የማይራመደዉ የደቡብ ሱዳን ድርድር | አፍሪቃ | DW | 01.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የማይራመደዉ የደቡብ ሱዳን ድርድር

የደቡብ ሱዳን መንግስትና አማፂያን አቋርጠዉት የነበረዉን የሰላም ንግግር የፊታችን ሳምንት እንደሚጀምሩ አደራዳሪዎች አስታዉቀዋል። የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ማለትም IGAD አደራዳሪዎች ዛሬ እንደገለጹት በያዝነዉ ሳምንት ይጀመራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረዉ የሁለቱ ወገኖች የሰላም ንግግር የፊታችን ሰኞ ይጀመራል።

IGAD እንደሚለዉ ድርድሩ የተጓተተዉ በተራዘመ የእረፍት ጊዜ ምክንያት ነዉ። ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ዉጊያዉ የሚቀጥል ከሆነ በሳምንታት ዉስጥ ሀገሪቱ ለከፋ ረሃብ ልትጋለጥ ትችላለች የሚለዉ ማስጠንቀቂያም እየተሰማ ነዉ።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር እና የቀድሞ ምክትላቸዉ የነበሩትና የአማፅያኑ መሪ ሪክ ማቻር ለሀገሪቱ ሰላም ያመጣል የተባለዉ ባለፈዉ ወር የተካሄደዉ ዉይይት አስተጓጉሏል በሚል አንዳቸዉ ሌላቸዉን ይከሳሉ። በሁለቱ መካከል የተነሳዉ አለመግባባት በዉይይት ሳይፈታ ቀርቶ አድጎ ጎራ አለያይቶ ነፍጥ ካማዘዘ ጥይት ማታኮስ ካስጀመረ ሰባት ወራት ነጉደዋል። በጎሳ የተቧደኑት የመንግስት ወታደሮችና ሚሊሺያዎች ባካሄዱት ጦርነትም በሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል። ከ1,5 ሚሊዮን የሚበልጡት ደግሞ የዉጊያዉ ሽሽት ለስደት ተዳርገዋል። የልዩነት ጦሳቸዉ ለምስኪኑ ዜጋ የተረፈዉ የሀገሪቱ አንጋፋ የፖለቲካ ሰዎች አዲስ አበባ ላይ ሰላም ያወርዳሉ በሚል በተቀናጣ ሆቴል ንግግርና ድርድር ላካሄዱት 12 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 17 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መፍጀቱ የፈረንሳይ የዜና ወኪል ይፋ አድርጎታል። ከዉይይቱ ግን እስካሁን ከቃልና ተስፋ የዘለለ ጠብ ያለ መፍትሄ የለም። ሶስት ጊዜ ተስማማን ያሉት የተኩስ አቁም እንደሁ አልተከበረም። ቢልላቸዉ ኖሮ መሪዎቿ ተባብረዉ ተፈጥሮ የለገሠቻቸዉን የነዳጅ ሃብት ክምችት ለፈላጊዎቹ እያቀረቡ ለዓመታት በጦርነትና ስደት ለተሰቃየዉ የደቡብ ሱዳን ህዝብ የተሻለ ኑሮ በቀየሱ ነበር። አሁን ግን የነዳጅ ዘይቱ ያለበት አካባቢ የጦርነት አዉድማ መሆኑ ነዉ የሚነገረዉ።

ደቡብ ሱዳን ከሰሃራ በስደተቡብ ከሚገኙ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ሃብት ካላቸዉ ሃገራት በሶስተኛ ደረጃ ትገኛለች። ለሰላም ድርድሩ ቅርበት ያላቸዉ አንድ ምዕራባዊ ዲፕሎማት የነዳጅ ክምችቱን በበላይነት የመቆጣጠር ጥያቄ ለንግግሩ እንቅፋት ከሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል። ዉጊያዉ የነዳጅ ማምረቱን ተግባር በአንድ ሶስተኛ እጅ ቀንሶታል። እንዲያም ሆኖ ዉጊያዉ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነዳጅ ድፍድፍ በመሸጥም ሆነ እሱን አስይዞ ገንዘብ በመበደር የፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር መንግስት ዋነኛ ገቢነቱ አልተለወጠም። ተቺዎች ብድሩ ድሃይቱን ሀገር ጨርሶ ወደታች እያስጎነበሳት ነዉ ይላሉ። የአማፅያኑ መሪ ማቻር የነዳጅ ሃብቱን ገለልተኛ አካል እንዲቆጣጠር ካልተደረገ የጥቃት ዒላማ ከመሆን እንደማያመልጥ ግልፅ አድርገዋል። ደቡብ ሱዳን ዉስጥ የአማፅያን ኃይሎች ይገኙበታል በሚባለዉ አካባቢ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2009ዓ,ም አንስቶ የሚገኙት ጀርመናዊ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ግሪጎር ሽሚት የእሳቸዉ ሃገረ ስብከት የሚገኝበት የጆንግሌ ግዛት ከሌሎቹ የተነጠ በመሆኑ በእርስ በርስ ጦርነቱ ባይጎዳም ከአጎራባች ግዛቶች በርካታ ተፈናቃዮች ወደእነሱ እንደሚመጡ ነዉ የሚገልጹት፤

«የእኛ ተልዕኮ የሚገኘዉ ፋንጋ ወረዳ ማለትም የጆንግሌ ግዛት ሰሜን ምዕራብ ጥግ ላይ በምትገኘዉ ስፍራ ነዉ። ወደኛ ወረዳ የሚወስዱ መንገዶች የሉም። ሆኖም ነጋዴዎች ሸቀጣ ሸቀጥ የሚያመላልሱበት አባይን ተከትሎ የተዘረጋ መሸጋገሪያ አለ። ትንሽ ገበያም ኣለችን። ከዚህ ሌላ ወረዳዉ እንዳለ የተገለለ ነዉ። በዚህ ምክንያትም እንደእድል ሆኖ የእርስ በርሱ ጦርነት አካባቢያችን አልደረሰም። ሆኖም በአካባቢችን በሚገኙት ስፍራዎች ግን ዉጊያ ነበር ሰዎች ተፈናቅለዋል። ብዙዎቹም ወደእኛ አካባቢ መጥተዋል።»

Südsudan Father Gregor Schmidt

ቄስ ሽሚት

ቄስ ሽሚት እንደሚሉት ምን እንኳን የእነሱ አካባቢ ሰላማዊ ቢመስልም ከአባይ ወንዝ በስተ ሰሜን በኩል ያለዉ እነሱ የሚገኙበት ወረዳ ዋና ከተማ ግን አንዳንዴ በመንግስት ሌላ ጊዜ በአማፅያን ስለሚያዝ ለጥቃት ተጋልጦ ወደ40 ሺ ሰዎች እንዲሰደዱ ሆኗል። እሳቸዉ እደሚሉትም መሸጋገሪያ የሌለበት በወንዝ የተከበበ መሆኑ አካባቢዉን ከጥቃት አድኖታል። በአካባቢዉ የሚገኙት የኑየር ጎሳ አባልት ሲሆኑ ሁሉም ፕሬዝደንት ኪር ስልጣን ይለቃሉ የሚል ተስፋ አላቸዉ። ሰላማዊዉን ዜጋ ከአማፅያኑ መለየት አዳጋችም ነዉ ይላሉ።

«በዚህ ግጭት ተራዉኑ ኗሪና አማፅያኑን መለየት በጣም አስቸጋሪ ነዉ። ምክንያቱም ሲቪሎቹንና ተዋጊዎቹን መለየት አዳጋች ነዉ በእኛ እይታ። አርብቶ አደሮች እንደመሆናቸዉ ሁሉም መሣሪያ የያዙ ናቸዉ ምክንያቱም ከብቶቻቸዉን ከዘራፊዎች የሚከላከሉት በዚያ ነዉ። በየዓመቱም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሞቱባቸዉ በጎሳዎች መካከል ግጭት ይካሄዳል። ከዚህ የእርስ በርስ ጦርነት በፊትም ቢሆን ሰላማዊ የሆነ ወቅት አልፎ አይታወቅም።»

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic