የማያንማር ምርጫ | ዓለም | DW | 09.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የማያንማር ምርጫ

የምርጫ አስፈፃሚው አካል ውጤቱን በይፋ ለመግለፅ ጥቂት ቀናት ሊወስድበት እንደሚችል ቢታወቅም የወይዘሮ አውን ሳን ሱቺ ቃል አቀባይ እንዳስታወቁት ግን ፓርቲያቸው አሸናፊነቱ ተረጋግጧል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:09

የማያንማር ምርጫ

ትናንት ማይንማር ዉስጥ ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ በተካሄደና ታሪካዊ በተባለለት አጠቃላይ ምርጫ የኖቤል የሰላም ተሸላሚዋ ወይዘሮ ኦንግ ሳን ሱ ቺ የሚመሩት ተቃዋሚው ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ሊግ አብላጫ ድምፅ ማግኘቱን ዛሬ አስታወቀ ። በመጀመሪያ የምርጫ ዉጤቶች መሠረትም ተቃዋሚዉ ብሔራዊ የዴሞክራሲ ሊግ በሀገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር እስከዛሬ እኩለ ቀን ድረስ ከአጠቃላዩ ድምጽ ሰባ ከመቶዉን መዉሰዱን የፓርቲዉ ቃል አቀባይ ዊን አታይን ገልጸዋል።

ዘገባዎች እንደሚሉት ግን የምርጫ ጉዳይ ባለስልጣናት ይፋ ያደረጉት ከዉጤቱ በጣም ጥቂቱን ነዉ። 70 ዓመቷ ታዋቂ ፖለቲከኛ ሱቺ ደጋፊዎች ገና በመጀመሪያዎቹ የምርጫ ዉጤቶች ከወዲሁ ተስፋ እና ደስታቸዉን መግለፅ ጀምረዋል።

«ሁኔታዎች ይለወጣሉ። እናት ለሀገሪቱ የተቻላትን ታደርጋለች።»

«በጣም ደስ ብሎኛል። እንደሰማሁት ብሄራዊ የዴሞክራሲ ሊግ እያሸነፈ ነዉ። ትናንት ማታ እስከሌሊቱ አምስት እና ስድስት ሰዓት መተኛት አልቻልኩም ነበር። ከየአካባቢዉ የሚመጡ ዉጤቶችን ስመለከት ነበር።» እሳቸዉ የሚሉት ዉጤት በምርጫ ባለስልጣናት የሚረጋገጥ ከሆነም ተቃዋሚዉ ፓርቲ የምክር ቤት መቀመጫዎችን ብቻ ሳይሆን የፕሬዝደንትነቱንም ስፍራ ሳይዝ እንደማይቀር እየተነገረ ነዉ። ሱቺ ደጋፊዎቻቸዉ የተሸናፊዉን ፓርቲ ደጋፊዎች እንዳይተናኮሉ አሳስበዋል።

«ሁሉንም ሌላዉ ቀርቶ በምርጫዉ ያላሸነፉ እጩዎችም ቢሆኑ አሸናፊዎቹን መቀበል እንደሚኖርባቸዉ ላስገነዝብ እፈልጋለሁ። ሆኖም ግን ያላሸነፉት መጥፎ ስሜት እንዲሰማቸዉ የሚያደርግ ትንኮሳ አለማድረጉ እጅግ ጠቃሚ ጉዳይ ነዉ።»የምርጫ አስፈፃሚው አካል ውጤቱን በይፋ ለመግለፅ ጥቂት ቀናት ሊወስድበት እንደሚችል ቢታወቅም የወይዘሮ ኦንግ ሳን ሱ ቺ ቃል አቀባይ እንዳስታወቁት ግን ፓርቲያቸው አሸናፊነቱ ተረጋግጧል። በወታደሩ የሚደገፈው ገዥው ፓርቲ የተሸነፈ መሆኑን የሚገልጡ መረጃዎች እየወጡ ነው። የገዥው ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት በተወዳደሩበት የምርጫ ጣቢያ መሸነፋቸውን አምነው የምርጫውን ውጤት ያለምንም ማቅማማት እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል ።ለዝርዝሩ ገበያው ንጉሴ

ገበያው ንጉሴ

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic