የማያባራው የስደተኞች እልቂት በሜድትራኒያን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 07.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የማያባራው የስደተኞች እልቂት በሜድትራኒያን

በርካታ ስደተኞች አሳፍራ ከሊቢያ ወደ አውሮጳ በሜድትራኒያን ባህር ላይ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ሰጥማ ከ200 በላይ ስደተኞች ሳይሞቱ አልቀረም ተባለ። ባለፈረዉ ሮብ የሰጠሙ ስደተኞችን ለማግኘት የአደጋ ሠራተኞች ፍለጋ በማካሄድ ላይ ሲሆኑ ከአደጋው የተረፉት መንገደኞች ወደ ጣልያኗ ፓሌርሞ ተወስደዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:39

የማያባራው የስደተኞች እልቂት በሜድትራኒያን

ከስድስት መቶ በላይ ስደተኞችን አሳፍራ ከሊቢያ ወደ አውሮጳ በመሻገር ላይ ሳለች የመስጠም አደጋ ከገጠማት ጀልባ ውስጥ ለጊዜው በህይወት የተገኙት አራት መቶ ብቻ ናቸው። እስካሁን የ25 ስደተኞች መሞት የተረጋገጠ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል እንደሚጠበቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። የሟቾች አስከሬን ወደ ጣሊያን የወደብ ከተማ ሲሲሊ መወሰዱ ተዘግቧል። በዚህች ጀልባ ተሳፍረው የሜድትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ወደ አውሮጳ ለመሻገር ሲሞክሩ አደጋ የገጠማቸውና በነፍስ አድን ሰራተኞች ከሞት ያመለጡትም ጤናቸው መልካም አይደለም። ስደተኞቹን የመታደግ ስራ በመከወን ላይ የሚገኘው ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን የጀርመን ቢሮ ሃላፊ ፍሎሪያን ቬስትፋል ስደተኞቹ አካላዊ ብቻ ሳይሆን ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ እንደሚያሻቸው ይናገራሉ።

«በሜድትራኒያን ባህርን በሚያቆርጡት ጀልባዎች ላይ ካገኘናቸው ሰዎች አብዛኞቹ የሰውነት ፈሳሻቸውን ቀንሷል። የባህር በሽታም ይዟቸዋል። አንዳንዶቹ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። ብዙዎቹ በሊቢያ በደረሰባቸው ጭቆናና ግርፋት ሰቀቀን ውስጥ ናቸው። አንዳንዶቹ የመንፈስ ሰቆቃ ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ አካላዊ ብቻ ሳይሆን ስነ-ልቦናዊ ድጋፍም ያሻቸዋል። በጀልባ ላይ ሳሉ ብቻ ሳይሆን በሲሲሉ ከደረሱ በኋላ አስፈላጊውን እገዛ እያደረግንላቸው ነው።»

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የደረሰው አደጋ 1,000 ስደተኞች በሚያዝያ ወር በአንድ ሳምንት ከሞቱ በኋላ ትልቁ መሆኑ ነው። ከሊቢያ ወደብ ከስድስት መቶ በላይ ስደተኞችን ጭና ወደ አውሮጳ በመጓዝ ላይ የነበረችው ጀልባ ስትስጥም የሞቱት ሰዎች ቁጥር አሁንም በውል አልታወቀም። በነፍስ አድን ስራው ላይ የተሰማሩት የአየር ላንድ ባህር ሃይልም ሆነ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ስጋት አላቸው። ፍሎሪያን ቬስትፋል 28 አባል ሃገራት ያሉት የአውሮጳ ህብረት የስደተኞቹን ህይወት ለመታደግ የሚያደርገው ጥረት መሻሻል ቢያሳይም በቂ ግን እንዳልሆነ ይናገራሉ።

«አሁን ከተከሰተው አደጋ የምንረዳው የፍለጋና ነፍስ አድን ስራው በቂ አለመሆኑን ነው። ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ መሻሻል ቢኖርም መሻሻሉ ዝቅተኛ ነው። ከግንቦት በፊት በተግባር ምንም አይነት ጥረት አልነበረም። አሁን በአካባቢው በርካታ መርከቦች ተሰማርተዋል። ይሁንና እንደአለመታደል ሆኖ በሚያሳዝን ሁኔታ በቂ አልሆነም።»

በጀልባዋ የተሳፈሩ ስደተኞች የነፍስ አድን መርከብ ተመልክተው ወደ አንድ ጎን በመሰብሰባቸው ጀልባዋ ሚዛኗን በመሳት የመገልበጥ አደጋ ገጥሟታል ተብሏል። በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት መረጃ መሰረት በዚህ አመት ብቻ 2000 በላይ ስደተኞች የሜድትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ወደ አውሮጳ ለመሻገር ሲሞክሩ ህይወታቸውን አጥተዋል።

የአውሮጳ ህብረት አባል አገራት የስደተኞቹን ነፍስ ለመታደግ የሚያደርጉት ጥረት አነስተኛ ነው እየተባለ በተደጋጋሚ ወቀሳ ይሰነዘራል። ከ40-50 ሰዎች ብቻ የመጫን አቅም ባላቸው ጀልባዎች ከመጠን በላይ ታጭቀው ወደ አውሮጳ ለመሻገር ከሚሞክሩትም ሆነ ህይወታቸውን ከሚጡት ስደተኞች መካከል አፍሪቃውያን በብዛት ይገኛሉ። የአፍሪቃ መሪዎችና መንግስታት ጉዳዩን ለአውሮጳ አገራት በመተው ችላ ያሉት ይመስላል። በጉዳዩ ላይ በዶይቼ ቨሌ የፌስቡክ ማህበራዊ ድረ-ገጽ አስተያየታቸውን የሰጡ ኢትዮጵያውያን የአፍሪቃውያን ፖለቲከኞችን ለችግሩ ተጠያቂ ያደርጋሉ። አብይ አውቶፓርኮ የተባሉ የማህበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚ የአፍሪቃ መሪዎች ለችግሩ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ «ህዝቡ ምን ሰርቶ ምን በልቶ አደረ ሳይሆን ምን እያሴረነዉ በሚል የስልጣን ዘመናቸዉን ለማርዘም ነዉ።» ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። «ከአመት አመት እጅግ አስደንጋጭ የሆነስ ደት ነው በአፍሪካ የምናየው» የሚሉት አሰፋ አዘነ የተባሉ የማህበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚ «አፍሪካዊያን መሪዎች የተወሠኑ ሐብታሞችን ይዘው እድገት እድገት ከማለት ውጭ ብዙሃኑን ያማከለ ዕድገት አይታይም።ለዚያም ነው አፍሪካውያን በተለይ ወጣቱ የበይ ተመልካች ስለሆነ ነው ስደትን የመረጠው።» ሲሉ ተችተዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic