የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጊዚያዊ ሁኔታ | አፍሪቃ | DW | 26.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጊዚያዊ ሁኔታ

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውዝግብ እየተባባሰ ሄዶ በሀገሪቱ ምስቅልቅሉ ሁኔታ እና ሥርዓተ አልባነት ተስፋፍቶዋል። ሕዝቡ፣ በተለይ ሴቶች እና ሕፃናት ለቀድሞ የሴሌካ እና ለሌሎች ዓማፅያን ቡድኖች ጥቃት ተጋልጦዋል።

ሀገሪቱ ወደ ጅምላ ጭፍጨፋ የምታመራበት ስጋት መደቀኑንም ነው ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ እያስጠነቀቀ ያለው። ይህንንም ተከትሎ አንድ ከፍተኛ የተመድ ባለሥልጣን በማዕከላይ አፍሪቃ የሚገኘው የአፍሪቃ ህብረት ጓድ ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሴሌካ ዓማፅያን ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የቀድሞ የሀገሪቱን ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ቦዚዜን በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ካስወገዱ በኋላ በሀገሪቱ በሚሼል ጆቶጂያ የሚመራ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞዋል። የታጠቁ፣ በብዛት ሙሥሊሞች የሆኑ የቀድሞዎቹ ያማፅያን ቡድኖች ብዙውን የሀገሪቱን ከፊል ተቆጣጥረዋል።

እርግጥ፣ ከሽግግሩ መንግሥት ምሥረታ በኋላ የሀገሪቱ መሪ ሚሼል ጆቶጂያ ያማፀያኑን ቡድንኖች በመበተን በብሔራዊው ጦር ውስጥ ቢያዋህዱም፣ ከሴሌካ ዓማፅያን ጋ ግንኙነት የነበራቸው ቡድኖች አሁንም በርካታ መንደሮችን እያጠቁ ሲቭሉን ሕዝብ በማሸበር ላይ እንደሚገኙ ተገልጾዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ፣ ሂውማን ራይትስ ዎች ባልደረባ የቡድኑን ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን አስጠንቅቋል።
« ሂውማን ራይትስ ዎች የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያን በርካታ አስከፊ ወንጀሎችን መፈፀማቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ሰብስቦዋል። በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች፣ መዲናዋን ባነግዊን ጨምሮ የሚገኙት እነዚሁ ዓማፅያን ባሁኑ ጊዜ ከቁጥጥር ውጭ ሆነዋል። በመጨረሻ የመዘገብነው አሰከፊ ወንጀል በጋጋ አካባቢ፣ ኦምቤላምቦኮ በተባለ መንደር ሲሆን በዚያ የሴሌካ ዓማፅያን በመንደሩ ላይ ጥቃትበመሰነዘር በነዋሪዎቹ ላይ እጅግ አስከፊ ወንጀል ፈፅመዋል። »
በባንግዊ የሚገኘው የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ሽግግር መንግሥት በሀገሩ እየተባባሰ የመጣው ውዝግብ እንዲያበቃ እና ለሲቭሉ ሕዝብ ጥበቃ እስካሁን ያደረገው ጥረት በቂ ሆኖ አልተገኘም፣ እንዲያውም አቅም አልባ መሆኑን ነው የገለጹት።
« አዲሶቹ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ባለሥልጣናት አንድም በአቅም መጓደል ይሁን በፍላጎት እጦት የተነሳ ሁኔታውን በሚገባ መቆጣጠር አልቻሉም። እነዚህ ሕዝቡን የሚያሸብሩትን የተለያዩ ቡድኖችን ማን እንደሚቆጣጠር በርግጥ አይታወቅም። እና እኛ እያልን ያለነው በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ አሁን ዓማፀያኑ እየፈፀሙት ያለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ለፕሬዚደንት ጆቶጂያ ይህንኑ አስከፊ በደል ለማስቆም ቆርጠው መነሳታቸውን ለማሳየት የሚፈተኑበት ጥሩ አጋጣሚ ነው። »
እንደ ሂውመን ራይትስ ዎች፣ መንግሥት ተጠያቂዎቹን ይዞ ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።
ይኸው ሁኔታ ያሳሰባቸው የተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ ጃን ኤሊያሰን ባማፅያኑ ጥቃት በተለይ ሴቶች እና ሕፃናት መጎዳታቸውን በማስታወቅ ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ አንድ ርምጃ ካልወሰደ ሁኔታው የከፋ ሊሆን፣ ብሎም ወደ ሀይማኖት እና ጎሳ ግጭት ሊቀየር እና ወደሌሎች አካባቢዎችም ሊስፋፋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ኤልያሰን በመቀጠልም የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ያለውን የአፍሪቃ ህብረት ጓድ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የቀድሞ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይም ለጓዱ ማጠናከሪያ 1000 ወታደሮች ላጭር ጊዜ እንደምትልክ የመከላከያ ሚንስትር ዣን ኢቭ ለ ድሪዮን ገልጸዋል። ፈረንሳይ በወቅቱ 400 ወታደሮች በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ አሰማርታለች።

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic