻው ሰልጣኝ ሰለሞንም በከፊል ይጋራዋል፡፡ በየዩኒቨርስቲዎቹ የሚሰጠው ትምህርት “ወደፊት ከዓለም ጋር ላያወዳድረን ይችላል” የሚል ዕምነት አለው፡፡ 

እርሱና የክፍል ተጋሪዎቹ በማይክሮሶፍት ተቋም ስልጠና መውሰድ ከጀመሩ በኋላ ከዓለም ጋር ለመወዳደር “ወደ መንገዱ እየገቡ እንደሆነ“ ይሰማዋል፡፡ ማይክሮሶፍትን የሚያህል ትልቅ ኩባንያ እውቀት ለማጋራት ወደ ኢትዮጵያ መዝለቁ ብቻ ሳይሆን የመረጠውም ቦታ የሚያስመስግነው እንደሆነ ይናገራል፡፡ ቀደም ሲል እንዲህ አይነት ዕድሎች በአዲስ አበባ ዙሪያ መታጠራቸውን የታዘበው ሰለሞን “ብዙ ነገሮች መሀል ከተማ ላይ ይቀሩና ወደ ክልል ያሉት ብዙ ነገሮች ይበደላሉ” ይላል፡፡ ማይክሮሶፍት ለጅማሬው ኮምቦልቻን መርጧል፡፡ እነጉግል ማረፊያቸው የት እንደሚሆን ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic