የማዕከላዊ መዘጋት እና «ደረጃዉን የጠበቀ» የምርመራ ተቋም  | ኢትዮጵያ | DW | 04.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የማዕከላዊ መዘጋት እና «ደረጃዉን የጠበቀ» የምርመራ ተቋም 

በትናንትናዉ ዕለት ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መንግሥት "በደርግ ዘመን በምርመራ ስም ልዩ የጭካኔ ተግባር ሲፈጸምበት የነበረ» ያሉትን ማዕከላዊ ዘግቶ «ዓለም አቀፍ ደረጃዉን የጠበቀ» ያለዉን የምርመራ ተቋም እንደሚያቋቋም ተናግረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:04

ማዕከላዊ መዝጋት

አቶ ታዬ ዳንዳኣ በ1996 ዓ/ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪ በነበሩበት ወቅት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ከፍኒፍኔ ወደ አዳማ መዛወር በመቃወም ለሦስት ዓመት መታሠራቸዉን ይናገራሉ። በድጋሚም በ2001 ዓ/ም እንዲሁ በፖለቲካ ጉዳይ ተጠርጥረዉ ለሰባት ዓመታት ከታሰሩ በዋኋ ግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ/ም በነፃ ተለቅቀዉ፣ የሕግ ዲግሪያቸዉን ባለፈዉ ዓመት መዉሰዳቸዉንም ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

በትናንትናዉ ዕለት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መንግሥታቸዉ «በደርግ ዘመን በምርመራ ስም ልዩ የጭካኔ ተግባር ሲፈጸምበት የነበረ» በተለምዶ ማዕከላዊ የሚባለዉን ወህኒ ቤት ዘግቶ «ዓለም አቀፍ ደረጃዉን የጠበቀ» የሚለዉን የምርመራ ማዕከል ለማቋቋም መወሰኑን አሳዉቀዋል።

 

በማዕከላዊ ወህኒ ቤት የእስር ጊዜ ኣሳልፌያለሁ የሚሉት አቶ ታዬ ዜናዉን ዉሳኔዉ አስደስቷቸዋል።

ጠበቃና የሕግ ባለሙያ አቶ ተማም አባቡልጉ የገዥዉ ፓርቲ ድርጊት እና ባሕሪ በሕግ መገዛት አለበት፣ መለወጥ ያለበትም ተቋም ሳይሆን  ሥርዓቱ መሆን አለበት ይላሉ። «ዓለም አቀፍ ደረጃዉን የጠበቀ የምርመራ ተቋም» ይባል እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ የእስረኛ አያያዝ መኖሩን አቶ ተማም ይጠራጠራሉ።

ለፖለቲካ ችግር የሕግ መፍትሄ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ የሚያመለክቱት አቶ ተማም የትናንቱ ንግግር «ከማሐል የጀመረ መሠረታዊ ችግርን ያልነካ ነዉ» ይሉታል።

የፖለቲካ እስረኞች ላይ ቁም ስቅል ይፈጸምባቸዋል ከሚባሉ እስር ቤቶች አንዱ እና ስሙ አብዝቶ የሚጠቀሰዉ ማዕከላዊ መዘጋቱ ድርጊቱን በሌላ ቦታ እንዳይፈጸም ዋስትና እንደማይሆን አስተያየት የሚሰጡ ወገኖች አሉ። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የፍትህ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የሥራ-ሒደት ኃላፍ ሆነው የተሾሙት አቶ ታዬ በዚህ ላይ የሚጨሩት አለ።

ማዕከላዊን መዝጋት አንድ ነገር ሆኖ እያለ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል መደበኛ ባልሆኑ እስር ቤቶች ዉስጥ ታስረዉ ስለሚገኙት ብዙዎች እጣፋንታም የሚያነሱ አሉ።

አቶ ታዬ በፌስቡክ ገጻቸዉ ላይ የጠቅላይ ሚንሥትሩን ንግግር አስመልክተዉ በጻፉት አስተያየት፤ ንግግራቸዉ «ህወሀትን ንፁህ አድርጎ ደርግን ብቻ ወንጅሏል። አቶ ኃ/ማርያም የህወሀትን ጥፋት በተቻለዉ ሁሉ ለማስተባበል ጥሯል።» ይህን ስሰማም አመመኝ በማለት ሰፋ ያለ ትችታቸዉን አስነብበዋል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic