1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማክሰኞ ጥር 14 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ማክሰኞ፣ ጥር 14 2016

ዜናውን በአጠቃላይ በጽሑፍም ከታች ማንበብ ይቻላል ።

https://p.dw.com/p/4bbGx

አርዕስተ ዜና

*ትግራይ ክልል ረሐብ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን በመግለጥ አስቸኳይ ርምጃ ካልተወሰደ የከፋ ጉዳት እንደሚከሰት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ዐስታወቁ ። በክልሉ አስቸኳይ ርምጃ ተወስዶ ለሕጻናትም ሆነ ለማኅበረሰቡ የምግብ ርዳታ ካልደረሰ መዘግየቱ የከፋ ጠኔ ሊያስከትል እንደሚችል ዓለም አቀፍ ድርጅት አስጠንቅቋል ።

*ኢትዮ ቴሌኮም በግማሽ ዓመት 42,9 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ዛሬ ዐስታወቀ ።  በሰሜኑ ያለው ጦርነት እና አንዳንድ ግጭቶች ለድርጅቱ ተግዳሮት መሆናቸውም ተገልጧል ።

*በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋችነት፣ ጋዜጠኝነት እና በመጽሐፍ ደራሲነት ለረጅም ዓመታት ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማበርከት የሚታወቀው አንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ።

*እሥራኤል ጋዛ ውስጥ የእግረኛ ጦር ካስገባችበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ቀን ብቻ በርካታ ወታደሮቿ መሞታቸውን ዛሬ ይፋ አደረገች ።

ዜናው በዝርዝር

መቀሌ፥ትግራይ ክልል ረሐብ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ አሰጋ

ትግራይ ክልል ረሐብ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን በመግለጥ አስቸኳይ ርምጃ ካልተወሰደ የከፋ ጉዳት እንደሚከሰት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ  ዐስታወቁ ። አቶ ጌታቸው በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪቃ አካባቢ ኃላፊ ኤትሌቫ ካዲሊ ከተመራው የልዑካን ቡድን ጋር ባደረጉት ውይይት በትግራይ ባለፉት ዐሥር ወራት የምግብ ርዳታ በመቋረጡ ምክንያት ያንዣበበውን አስከፊ ሰብአዊ እልቂት ለመቀልበስ አፋጣኝ ርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል ። በክልሉ የምግብ ርዳታው መቋረጡን በመቶ ሺህዎች ላይ የተበየነ «የሞት ቅጣት» ነው ያሉት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ዘግይቶ የሚቀርብ ማንኛውም ርዳታ በኋላ ትርጉም አልባ እንዳይሆን ያላቸውን ስጋት መግለጻቸውን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ኤትሌቫ ካዲሊ በበኩላቸው በክልሉ  የድርቅ ሁኔታ መባባሱ አሳሳቢ መሆኑን በማረጋገጥ፤ አስቸኳይ ርምጃ ተወስዶ ለሕጻናትም ሆነ ለማኅበረሰቡ የምግብ ርዳታ ካልደረሰ መዘግየቱ የከፋ ጠኔ ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል ።

አ.አ፥ ኢትዮ ቴሌኮም በግማሽ ዓመት በርካታ ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ

ኢትዮ ቴሌኮም በግማሽ ዓመት 42,9 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ዛሬ ዐስታወቀ ።  ነዳጅ መቅዳትን ጨምሮ  የመንግሥት አግልግሎቶችን ለማግኘት ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌ ብር አገልግሎት መጠቀምን ካስጀመረበት ጊዜ አንስቶ ደግሞ ድርጅቱ በአጠቃላይ የግብይት መጠን 1 ነጥብ 7 ትሪልየን ብር በኢኮኖሚው ላይ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሷል ።  የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ከጋዜጠኞች ተጠይቀው ሲመልሱ፦ በሰሜኑ ያለው ጦርነት እና አንዳንድ ግጭቶች ለድርጅቱ ተግዳሮት መሆናቸውንም ተናግረዋል ። ከፀጥታው ችግር  ባሻገር፦ በኔት ወርክ ላይ የሚደርሱ አደጋዎች የፋይበር ኮፐር ስርቆት እና መቆራረጥ፤ የግንባታ እቃ አቅርቦት እጥረት እንዲሁም የዋጋ ንረት የገበያ አለመረጋጋት  እና የኃይል  አቅርቦት መቆራርጥ  ተግዳሮቶች ናቸው  ሲሉም አክለዋል ። እንዲያም ሆኖ በበጀት ዓመቱ ያሰቡትን በግማሽ ዓመት ግምገማቸው ጥሩ ሆኖ ማግኘታቸውን ገልጠዋል ።

«ለበጀት ዓመቱ የያዝነው ታስታውሱ እንደሆን 90,5 ቢሊዮን ነው በበጀት ዓመቱ እንሠራለን ብለን ያሰብነው ። በግማሽ ዓመቱ ወደ 43 ቢሊዮን ገደማ ገቢ እንገኛለን ብለን ነው ዐቅደን የነበረው ። ከዚህ አንጻር አሁንም የገቢ አፈጻጸማችን እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል  ሆኖ አግኝተነዋል በግምገማችን ማለት ነው። »

ኢትዮ ቴሌኮም ዛሬ (ጥር 14 ቀን የ2016 ዓ.ም) የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ባሳወቀበት ወቅት እንደገለፀው ቴሌ ብር የተሰኘው የዲጅታል ገንዘብ ዝውውር ከ41 ሚሊየን በላይ ደንበኞች እንዳፈራለትም ዐስታውቋል ። ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹን ብዛት 74 ነጥብ 6 ሚሊየን ያደረሰ መሆኑንም ይፋ አድርጓል ። ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻርም በ4 ነጥብ 7 ሚሊየን ማለትም 6 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገልጿል ። ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ባለው ሁኔታ ከተፎካካሬው ሳፋሪ ኮም የውድድር ስጋት የለብኝም ማለቱንም የአዲስ አበባ ወኪላችን ሐና ደምሴ ከስፍራው ዘግባለች ።

አ.አ፥ ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ 

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋችነት፣ ጋዜጠኝነት እና በመጽሐፍ ደራሲነት ለረጅም ዓመታት ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማበርከት የሚታወቀው አንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ። በ1957 ዓ.ም በይርጋለም ከተማ የተወለደው ጋዜጠኛ ገነነ በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ኅልፈተ-ዜናው የተሰማው በዛሬው ዕለት ነው ። ገነነ ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ከተገለለ በኋላ ከ30 ዓመታት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት ማሳለፉን፤ ታሪክ ዐዋቂ መሆኑን እና በርካታ መጻሕፍትንም ለንባብ ማብቃቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጧል ። ለንባብ ካበቃቸው መጻሕፍቱ መካከልም በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተው፦ «ኢህአፓ እና ስፖርት» የተሰኘው መጽሐፉ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አትርፎለታል ። ገነነ መኩርያ በጋዜጣ እና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ አውታሮች ላይ ለረዥም ጊዜ አገልግሏል ። ለእግር ኳሱ ላበረከተው የላቀ አስተዋፅኦም በ2009 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተሰናዳው የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፈደሬሽን (CAF) ጉባኤ ላይ የረጅም ዘመን አግልግሎት ሜዳይ ተበርክቶለታል ። ዶይቸ ቬለ ለአንጋፋው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመዶች እና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል ።

ካራካስ፥ቬኔዙዌላ ፕሬዝዳንቷን ለመግደል ዐሲረዋል የተባሉ 32 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዐዋለች

የቬኔዙዌላ መንግሥት ፕሬዝደንቱን ለመግደል ዐሲረዋል በሚል የተጠረጠሩ ያላቸውን 32 ሰዎች ማሰሩን አስታወቀ። የፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ መንግሥት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በመሆን ፕሬዝደንቱን የመግደል  ሴራ አቀነባብረዋል ሲል ከሷል። በሴራዉ ተካፍለዋል የታባሉ 32 ወታደሮችና ሲቢሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። የቬኑዝዌላ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ታረክ ዊሊያም ሳብ ማኅበራዊ አንቂዎች፤ ጋዜጠኞች እና ወታደሮችን ጨምሮ በሌሎች 11 ሰዎችና በሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ላይም ተጠንስሶ ነበር ባሉት ሴራ የተጠረጠሩትን ለመያዝ የእስር ማዘዣ እንደተቆረጠባቸው ተናግረዋል። ሳብ፣ ተጠርጣሪዎቹ ለመገናኛ ብዙሃን ስለዕቅዳቸው ተናዝዘዋል፤ መረጃዎችን አውጥተዋልም ብለዋል። ማዱሮ ትናንት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫም የሀገሪቱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የእሳቸውን ሕግ ችላ ብለው ከአሜሪካን ጋር እየሠሩ ነው በማለትም ከሰዋል። የዛሬ ስድስት ዓመት ማዱሮ በድጋሚ መመረጣቸውን ይፋ ባደረጉ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎች ሃገራት ምርጫውን አሳፋሪ በማለት ውድቅ አድርገውት ነበር። ምንም እንኳን ዘንድሮ በሀገሪቱ ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ማዱሮ ቃል ቢገቡም ዋነኛዋ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ በሙስና እና በአሜሪካ ይደገፋሉ በሚል በቀረበባቸው ክስና ወንጀል ምክንያት ከተሳትፎ ታግደዋል ።  

ጋዛ፥እሥራኤል በርካታ ወታደሮቿ ጋዛ ውስጥየተገደሉበትን ክስተት መመርመር ጀመረች

እሥራኤል ጋዛ ውስጥ የእግረኛ ጦር ካስገባችበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ቀን ብቻ በርካታ ወታደሮቿ መሞታቸውን ዛሬ ይፋ አደረገች ። የእሥራኤል የመከላከያ ሚንሥትር ዮቭ ጋላንት ትናንት 24 ወታደሮቻቸው ጋዛ ውስጥ መገደላቸውን ከፍተኛ «ውድመት» ብለውታል ። የእሥራኤል ጠቅላይ ሚንሥትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው፦ የትናንቱን ቀን ከባዱ ቀን ሲሉ ገልጠውታል ።

«ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የትናንትናው ቀን በጣም ከባድ ከነበሩት ዕለታት አንዱ ነበር አገራቸውን ለመከላከል የተዋደቁ ጀግኖች፤ 24 ምርጥ ልጆቻችንን አጥተናል ከእሥራኤል ዜጎች ለእያንዳንዱ ሐዘኔን እገልጻለሁ ዓለማቸው ለዘለዓለም የተቀየረባቸው ቤተሰቦችንም አቅፌ አጽናናለሁ   ከዚህ ካለንበትም የቆሰሉ ወታደሮቻችን እንዲያገግሙ ጸሎታችን እናደርሳለን »

ጠቅላይ ሚንሥትሩ በአንድ ቀን ከ20 በላይ ወታደሮቻቸው የተገደሉበትን ክስተት ጦር ሠራዊታቸው ለማጣራት ምርመራ እንዲጀምር ማዘዛቸውንም ዐስታውቀዋል ። በዩናይትድ ስቴትስ፣ በአውሮጳ ኅብረት፣ በብሪታንያና በሌሎች መንግስታት አሸባሪ ድርጅት በሚል የተሰየመው ሐማስ መስከረም 26 ቀን፣ 2016 ዓ.ም እሥራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ካደረሰ በኋላ የእስራኤል ጦር የአጸፌታ ብርቱ ርምጃ ጋዛ ላይ ከፍቶ ተደጋጋሚ ድብደባዎችን እያካሄደ ነው ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም እሥራኤል ጋዛ ውስጥ በአንድ ቀን ብቻ ይህን ያህል ወታደር ሲገደልባት የመጀመሪያው ነው ።

በስተመጨረሻም ስፖርት፦

አስተናጋጇ አይቮሪኮስት በደጋፊዎቿ ፊት በሰፋ ግብ የተሸነፈችበት፤ ጋና የማታ ማታ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ዕድሏን ያጨለመችበት የአፍሪቃ ዋንጫ በአስደማሚ ውጤቱ ቀጥሏል ። ወደ ቀጣዩ ጥሎ ማለፍ ፉክክር ለመሻገር የሦስተኛ ዙር የምድብ ግጥሚያዎች ዛሬ ማታም ይከናወናሉ ። የምድብ ጥሩ ሦስተኛ ሆኖ ለማለፍ ቀጭን ገመድ ላይ የተንጠለጠለችው ጋምቢያ ከምሽቱ ሁለት ሰአት ላይ ከካሜሩን እንዲሁም ጊኒ ማለፏን ካረጋገጠችው ሴኔጋል ጋ በተመሳሳይ ሰአት ጨዋታቸውን ያከናውናሉ ።  እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች፦ ከምድብ «ሀ» ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ናይጄሪያ፤ ከምድብ «ለ» ኬፕ ቬርዴ እና ግብጽ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው አልፈዋል ። ማለፏን ያረጋገጠችው ሴኔጋል ዛሬ በምታደርገው ግጥሚያ ከምድብ «መ» አንደኛ ወይንም ሁለተኛ ትሆናለች ። ትናንት መደበኛው 90 ደቂቃ ከተጠናቀቀ በኋላ በተከታታይ በተቆጠሩባት ግቦች ከሞዛምቢክ ጋ ሁለት እኩል ተለያይታ እድሏን ያጨለመችው ጋና የምድብ ጥሩ ሦስተኛ ሆና ለማለፍ የሌሎችን ውጤት ትጠብቃለች ። በነገው እለት የምድብ ሦስተኛ ዙር የመጨረሻ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ ። በዚህም መሰረት ማታ ሁለት ሰአት ላይ ናሚቢያ ከማሊ እንዲሁም ደቡብ አፍሪቃ ከቱኒዝያ ጋ ይጋጠማሉ ። ከምሽቱ አራት ሰአት ላይ ደግሞ  ዛምቢያ ከሞሮኮ እና ታንዛኒያ ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጋ  ይጫወታሉ ። በነገው  ዕለት አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡ ምርጥ 16 ቡድኖች እንዲሁም ከእየምድቡ ጥሩ ሦስተኛ ሆነው ወደ ጥሎ ማለፉ መሻገር የሚችሉ አራት ቡድኖች ይለያሉ ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።