የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች | ዓለም | DW | 16.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች

በመደበኛ መልኩ ይፋ ያልሆኑ ሆኖም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናልም፥ አያገባንም የሚሉ የተለያዩ ትንንሽ ድርጅቶች እዚህም እዚያም እንደ አሸን እየፈሉ ነው። ከሰሞኑ አንድ ሌላ ተቋቁሟል። «ሸነግ» ይሰኛል በምሕጻሩ። ይኸኛው በእርግጥ ሌሎቹን ትንንሽ ድርጅቶች ለመወረፍ ብሎም ለመሳለቅ የተፈጠረ ምናባዊ ድርጅት ነው። የሸገር ነፃ አውጪ ግንባር «ሸነግ»።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:21
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:21 ደቂቃ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አበይት መነጋገሪያዎች

በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ሁለት ርእሰ ጉዳዮች አበይት መነጋገሪያ ጎልተው ወጥተዋል። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በእስር ቤት የለም የመባሉ ዜና ቀዳሚው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች በየጊዜው ብቅ የሚሉትን አዳዲስ  ድርጅቶች እና የፖለቲካ እሰጥ አገባዎች ላይ የሚሳለቀው «ሸነግ» የተሰኘው ሀሽ ታግ ሌላኛው መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።

በመደበኛ መልኩ ይፋ ያልሆኑ፥ ሆኖም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናልም፥ አያገባንም የሚሉ የተለያዩ ትንንሽ ድርጅቶች እዚህም እዚያም እንደ አሸን እየፈሉ ነው። ከሰሞኑ አንድ ሌላ ተቋቁሟል። «ሸነግ» ይሰኛል በምሕጻሩ።ይኸኛው በእርግጥ ሌሎቹን ትንንሽ ድርጅቶች ለመወረፍ ብሎም ለመሳለቅ የተፈጠረ ምናባዊ ድርጅት ነው። የሸገር ነፃ አውጪ ግንባር «ሸነግ»። «ሸነግ»ን ተደግፈው ብዙዎች ብዙ ተሳልቀዋል። ስላቁን አብረን እናነባለን።

በእርግጥ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የት ነው ያለው? ለ9 ቀናት የዘለቀ ጥያቄ፤ በዐሥረኛ ቀኑ መልስ አግኝቷል። በጽሑፎቹ የተነሳ ለሦስት ዓመት እስራት የተዳረገው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ካለፈው ሳምንት አንስቶ የት እንደሚገኝ እንደማያውቁ ቤተሰቦቹ መግለጣቸው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዋነኛ መነጋገሪያ ኾኖ ቆይቷል። 

ደብርሀን ዳት ኮም ሐሙስ ዕለት ባቀረበው የትዊተር ጽሑፍ «ዘጠነኛ ቀኑ፤ እስረኛው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አሁንም ያለበት አይታወቅም» ሲል ጽፏል። «ተመስገን ደሳለኝ የታሰረዉ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 ዓመት ነው። ኢትዮጵያ ለአሶሺየትድ ፕሬስ ያለበትን እንደማታውቅ ተናግራለች» ሲል በትዊተር ገጹ ያስነበበው ደግሞ ላውላድ ኢቦሌ ነው። ኢትዮጵያን ዲጄ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሰኞ ዕለት ባወጣው የፌስ ቡክ ጽሑፉ፦«ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከታሰረበት ዝዋይ እስር ቤት ‹የለም› ከተባለ ስድስተኛ ቀን ተቆጥሯል» ብሏል። እዚሁ ጽሑፍ ስር ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል አታኽልቲ ገብረ ሥላሴ፥ «ለአሸባሪ አዘኔታ የለኝም» ሲሉ አጭር መልስ አስፍረዋል።

ፍጹም ጎሳዬ በፌስቡክ ገጹ የሚከተለውን ጽፏል። «ቤተሰቦቹ በሄዱባቸው ቦታዎች ሁሉ ተመስገን የለም አሏቸው። እሺ ምን እናድርግ? የትስ እንፈለገው? አሁንም ደግመን እንጠይቃለን መንግስት ተብዬው የትግራይ ነፃ አውጪ ቡድን ስለ ተመስገን ደሳለኝ አሳውቀን ታህሳስ 6» ሲል ጽሑፉ ይጠናቀቃል። 

ስለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰቦቹ የሰሙት ነገር ካለ እንዲነግረን ለታናሽ ወንድሙ ለታሪኩ ደሳለኝ ሐሙስ ከሰአት በኋላ ደውለንለት ነበር። ስለ ጋዜጠኛ  ወንድማቸው እስካሁን ምንም አለማወቃቸውን ታሪኩ ገልጧል። «ዛሬ ዘጠነኛ ቀኑን ይዟል እንግዲህ፤ የት እንዳለ ሳናውቅ» ሲልም አክሏል። 

«የእናንተን ዘገባ ሰምተን በንጋታው ሄደን ነበር ዝዋይ ማረሚያ ቤት  በር ላይ ያሉት ተረኛ ወታደሮች ተመስገን የለም፤ ነግረናችሁ የለም ወይ? ምን ልትሠሩ መጣችሁ? አሉን።  ትናንትና በዶይቸ ቬለ ሬዲዮ ተመስገን እዚህ እኛ ጋር ነው ያለው ብላችኋል ስለተባለዉ እንደዚህ ያልነው ነገር የለም  አሉ። እሺ ውስጥ ገብተን አስተዳደሮችን እናናግር አልን። አትገቡም፤ ደግመን ደጋግመን ነግረናችኋል እዚህ እንደሌለ አሉን። ሳናገኘው ተመልሰን መጥተናል።»

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታናሽ ወንድም ታሪኩ ደሳለኝ ተመስገን ያለበትን ሳያውቁ ከቆዩ በዐሥረኛው ቀን ዛሬ ዐርብ ታኅሣሥ 7 ቀን ተመስገን ደሳለኝን ዝዋይ እስር ቤት ለጥቂት ደቂቃ እንዲያዩት መደረጉን በፌስቡክ ገጹ ገልጧል።

«ተመስገንን አግኝተነዋል፤ ከ 10 ቀናት በኃላ ከ30 ደቂቃ በፊት ለ 3 ደቂቃ በዝዋይ እስር ቤት በልዩ ጥበቃ ለብቻው በ7 ወታደሮች ተከቦ ተመሰገንን አግኝተነዋል። ተመስገንን ሰናገኝው ምንም ማውራት ባንችልም ሲራመድ እንደሚያሰቸግረው አይተናል። እሱም ከሌሎቹ ህመሙ ውጪ ጨጓራው እጅጉን መታመሙን ነግሮናል። እስካሁን የት እንደነበረ ምን እንዳረጉት በንጠይቅም ወታደሮቹ መመለስም ሆነ መጠየቅም አይቻልም ብለው ከልክለውናል። ተመሰገንን ከበው ካመጡት ወታደሮች መካከል ሀላፊያቸውን እስካሁን ለምን እዚህ እንዳለ አልነገራቹህንም ስንለው ተመስገን እዚህ ያገኘነው ዛሬ ነው ብሎናል። የሆነው ሆኖ ተመሰገንን አግኝተነዋል።» የሚለው ጽሑፍ «ተመስገንን አጣነው ካልንበት ግዜ አንስቶ ከጎናችን መሆናቹህን ላሳያቹሁን ሁሉ እጅግ በጣም እናመሰግናለን። ታህሳሰ 7/09ዓም» ሲል ይጠናቀቃል።

 በያዝነው ሳምንት ሰኞ ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የዝዋይ እስር ቤት ባልደረባ ጋዜጠኛ ተመስገን እዛው ዝዋይ እንዳለ ተናግረው ነበር። «አያይ እንደዚህ አይነት ደግሞ፤ ጭራሽ ተመስገን የለም የሚባል ነገር የለም። እኛ  ጋር ነው፤ አለ» ነበር ያሉት። የዩናይትድ ስቴትሱ ኒው ዮርክ ታይምስ ግን በኢንተርኔት ዘገባው ባወጣው ጽሑፍ  «የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ  አቶ ግዛቸው መንግሥቴ ተመስገን የት እንዳለ እንደማያውቁ ለአሶሺየትድ ፕሬስ ተናግረዋል» ሲል አትቷል።  ይኽ እርስ በእርሱ የሚጣረስ መግለጫ መሰማቱ ብዙዎችን አስደምሟል። የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች «ተመስገን ደሳለኝ የት ነው ያለው?» የሚል ጥያቄ በማስቀደም እንዲፈታ የኢንተርኔት ዘመቻ መጀመራቸው የሚታወስ ነው። በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ተመስገን ያለበት መታወቁ እፎይታ እንደሰጣቸው ገልጠዋል።

በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተደነገገ ወዲህ ለተወሰነ ብሔር የሚቆረቆሩ ድርጅቶች መቋቋማቸው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እየተነገረ ነው። እነዚህን አብዛኞቹን ድርጅቶች በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ከሚወረወሩ እሰጥ አገባዎች ባለፈ ግን  ማን እንዳቋቋማቸው በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።

የሸገር ነፃ አውጪ ድርጅት በምኅጻሩ «ሸነግ» በኢንተርኔት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ተፈጥሮ ሰሞኑን በርካቶች ሲሳለቁበት የቆዩበት ርእስ ነው።  

የኢሕአዴግ ደጋፊ የኾነው ከበደ ካሳ በፌስቡክ ገጹ፦ «ምንድን ነው ነገሩ? ሰሞኑን ፌስቡክ በደረሰበት ዝር አላልኩም ነበር፡፡ «መረራ ጉዲና ይፈታ!» «ተመስገን ደሳለኝ ጠፋብን» የሚለው አጀንዳ ላይ የዘጋሁትን ፌስ ቡክ ዛሬ ስከፍተው ወሬው ሁሉ ሸነግ እና ሰገጤ ብቻ ሆኗል» ሲል አስነብቧል። አዲስ አበባ ከገባ ዘጠኝ ዓመት እንደሞላው የተናገረው ከበደ ካሳ «ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ? ሰገጤ ነኝ ወይስ ሸነግ ይቀበለኛል?»  ሲል ጽሑፉን አጠቃሏል። አማር ቢን ያሲር በትዊተር የሚከተለውን ጽፏል። « ሸነግ (ሸገር ነጻ አውጭ ግንባር) ነጻነቱን ባገኘ ማግስት ከሚያከናውናቸው ሥራዎች አንዱ ሸገርን ዙሪያዋን በግንብ ማጠር ነው።»

ታምራት ነገራ፦ «አረ ለመሆነ የሸነግ መስራቾች እኛን አንጋፋ የሸገር ታጋዮች ለምን አላማከሩንም? ይሄ በጣም በጣም ያነጋግረናል» ሲል ተሳልቋል። «አሁን ዘግይቶ በደረሰን ዜና መሰረት 2 ሰገጤዎች ወደ ጀግናው የሸነግ ሰራዊት የጦር ካምፕ ተመሳስለው በመግባት ባለ አምስት ብሩን ሮኬት አፈንድተው ለማምለጥ ሲሞክሩ በሸነግ የደህንነት አባላት ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል፡፡አብዮታዊት ሸነግ ወይም ሞት፤ ድል ለጭቁኑ ቂነግ(የቂርቆስ ነፃ አውጪ ግንባር)» ሲል የተሳለቀው ደግሞ ሸነግ በሚል ርእስ የወጣ ገጽ ነው። 

ቢኒያም ሐብታሙ በፌስቡክ ገጹ ያሰፈረው ጽሑፍ «ከአልጀዚራ ተደውሎልኝ ነበረ… ሰለ SLF (Sheger Liberation Front) መረጃ ፈልገው» ሲል ይንደረደራል። «የውጭ ሚዲያዎች ሳይቀሩ አምርረዋል» የሚለው ጽሑፍ  የሳቅ ምልክት ያስከትልና «ለማንኛውም መረጃውን በእንግሊዘኛ እስከማሰናዳ እቺን እንኳ በአማርኛ…» በማለት ቀጣዩን አስፍሯል። «ገንዘብ ሳሙና ነው ይሙለጨለጫል፥ ጀለስካ አትተክዝ ሙድ መያዝ ይበጃል። ሸነግ ሸነግ አሉት ስሙን አሳንሰው፥ ከስንግ ይበልጣል አንዴ ለቀመሰው»። የቢኒያም  ጽሑፍ ዝም በልና ሸነግን ደግፍ በሚል ሀሽታግ በተደረገበት ሐረግ ይጠናቀቃል። 

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ማክሰኞ ዕለት ባወጣው ዘገባ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰኔ እስከ ኅዳር ባሉት ወራት ውስጥ 16 ድረ-ገጾች ተዝግተው እንነበር በኢንተርኔት አስነብቧል። የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች እና ጠንካራ ትችት የሚያቀርቡ ድረ-ገጾች መዘጋታቸውንም ገልጧል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉን አቀፍ የኾነ የኢንተርኔት ግንኙነት መቆጣጠሪያ ስልት (DPI) ጥቅም ላይ መዋሉንም ደርሼበታለሁ ሲልም አስነብቧል። 
 
ታግዶ የነበረው የተንቀሳቃሽ ስልክ የኢንተርኔት አገልግሎት መከፈቱ ቢነገርም በአሁኑ ወቅት ብዙዎች አንዳንድ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ለመጠቀም መቸገራቸውን ሲናገሩ ይደመጣል። ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ በኢንተርኔት በነፃነት ይሰጡ የነበሩ ትችቶች አሁን ቁጥብነት ይስተዋልባቸዋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic