የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 19.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ባለፉት ቀናት መንግሥት የትገባ እያሉ ጥያቄ ሲያቀርቡ አልፈውም ሲተቹ የነበሩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ክፉኛ መጉዳቱ የተገለጸው እሳት በቁጥጥር ሥር የመዋሉን ሰናይ ዜና ሲቀባበሉ ታይተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:01

የኢህአዴግ ምክር ቤት መግለጫ እና የሚኒስትሮች ሹመት

 ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙት ብርቅዬ እንስሳትን ሕልውና እንደተፈታተነ በርካታ ቀናት ያስቆጠረው እሳት ከእስራኤል በመጡ ቤተ እስራኤላውያን ኢትዮጵያውያን እና እስራኤላውያን ባልደረቦቻቸው እንዲሁም ከኬንያ በተውሶ በተገኘችው ሄሊኮብተር እገዛ እሳቱ ሊጠፋ ፓርኩም ከውድመት ሊዲን በመቻሉ ለብዙዎች እፎይታ ሆኗል።

ኤልሞጌ ካሚል ሻማ የተባሉ የፉስቡክ ተጠቃሚ ፓርኩን ያጋየውን እሳት ለማጥፋት የተውሶ ሄሊኮፕተር መራዳቱን አስመልክተው፤ «ይገርማል፤ ይህች ሀገር በአፍሪቃ ምርጥ የተባለ አየር መንገድ አላት ሆኖም  እንዲህ ባሉ የብሔራዊ ፓርኮች የእሳት አደጋዎችን ማጥፋት የሚያስችሉ ሄሊኮፕተሮች የሏትም። አዳጋች ተልዕኮ።» በማለት ግርምታቸውን ሲገልፁ የሱነህ ወልዴ ደግሞ፤ «የሀገር መኩሪያ እንዲሁም የኤኮኖሚ ምንጭ የሆኑ ቅርሶቻችን ጥብቅ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል።» በማለት አሳስበዋል።

 በዓለም ቅርሰነት በተመዘገበው በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክም ሆነ በሌሎች የደን ቦታዎች በሰው ሠራሽ መንገድ የእሳት ቃጠሎ የሚያስነሱ ግለሰቦች ጉዳዩ እየተጣራ ለሌሎችም አስተማሪ የሆነ ርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ያሳሰቡም አሉ።

ከእስራኤል መጥተው በእሳት ማጥፋቱ ለተባበሩት ባለሙያዎች  የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ምስጋና ማቅረባቸውን ባለልጣን መሥሪያ ቤቱ በፎቶ አስደግፎ በፌስቡክ ያሰራጨመው መረጃ ያመለክታል። በሰሜን ብሄራዊ ፓርክ ቃጠሎ አብሮ ሲጨስ የከረመው ኢትዮጵያዊ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚ በፈረንሳይዋ ፓሪስ ከተማ ማዕከል የሚገኘው ግንባታው ከ180 ዓመታት በላይ እንደወሰደ የሚነገርለት ዝነኛው ኖትር ዳም ካቴድራል ድንገት በእሳት መጋየቱን አስመልክቶም ቅርስ ወደመ በሚል ሃዘኑን ሲገልፅ ታይቷል። ከበርካቶች መካከል ፍሬህይወት ፌሪ የተባሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «በጣም ያሳዝናል ገብቶ ላየው ሰው ሙሉ በሙሉ የተሰራው በድንጋይ ነው የፈጣሪ ቁጣ ካልሆነ በቀር እንዲህ እንደ እንጨት ይነዳል ብሎ መገመት ከባድ ነው።» በማለት አግራሞታቸውን ገልጸዋል። የፈረንሳይን የጎቲክ ሥነ ሕንጻን የሚያሳየው ኖትር ዳምን በመጪው አምስት ዓመታት ዳግም ለማደስ ከበጎ አድራጎዊች እስከ 600 ሚሊየን ዩሮ ቃል ተገብቷል።

ገዢው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር ኢህአዴግ በዚህ በያዝነው ሳምንት ነበር የሁለት ቀናት የምክር ቤት ስብሰባውን ያካሄደው። የምክር ቤቱን ጉባኤ በትኩረት በመከታተል ላይ መሆናቸውን ይገልፁ ከነበሩ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች ስብሰባው መጠናቀቁን የጠቆመው መግለጫ ይፋ እንደሆነ በደቂቃዎች ውስጥ ነበር አስተያየታቸውን አከታትለው ማስነበብ የጀመሩት። ተስፋችን ሃይሌ በፌስ ቡክ፤ «ከለውጡ በኋላ ስንቱ ከቦታው ሲነሳ የኢሕአዴግን መግለጫ የሚፅፈው ሰውዬ ብቻ እንዳለ መቀጠሉ ይቆጫልⵆ ሌላው ቢቀር ፎርማቱን ቀሙት!»  ብለዋል፤ ተስፋ አለም ደግሞ፤ «ከዚህ ስብሰባ ምንም ጠብቄ ስለማላውቅ በመግለጫው ምንም ባለመባሉ ብዙም አይደንቀኝምሰዎቹ የአገሪቱን ስልጣን እንዴት እንደሚከፋፈሉ ብቻ የሚነጋገሩ እንጂ ስለሌላው ህዝብ ግድ የሌላቸው ስብስቦች ናቸው።  አንድ ነገር ግን ማወቅ ያለባቸው ሚኒስቴርም ለመሆን አገር እና ህዝብ ያስፈልጋል።» ብለዋል።

አክሱም ሳዶ በበኩላቸው በእንግሊዘኛ « ይህን በጣም ጥሩ እንደሆነ መግለጫ ብቻ ነው የማነብበው። አብዛኛው ተሳታፊዎችም ያመኑበት እና የተቀበሉት ነው ብዬም አምናለሁ። ይህ እንዲህ ከሆነ ደግሞ መንግሥት የሕዝቡን ይሁንታ እያገኘ ወደፊት ይጓዛል ማለት ነው። የተቀመጡት እቅዶች አጣዳፊ በመሆናቸው ባስቸኳይ ተግባራዊ መሆን ይኖርባቸዋል።» ሲሉ አስተያየታቸውን በፌስ ቡክ አስነብበዋል። ዓለሙ ኃይሌም እንዲሁ በፌስቡክ በአጭሩ ፤ «የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል» ሲሉ፤ አብዱ ሰይድ ደግሞ፤ «ከተለመደው ማደናገሪያና ማጭበርበሪያ ውጭ ጉባኤውን ችግር ፈች መፍትሄ አላየሁበትም፡፡ ችግር ሲፈጠር ህዝብ ለማደናገር ይጠቀሙበታል የዚህ ድርጅት የተሰለቸና ያረጀ አካሄድ ነው፡፡ » በማለት አስተያየታቸውን ከዘለፋ ጋር አክለዋል። ለዊ ሃይሉ ጌታነህ ደግሞ፣ «መግለጫ አገር አያረጋጋም፣ የውጪ ምንዛሪ አያመጣም፣ ዳቦ አይገዛም…» ብለዋል። ጥላዬ አልማዜ ፊልም ደግሞ፤ «አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ነው ጉዳዩ።» ሲሉ በአጭር ምሳሌያዊ አነጋገር ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።»

ሌላው የብዙዎችን ትኩረት የሳበው በትናንትናው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቅራቢነት የሀገሪቱ ምክር ቤት ያጸደቀው የሦስት ሚኒስትሮች ሹመት ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦታውያለ ተሿሚ ለሳምንታት በመቆየቱም የብዙዎች ትኩረት እና ግምት ማን ሊሆን ነው የሚለው እንደነበር ታይቷል። በዚያው ልክ ምነው ዓመት ባልሞላ ጊዜ በውስጥ ሹምሽሩ ተደጋገመ  ያሉም አልጠፉም። ያም ሆኖ ምክር ቤቱ የቀረቡለትን እጩ ሚኒስትሮች የማጽደቅ ሂደት በደቂቃዎች ውስጥ መከናወኑን አስመልክቶ ሳይድ ዳውድ በፌስቡክ፤

«እኔን የሚገርመኝ ፓርላማ !! ወፍጮ ቤት እንኳን በደንብ ሣያበጥር የመጣለትን ሁሉ ወደቋት አያሥገባም ከተፈጠረ ጀምሮ ይሄ አይዋጥልኝም ያልሠማሁት አንድ ወፍጮ ቤት ቢኖር ርላማ ነው !! ተዘጋጅቶ የቀረበለትን ሁሉ በጭብጨባ እያዋዛ ግባ በለው !!! ለተመራጮች ግን አንዲት ኢትዮጵያ የሚለው ዛር ሠፍሮባችሁ መልካም የሥራ እና የሠላም ዘመን ያርግላችሁ !! ቀኝ ቀኙን ንዱት !!!!!» ሲሉ፤ አብነት ምትኩ ደግሞ በዚሁ በፌስ ቡክ፤ «ቀድሞ እኮ ከፓርላማዉ ስብሰባ ዉጪ ሹመኞቹ እነሱ መሆናቸዉ ታውቋል አጨብጭቦ ለማሳወቅ ሁለት ደቂቃ ይበቃ ነበር ተቀበል ተብሎ ለተዘፈነለት ምክርቤት።» ብለዋል።

አብዲ አባ ወልድ የሚል መጠሪያ ያላቸው የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ 

«ጠቅላይ ሚኒስቴሮች ለሹ ቀረቡትን ሁሉ አጨብጭቦ የሚቀበል ፓርላማ አባል ለአባል ነው እንዴ የሚሰጠው?? / አይሻ የመከላከያ ሚኒስቴር ሆነው ሲሾሙ ድገፍ ይሰጣል ሲሻ ድገፍ ይሰጣልየፓርላማ አባላት የወከላቻው ጠቅላይ ሚንስቴሩ ነውን??» በማለት አስተያየታቸውን በጥያቄ አስፍረዋል።

ተሿሚዎቹን በሚመለከት በትዊተር ከተጻፉ  አስተያየቶች ዮሐንስ በርኼ፤ « ሁለቱም ባስተዳደሯቸው ክልሎች የሚያንፀባርቅ ሪከርድ የሌቸውም። ይህ ወደፌደራል ሥልጣን ሲመጡ እንዴት ሊለወጥ እንደሚችል አላውቅም። ሀገሪቱ አዳዲስ ሃሳብ እና አዲስ ደም ያስፈልጋታል።» ሲል ፤  ጋሻው ሽፈራው፤ « የመከላከያ ሚንስትር ሠራዊቱን የማዘዝ ስልጣን አለው? ከሆነስ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ለምን አስፈለገ? ልዩነታቸውስ ምንድን ነው?» በማለት ጠይቋል።

ዳንኤል ብርሃኔ በትዊተር፤ «ገዱ አንዳርጋቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ለማ መገርሳ የመከላከያ ሚኒስትር? እየቀለድክ እንዳይሆን! እየወደቀ ያለውን የዐቢይ አህመድን መንግሥት ለማዳን የመጨረሻ ርምጃ መሆኑ ነው? ወይንስ የመውጫ ስልት? ድግሱ ከማብቃቱ በፊት የመጨረሻው ቢራ።»

እንዲሁም በትዊተር አቤል ዋበላም፤ «ምንአልባት የለማ መገርሳ መከላከያ መሆን ሀገሪቱ ካለባት የጸጥታ ችግር አንጻር ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ የገዱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ግን አልተዋጠልኝም፡፡ ባለሙያ ቢሾምበት መልካም ነበር፡፡ ዐቢይ ራሱ እንደሚዘውረው ከወዲሁ መገመት ይቻላል» ብሏል። አፈንዲ ሙተቂ በፌስቡክ፤ «ግራ የተጋቡ መሪዎች ግራ እያጋቡን ነው!! ይሄ መንግ ዛሬም የካቢኔ ሹምሽር አድርጓል። እንደዚህ ሲያደርግ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ሹምሽር! ሹምሽር! ሹምሽር! ሹምሽር! እጅግ በጣም ያሳዝናል። ቀደም ብለን እንደገለፅነው ለዚህ መንግስት እውቅና የሰጠነው እንደ ሽግግር ጊዜ መንግስት እንዲያገለግለን ነው። ታዲያ በሽግግር ጊዜ የሚሰራው ሹምሽር ብቻ ነው እንዴ?» በማለት ረዘም ያለ ዝርዝር አስተያየቱን አስፍሯል። በዶይቼ ቬለ DW ኋትስአፕ ከደረሱን አስተያየቶች ውስጥ ደግሞ «የማይታመን ሹመት ነው ምንድ ነው ኦሮሞ ተሰበሰበ አብይ ከበፊቶቹ መማር አልቻለም» ሲል፤ ሌላኛው «መልካም የሥራ ዘመን ይሁንላቸው ሀገራችንም ሰላሞ ይብዛላት» ይላል።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic