የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 06.05.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢድ አል-ፊጥር በዓል አዲስ አበባ ሲከበር አንድ ፖሊስ «በስሕተት» አፈነዳዉ የተባለ አስለቃሽ ጢስ መዕምናን ማስደንገጡና ማተራመሱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት 7.2 ሚሊዮን ቤቶች በ10 አመታት ለመገንባት የያዘው ውጥን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ነበሩ። የፕሬስ ነጻነት ቀን ሲከበር በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ጉዳይ ተነስቷል።

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ባለፈው ሰኞ የኢድ አል-ፊጥር በዓል በአዲስ አበባ ዉስጥ ሲከበር የፀጥታ አስከባሪ "በስሕተት" ባፈነዳዉ  አስላቃሽ ጢስ በቦታው የነበሩ ምዕመናን ማስደንገጡና ማተራመሱ በሣምንቱ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዋንኛ መነጋገሪያ ከነበሩ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ነው። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት በዓሉ ከሚከበርበት የአዲስ አበባ ስታዲየም ውጪ በአብዮት አደባባይ የጸጥታ አስከባሪዎች ብረት ለበስ ተሽከርካሪ እየተንቀሳቀሱ አስለቃሽ ጭስ ሲተኩሱ የሚያሳይ ቪዲዮ በዕለቱ ይፋ አድርጓል። ይኸ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት የቪዲዮ ዘገባ ጸጥታ አስከባሪዎች አስለቃሽ ጭስ በተኮሱበት አካባቢ አንዳንድ የበዓሉ ታዳሚያን እየተሯሯጡ ሌሎች በዝግታ እየተራመዱ ከአካባቢው ሲርቁ ያሳያል። ፌስቡክን በመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከቀይ ሽብር ሰማዕታት ቤተ-መዘክር አካባቢ የጸጥታ አስከባሪዎች በሚተኩሱት አስለቃሽ ጭስ የተደናገጡ እና የተቆጡ የበዓሉ ታዳሚያንን አሳይተዋል። በዕለቱ በተፈጠረው አለመረጋጋት ከቤተሰቦቻቸው የተነጣጠሉ ሕጻናት በጀርመን እና ፍልውሃ መስጂድ፣ ስቴዲየም አካባቢ በሚገኘው ቀይ መስቀል፣ በካሳንቺስ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ፣ ለገሀር እና ደምበል ፓሊስ ጣቢያ ይገኙ እንደነበር ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።

አንድ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ባለሥልጣን የኩነቱ መነሾ የጸጥታ አስከባሪ በቦታው በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ "ባለማወቅ" አስለቃሽ ጭስ መተኮሱ እንደሆነ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። በዚህ ምክንያት ሰዎች መደናገጣቸውን፣ አንዳንዶች መፈክር ማሰማታቸውን እና ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጪ መውጣቱን የተናገሩት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ባለስልጣን ፖሊሱ በሌሎች ባልደረቦቹ ከቦታው መወሰዱንም ገልጸዋል። በማኅበራዊ ድረ-ገጾች የተሰራጩ የቪዲዮ ምስሎች ይኸው አስለቃሽ ጭሱን በስህተት ተኮሰ የተባለ የጸጥታ አስከባሪ በሌሎች ባልደረቦቹ ከቦታው ሲወሰድ አሳይተዋል።

የኢትዮጵያ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል በዕለቱ በፌድራል ፖሊስ የተረጋገጠ የፌስቡክ ገጽ በኩል ባሰራጨው መግለጫ ኩነቱ "የሁከትና ብጥብጥ ዓላማ ያላቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች" የተፈጠረ መሆኑን ገልጿል።  

"ለብጥብጥ መነሻ በማይሆን ምክንያት" መቀስቀሱንም በመግለጫው ጠቅሷል። "ፀረ-ሰላም" የተባሉት  ግለሰቦች እና ቡድኖች በስም ባይጠቀሱም "ስለታማ ነገሮችን፣ የውጭ ሀገር አክራሪዎችን አርማ እና የተለያዩ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችን በመያዝ ጥቃትና በቀል ለመፈፀም ወደ በዓሉ ስፍራ" እንዳቀኑ የኢትዮጵያ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ገልጿል።

ከአዲስ አበባ ስታዲየም ውጪ በቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም አጠገብ ተነሳ ባለው "ረብሻ እና ብጥብጥ" በጸጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ገልጾ ነበር። በዕለቱ "ግንባር ቀደም" የተባሉ 76 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በፌድራል ፖሊስ የፌስቡክ ገጽ በተሰራጨው መግለጫ አስታውቋል።

ሰሚር የሱና "በአይናችን ያየነውን ነገርማ እንዳትዋሹን። በዋነኛነት የፀቡ መንስኤ አስለቃሽ ቦንብ የለቀቀው የፀጥታ አካል ነው። እኛ የኢድ ሶላት ለመስገድ ልጆቻችንን፣ እናቶቻችንን ይዘን ስንመጣ በፀጥታው ሀይል ከአላህ በታች ተማምነን ነበር። የእውነት ከፍቶናል። ሌላ አጀንዳ ያላቸውን ሰዎች ማጣራት የእናንተ ሥራ ነው። ግን መነሻ የሆነውን የፀጥታ አካል  በደንብ ይመርመርልን። ይሄ ከባድ ክህደት ነው" ሲሉ በኢትዮጵያ ፌድራል ፖሊስ የፌስቡክ ገጽ ለቀረበው የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ መልስ ጽፈዋል።

"ድራማውን ቀጠላችሁበት አይደል?" ሲሉ የሚጠይቁት አቡ ማሒራ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚም ማብራሪያው አልተዋጠላቸውም። አቡ ማሒራ "ተንኳሹ የራሳችሁ አባል ሆኖ ሳለ፤ በግልጽ አይን ፍጥጥ ብሎ በገሃድ የታየን የጠራራ ጸሐይ እውነታን ክዳችሁ ወደ ሌላ ግለሰቦች ለማላከክ የምታደርጉት ጥረት ´አጨፍኑ እንሸውዳችሁ´ እንጂ ቁስልን አያክምም። ይኸው ተግባር እንዲከሰት ስላሰባችሁ አላማችሁ ስለነበር ፍተሻ እንኳን አልነበረም" ሲሉ ጽፈዋል። ናሲህ ሻሚል በበኩላቸው የጸጥታ አስከባሪዎች በዕለቱ ለተፈጠረው ኩነት ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ "ረብሻውን ያስነሱት የፀጥታ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ እና ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ" ከዚህ በተጨማሪ "ይኸ ክስተት ፈፅሞ ላይደገም ዋስትና" እንዲሰጥ በፌስቡክ ባሰፈሩት ሐሳብ ጠይቀዋል።

ሐም ሐም የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው "ሁሌም ችግሮች ሲፈጠሩ በማን እና እንዴት ተፈጠረ? ከሚለው እውነት በላይ የተፈጠረውን ችግር አሳንሶ ማየት ይቀላችሁኋል" ሲሉ ይወቅሳሉ። "ለመሆኑ በዚህ አስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ መሆናችን እየታወቀ፤ እኛን ይጠብቀናል ብለው የሚመኩበት የፀጥታ አካል ሴት እህቶቻችን ላይ አስለቃሽ ጪስ ወርውሮ ጥፋት ከመስራት በላይ ለግጭት መነሻ ሌላ ምን ነገር ሊኖር ይችላል?" ሲሉ ሐም ሐም ጠይቀዋል።  "እውነት ለመናገር የፖለቲካ ነገር ሆኖባችሁ አይናችሁን በጨው አጥባችሁ ወጣችሁ እንጂ፤ በድርጊቱ እንደምታፍሩ ግልፅ ነው። ምክንያቱም የፌዴራል ፖሊስ በጣም ዘምኗል እየተባለ ባለበት ሰዓት እንደዚህ አይነት የማይመጥን እኩይ ተግባር ማሳየቱ ነውርም ነው። ስለዚህ አሁን እናንተ የአይኑ ቀለም ያላማራችሁን ሰው እየያዛችሁ ማሰር ብትችሉም ግን ብቸኛው መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ትክክለኛውን ወንጀለኛ ለህግ ማቅረብ እና በህግ ብቻ መዳኘት ሲችል እንደሆነ ከሁላችንም እናንተ ጠንቅቃችሁ ታውቁታላችሁ። እባካችሁ ለእውነትና ለፍትህ ብቻ ስሩ ያኔ ወንድማማችነትን እና የኢትዮጽያን ብልፅግናን እውን ማድረግ እንችላለን" ብለዋል።

Äthiopien | Feche Housing Development project in Addis Abeba

የኢትዮጵያ የከተማ እና የመሠረተ-ልማት ሚኒስቴር በአስር ዓመታት 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ማቀዱን ይፋ አድርጓል።

7.2 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶች በአስር አመታት?

የኢትዮጵያ የከተማ እና የመሠረተ-ልማት ሚኒስቴር በአስር ዓመታት 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ማቀዱን ይፋ አድርጓል። የመሥሪያ ቤቱ ባለሥልጣናት እንዳሉት 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶች በከተሞች 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶች ደግሞ በገጠር ለመገንባት ታቅዷል። የኢትዮጵያ የከተማ እና የመሠረተ-ልማት ሚኒስቴር በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ በዕቅዱ ላይ ጥርጣሬ ላላቸው ማብራሪያ ለመስጠት ሞክሯል። መሥሪያ ቤቱ "በቀጣይ 10 ዓመታት 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቤቶች 20 በመቶ የሚገነባው በመንግስት፣ 35 በመቶ በመኖሪያ ቤት ኀብረት ሥራ ማኀበራት፣ 15 በመቶ በግለሰቦች፣ 10 በመቶ በሪል ስቴት አልሚዎች፣ 15 በመቶ በመንግሥትና በግል ባለሃብት አጋርነት እና 5 በመቶ በሽርክና (ጆይንት ቬንቸር) ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል" የሚል ማብራሪያ ሰጥቷል።

መሥሪያ ቤቱ ከጻፈው ማብራሪያ ሥር ጥያቄ እና ትችት ለጻፉ እግር በእግር እየተከታተለ መልስ ለመስጠት ሲሞክርም ነበር። ቢኒያም ፍቅሬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ከሌለ እቅድ ብቻውን ተግባር አይሆንም" ሲሉ በተቋሙ ማብራሪያ ሥር ጽፈዋል።

አሰፋ በቀለ ደግሞ "በዛ እቅዳችሁን ቀንሱ የሚል አስተያየቶች ሲሰጥ አላስተዋልኩም። ከነበረው አፈጻጸም አንጻር እቅዱ ምኞት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር በምን እንመናችሁ ነው እያልን ያለነው" ሲሉ ጽፈዋል። የኢትዮጵያ የከተማ እና የመሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ለአሰፋ " ለተግባራዊነቱ ሁላችን እንደ ተቋምና ህዝብ ከተረባረብን የማይሳካ ነገር የለም። የሚሳለቁና ለግል ፍላጎታቸው ነገሩን ለመጠምዘዝ የፌስ ቡክ ማድመቅያ ከማድረግ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣ መጣር ነው። እኛ ዕቅዱን ለማሣካት ዝግጁ ነን እናንተስ?" የሚል ጥያቄ በመሠንዘር መልስ ለመስጠት ሞክሯል።

"ጥቂት ግዜ ቢሆንም ሀገርን እንደሚመራ ፓርቲ ሀገራዊውን ሁለንተናዊ ለውጥ ባወራችሁት ልክ አለማድረሳችሁ፤ የማስፈፀም አቅማችሁ ይብስኑ ቁልቁል መውረዱ፤ በሚንስቴችሁ ተጠሪ ተቋማት እና ማዘጋጃ ቤቶች ያለው ጉድ እኮ አሳፋሪም አስፈሪም ነው" የሚሉት ደግሞ ጌታሁን አየለ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው። "ሒስ ትታችሁ ´ኑ አብረን እንስራ` የምትሏት ፈሊጥ ነው ደግሞ ሚገርመው፤ ስሩ ብሎ ህዝቡ መርጦ ወንበር ከሰጣችሁ በኋላ" የሚሉት ጌታሁን "ለቡድን ሳይሆን ለባለሞያ እና ለለውጥ ተራማጅ ለሆኑ ቅድሚያ ስጡ" በማለት እርሳቸው መፍትሔ ያሉትን ጠቆም አድርገዋል።

የፕሬስ ነጻነት ቀን እና የጋዜጠኞች እስር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ይዘው በኢትዮጵያ የለውጥ ንፋስ ሽው አለ በተባለበት ወቅት በአገሪቱ የፕሬስ ነጻነት ረገድ ታይቶ የነበረው ተስፋ ተመልሶ የመጥፋት ምልክት ማሳየቱ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ያሰጋ ጉዳይ ሆኗል። ባለፈው እሁድ ሚያዝያ 23 ቀን 2014 በጸጥታ አስከባሪዎች ከመኖሪያ ቤቱ በጸጥታ አስከባሪዎች እንደተወሰደ የተገለጸው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ጉዳይ ለዚህ ኹከኛ ማሳያ ነው። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ባወጣው እና በፌስቡክ ገጹ ባጋራው መግለጫ  ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ "ታፍኖ ተወስዶ እንዲሰወር የተደረገው የዓለማችን የፕሬስ ነጻነት ሳምንት በሚከበርበት ወቅት መሆኑ መንግስት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ጥቃት እንደከፈተ ያስቆጥረዋል" ሲል ነቅፏል። ጋዜጠኛው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር አባል እንደሆነ የጠቀሰው መግለጫ "ጎበዜ ሲሳይ ያጠፋው ጥፋት ቢኖር እንኳን እንደማንኛውም ተጠርጣሪ በሕግ ቁጥጥር ሥር ሊውልና ዳኝነት ሊሰጠው ሲገባ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ የት እንደሚገኝ እንኳን ሳይገለጽ ቀናትን ማሳለፉ የመብት ጥሰት ብቻ ሳይሆን መንግሥት ይህን ያልተገባና አደገኛ አዝማሚያ በጋዜጠኞች ላይ ማድረሱን እንደመብት የቆጠረው አስመስሎታል" ብሏል። ማኅበሩ "ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ለምን በዚህ ሁኔታ እንደታሰረ?፣ የት እንደሚገኝ? እና የተያዘበት ምክንያት" እንዲገለጽ ጥያቄ አቅርቧል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ የጋዜጠኛው እስር አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ሲፔጄ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ከመቀከበሩ ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ በእስር ላይ የሚገኙት ደሱ ዱላ እና ብቂላ አመኑ የተባሉ ሁለት ጋዜጠኞች በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ከተባሉ ከሶስት አመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ሊወሰንባቸው እንደሚችል ገልጿል። ኦሮሚያ ኒውስ ኔትወርክ የተባለ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ዘገባዎቹን የሚያሰራች ብዙኃን መገናኛ ባልደረቦች የነበሩት ሁለቱ ጋዜጠኞች መጋቢት 29 ቀን 2014 በኦሮሚያ ክልል ክስ እንደተመሠረተባቸው ጠበቃቸው ለሲፒጄ ተናግረዋል። ሁለቱ ጋዜጠኞች የታሰሩት ሕዳር 9 ቀን 2014 ነበር።

ሲፒጄ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋዜጠኛ ደሱ ዱላ እና ብቂላ አመኑን በአፋጣኝ እንዲፈቱ፣ የመሠረቱባቸውን ሁሉንም ክሶች እንዲያነሱ፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ዒላማ ማድረግ እንዲያቆሙም ጥሪ አቅርቧል።

የዓለም የፕሬስ ቀን የተከበረው ባለፈው ማክሰኞ ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ነበር። ለሰዎች መረጃ የማግኘት መብት የሚሟገተው ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ በዚህ ሣምንት ይፋ ባደረገው ሰነድ መሠረት በፕሬስ ነጻነት ኢትዮጵያ ከ180 አገራት በ114ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ባለፈው ዓመት 101ኛ ደረጃ ላይ ነበረች።  በአመቱ በርካታ ጋዜጠኞች እየታሰሩ ተፈተዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic