የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተልኮ | አፍሪቃ | DW | 29.01.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተልኮ

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የአውሮፓ ህብረት ወታደሮች ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ እንዲዘምቱ የሚፈቅደውንና ደም አፋሳሽ ብጥብጥ እንዲካሄድ ያደረጉ የቡድን መሪዎች ላይ ማዕቀቦች እንደሚጣል የሚያስጠነቅቀውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ትናንት ማፅደቁን አሳውቋል ።

15 ሀገራትን ያቀፈው ምክር ቤት በፈረንሳይ ተረቆ የቀረበውን የአውሮፓ ህብረት የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል። ረቂቁም በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ አስፈላጊን ርምጃ ለመውሰድ ያስችላል። ሀገሪቱ ላለፉት 10 ወራት በአማፂያን እጅ ወድቃ ትገኛለች። የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ሳምንት እንደተስማማው ወደ 600 የሚሆኑ የአውሮፓ ህብረት ወታደሮች ወደ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ለመላክ ተስማምቷል። በስፍራውም 3500 ለሚሆኑት የአፍሪቃ ህብረት ወታደሮችን እና በሀገሪቱ ለሚገኙት 1600 የፈረንሳይ ወታደሮች ድጋፍ ይሰጣሉ። የተባበሩት መንግሥታት የፈረንሳይ አምባሳደር ጌራርድ አራውድ እንደሚሉት ይህ ውሳኔ በሀገሪቱ ሰላም በማስከበሩ ረገድ የመጀመሪያው አንድ ርምጃ ነው።

« እንደምታውቁት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው ሳምንት በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የአውሮፓ ህብረት ተልኮ ለማድረግ ወስነዋል። በዚህም ተልኮ ሚሳ በመባል የሚታወቀው የአፍሪቃ ህብረት ኃይልና እና የፈረንሳዩን ልዑክ ኃይል ሳንጋሪን ይተባበራሉ። ያፀደቅነው ስምምነት የአውሮፓ ህብረት ተልኮን በምዕራፍ 7 መሰረት ውክልና ይሰጣል። ይህ ተልኮ ማለትም ከፈረንሳይ እና ከአፍሪቃ ህብረት ባሻገር የሰብዓዊ ርዳታዎችን ተደራሽ ያደርጋል፣ የሲቪሉን ማህበረሰብ ደህንነት ያስከብራል፣ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም የኃይል ርምጃ ይወስዳል። የ2134ቱ ስምምነት በፖለቲካዊ ረገድ የሽግግሩን መንግሥት ስራ ማፋጠን ይኖርበታል። ከተቻለ በሁለተኛው የዓመቱ አጋማሽ ምርጫው እንዲካሄድ ማለት ነው። »

Zentral Afrikanische Republik UN Truppen nach Bangui

በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ

አምባሳደሩ እንደገለፁት የአውሮፓ ህብረቱ የጦር ኃይል የባንግዊ የአየር ማረፊያን ይጠብቃል። በአሁኑ ሰዓት በአየር ማረፊያውም ብቻ 100 000 የሚደርሱ ሰላማዊ ሰዎች ተጠልለው ይገኛሉ። በአጠቃላይ 900 000 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ምናልባትም በሀገሪቷ ሰላም ለማስከበር ቢያንስ 10 000 ወታደሮች አስፈላጊ ናቸው ባይ ናቸው አምባሳደሩ። በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሰብዓዊ መብት ተማጋጅ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ቨርጅኒ ዴሮ ተጨማሪ ወታደር በማስፈለጉ ይስማማሉ። ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ ፤ ሁሉ ነገር ከቁጥጥራቸው ውጪ ነው።

« አሁን ባለንበት ቀውስ ያሉት የሳንጋሪ እና የሚሳ ኃይሎች ያለውን ሰላም እንኳን ማስከበር አልቻሉም። ተጨማሪ ወታደሮች ያስፈልጉናል። ለምሳሌ ከባንጉይ 600 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘው የካቡን ከተማ ብንወስድ፤ ባንጉይ የሚገኙት የሳንጋሪና እና ሚሳ ኃይሎች እዚያ የሉም። እስካሁን ድረስ በሴሌካም ይሁን በፀረ ባላካ አማፅያን የከተማዋ ነዋሪዎች በታጣቂዎች ተጨቁነዋል። እና ህብረተሰቡ ታግቷል።»

ሚሳ በመባል የሚታወቀው የአፍሪቃ ህብረት አረጋጊ ሀይል ስራውን በአግባቡ እንዲያከናውን ቢያንስ የአንድ ዓመት ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ባን ኪ ሙን የአለም አቀፉ ጦር ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክን ለመርዳት በሚያደርገው ጥረት ስለሚኖረው ቀጣይ ርምጃ በየካቲት ወር መጨረሻ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic