የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ቀዉስ | አፍሪቃ | DW | 30.12.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ቀዉስ

የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት ፍራንሲዝ ቦዚዚ ከአማፂያን መሪዎች ጋር ስልጣናቸውን መጋራት እንደሚሹ እሁድ ገለፁ። በሌላ በኩል አማፂያኑ ዋና ከተማዋን ለመቆጣጠር ጥቂት ኪሎ ሜትሮች እንደቀራቸው እየተነገረ ነው።

የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የመንግስት ባለስልጣን አማፂያን ለዋና ከተማዋ ባንጉዊ የምትቀርብ አንድ ሌላ ከተማ መቆጣጠራቸውን ማረጋገጫ ሰጥተዋል። አማፂያኑ የተቆጣጠሯት ከተማ ሲቡት ስትሰኝ ከባንጉዊ 185 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ናት። የድንበር አስተዳደር ሚንስትሩ ጆዜ ቢኖዋ አማፂያኑ ሲቡትን የተቆጣጠሩት ትናንት መሆኑን አክለው ጠቅሰዋል። የቻድ ጦር ሠራዊት ከማዕከላዊ መንግስት ጋር በሲቡት የሰፈረ ቢሆንም የመከላከያ ሀይሉ ከዋና ከተማዋ 75 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ዳማራ አርብ ዕለት በማፈግፈጉ አማፂያኑ ሲቡትን የተቆጣጠሩት ያለምንም ውጊያ እንደነበር ተዘግቧል። ወደ ሲቡት የሚያልፉ የስልክ መስመሮች የተቆራረጡ ሲሆን፤ ሁኔታውን በአካባቢው ሰዎች ለማጣራት አስቸጋሪ አድርጎታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአካባቢው የአፍሪቃ ሀገራት፤ ፕሬዚዳንት ፍራንሲዝ ቦዚዚን ለመርዳት ተጨማሪ ጦር ለመላክ ተስማምተዋል። ፕሬዚዳንት ቦዚዚ ሴሌካ ከተሰኘው የአማፂያን ቡድን ጋር ጣምራ መንግስት ለማቋቋም ፈቃደኛ መሆናቸውን እና ከሦስት ዓመታት በኋላ በሚካሄደው ዳግም ምርጫ እንደማይሳተፉም ገልፀዋል። የአካባቢው ሀገራት መሪዎች በአማፂያን እና በቦዚዚ መንግስት መካከል ጋቦን ውስጥ በሚያዘጋጁት የሠላም ንግግር ፕሬዚዳንቱ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታና መዘግየት ለመሳተፍ ፈቃደኛ እንደነበሩም ጠቅሰዋል። አማፂያኑ በበኩላቸው የፕሬዚዳንቱን ጥሪ የሚመለከቱት መሆኑን ሆኖም አሁን ካለው መንግስት ጋር መጣመር እንደማይፈልጉ በቃል አቀባያቸው በኩል ገልፀዋል። በሌላ በኩል በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ሴሌካ የተሰኘዉ አማፂ ቡድን ወደ ዋና ከተማዋ ግስጋሴዉን በመቀጠሉ ፈረንሳይ በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ያላትን የጦር ሃይል ማጠናከርዋ ተገልጾአል። በዚህም በጋቦን ሰፍረዉ የነበሩ 150 የፈረንሳይ አየር ወለድ ወታደሮች ዉጥረት በነገሰባት በማዕከላዊትዋ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ከሚገኙት የፈረንሳይ ወታደሮች ጋር መቀላቀላቸዉ ነዉ የተነገረዉ። በፓሪስ የሚገኘዉ የፈረንሳይ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀዉ ይህ የሆነዉ በአካባቢዉ የሚኖሩትን ፈረንሳዉያንን እና የአዉሮጳ ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ነዉ።

ፕሬዚደንት ፍራንሲዝ ቦዚዚ

ፕሬዚደንት ፍራንሲዝ ቦዚዚ

ከጋቦን ወደ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ የገቡት 150 የፈረንሳይ አየር ወለዶች በዋና መዲናዋ በሚገኘዉ የአየር ማረፍያ አጠገብ በሚገኘዉ ወታደራዊ ማዕከል በመስፈር እዝያዉ የነበሩትን 250 የፈረንሳይ ወታደሮች ይደግፋሉ። ዩናይትድ ስቴትስ በዋና ከተማ ባንጉዊይ የሚገኝዉን ኤምባሲዋን በመዝጋት ዴፕሎማቶችዋን እና ሌሎች የዉጭ ዜጎችን ማስወጣትዋ ይታወቃል። አማፅያኑ ከሁለት ሳምንት በፊት በትጥቅ ትግል ፕሬዝደንት ፍራንሲዝ ቦዚዚን በመቃወም እንቅስቃሴያቸዉን መጀመራቸዉ ይታወሳል። የመካከለኛዉ አፍሪቃ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ECCAS በበኩሉ፤ በአማፅያን እና በመንግስት መካከል የተነሳዉን ተኩስ ለማስቆም ጥረት ላይ መሆኑ ተነግሮአል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

 • ቀን 30.12.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17BQ1
 • ቀን 30.12.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17BQ1