የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 14.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በኢትዮጵያ የወጣቶች ሥራ አጥነት መቀነሱን ያተተው የኳርትዝ ዳት ካም የኢንተርኔት ጽሑፍ መተቸቱ፤ የሐብታሙ አያሌው የአሜሪካ ንግግር እና የጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ የእስር ቤት ደብዳቤ በዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ፕሮግራም የምንዳስሳቸው ርእሰ ጉዳዮች ናቸው። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:02

የሳምንቱ አበይት መነጋገሪያ ርእሰጉዳዮች

በኢትዮጵያ የወጣቶች ሥራ አጥ ቁጥር ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ጋር ሲነጻጸር በተሻለ መቀነሱን የሚያትተው የኳርትዝ ዳት ካም የኢንተርኔት ጽሑፍ  በትዊተር ተጠቃሚዎች ዘንድ ጠንከር ያለ ትችት ቀርቦበታል። ጽሑፉ የወጣቶች ሥራ አጥነት ከኢትዮጵያ በስተቀር በመላው አፍሪቃ ችግር እንደሆነ ይጠቅሳል። ፖለቲከኛ ሐብታሙ አያሌው በዩናይትድ ስቴትስ ያሰማው  ንግግር በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ሰፊ መነጋገሪያ ኾኗል። በእስር ላይ የሚገኘው የጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ደብዳቤ በርካቶች ተቀባብለውታል። በግብጽ ክርስቲያኖች ላይ የተጣሉት የሽብር ጥቃቶችን እንዲሁም የሚዳስሱ አስተያየቶችንም አካተናል።

ዕለታዊ ዘገባዎችን በኢሜል እንደሚያሰራጭ የሚገልጠው ኳርትዝ ዳት ካም አፍሪቃን በሚመለከተው የኢንተርኔት ዘገባው፦ «የወጣቶች ሥራ አጥነት በመላው አፍሪቃ ችግር ነው፤ ከኢትዮጵያ በስተቀር» የሚል ጽሑፍ በኢንተርኔት አስነብቧል። ኢትዮጵያን ፕሬስ በተሰኘው የትዊተር ገጹ አቤኔዜር ይኽን የኳርትዝ ዳት ኮም ዘገባን በማያያዝ በቅጥፈት የተሞላ ነው ሲል አስነብቧል። በሊንሴ ቹቴል የቀረበው ይኽው ጽሑፉ በጎርጎሪዮሱ 2016 ዓመት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪቃ ስላለው ሥራ አጥነት ያትታል። 

ጄ ቦንሳ ደግሞ የሞ ኢብራሂም በምስል የተቀናበረ ጽሑፍን በማያያዝ፦ «አዎ ምስሉ ያሸበረቀ ነው በአይ ኤም ኤፍ ሰነድም የተዋቀረ ሊሆን ይችላል፤ ግን አስታውሱ አይ ኤም ኤፍ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያቀርበው ምስል የቅጥፈት አዙሪት ነው» ብሏል። 

የዞን ዘጠኝ አምደ መረብ ጸሓፊው ዘላለም ክብረት በበኩሉ፦ «ዐይኖቼን ፈጽሞ ማመን አልቻልኩም» ይላል በትዊተር ጽሑፉ።  ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሥራ አጥነት ከ16 በመቶ በላይ ነው ሲሉ ሊንሴ ዝቅ ያለ አሃዝ ማቅረቧን በማነጻጸር  ዘላለም እጅግ መሰላቸቱን ይጠቅሳል።  የኳርትዝንም ጽሁፍ  ጠቅላይ ሚንሥትሩ ቀደም ሲል የተናገሩትንም በዋቢነት በትዊተር ገጹ አያይዟል። 

ዘላለም ያያዘው ጽሑፍ ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከአንድ ዓመት በፊት ከ«ኦል አፍሪቃ» ድረ ገጽ ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ በሚል ዘ ጋርድያን የተሰኘው ጋዜጣ በኢንተርኔት ላይ አስፍሮት ይገኛል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከተናገሩት የተቀነጨበው ጽሑፍ፦«ያለን የሥራ አጥ መጠን 16,5 በመቶ ነው፤ በጣም ብዙ ነው። በወጣቶች ደግሞ ይብሳል፤ ከህዝባችን 70 በመቶው  ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች ነው» ይላል። ዘላለም የሊንሴ የተዛባ አሃዝን በመጥቀስ የሰነፍ ጋዜጠኛ ተግባር  ሲል ተችቷል። ኢትዮ ኤክሶዶስ የሚል መጠሪያ ያለው የትዊተር ተጠቃሚ «ምን አይነት ዝባዝንኬ ነው» ብሏል በአጭሩ። ሩቲ ደግሞ «የምናወራው ስለ ተመሳሳይ ኢትዮጵያ ነው?» ስትል ጥያቄ አቅርባለች። 

ይኽን የኳርትዝ የኢንተርኔት የእንግሊዝኛ ጽሑፍ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት «በኢትዮጵያ የሚታየው የወጣት ስራ አጥነት አሃዝ ከተቀረው አፍሪካ አንጻር» በሚል ርእስ በአማርኛ ተርጉሞ ለንባብ አብቅቶታል።  ጽሑፉ ሥራ አጥነት ከአፍሪቃ በኢትዮጵያ ብቻ መቀነሱን ያትታል። 

የኢዜአ ጽሑፍ «የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በ2015 አስር ነጥብ ሁለት የነበረውን የወጣት ስራ አጥ ቁጥር በ2016 ወደ 6,5 በመቶ እንዲቀንስ አድርጎታል፤ ይህም ከሌሎቹ ሃገራት አንጻር ሲታይ የወጣት ስራ አጦች ቁጥርን አሻቅቧል እንድንል አያደርገንም» በማለት የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ተጠባባቂ ኃላፊ ሪቻርድ ሙራይ ለዘጋቢው ነግረውታል ይላል። ኳርትስ በኢንተርኔት ያስነበበው እና የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎችየተቹት ኢዜአ የተረጎመው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ መልእክት እርስ በእርሱ የተጣረሰ ነው።  

ግብርና በኢትዮጵያ 80 በመቶ የሥራ ኃይል የተከማቸበት መኾኑን የሚገልጠው የኳርትዝ ዳት ካም ጽሑፍ፦«ይኽ ማለት በኢትዮጵያ በ2015 የነበረው 10.2% አጠቃላይ ሃገራዊ ምርት እድገት GDP በ2016 ወደ 6.5%  ሲኮማተር የወጣት ሥራ አጥነቱ እጅግ አልናረም» ሲል ይነበባል። በአቤኔዜር ትዊት አስተያየት መስጫ ስር የሞ ኢብራሂም ጽሑፍ በ2016 በኢትዮጵያ የወጣት ሥራ አጥነት መጠን 8,1 በመቶ እንደሆነ ይጠቅሳል።

የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ አመራር አቶ ሐብታሙ አያሌው  በዩናይትድ ስቴትስ ያሰሙት ንግግር የቪዲዮ ምስል በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ከተሰራጨ በኋላ በሰፊ ሲያነጋግር ከርሟል። በንግግሩ ላይ የመንግስት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል። 

አቶ ሐብታሙ በእስር ቤት የደረሰበት በደል እና ሰቆቃ በቃል የሚገለጽ አይደለም፤ ጀግናችን ነው ያሉ አስተያየት ሰጪዎች በርካቶች ናቸው። አቶ ሐብታሙ በተለይ በእስር ቤት ውስጥ ስቃይ የሚፈጽሙ ሰዎች አብዛኞቹ ከአንድ ብሔር የመጡ መሆናቸውን የገለጡበት ንግግር በተቃዋሚ እና በደጋፊዎች ዘንድ ይበልጥ ትኩረት አግኝቷል። በንግግሩ የአንድ ብሔርን ተጠያቂ አድርጓል፤ ያን ያደረገውም በዳይስፖራው ፖለቲካ ተደማጭ ለመሆን እና ለመጠቀም ነው ከዕውነት የራቀ ነው ሲሉ አስተያየት የሰጡ አሉ። ይህን አጥብቀው የሚቃወሙ አስተያየት ሰጪዎች የለም ሐብታሙ ግፍ በሚፈጸምባቸው እስር ቤቶች ያለውን ዕውነታ ነው የተናገረው ከሐቁ ጋር መጋፈጡ ነው የሚበጀን እንጂ  መሸሹ አያዋጣንም ሲሉ ተደምጠዋል። 

ከእስር ቤት ጉዳይ ሳንወጣ በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ሰሞኑን  በእጅ ጽሑፉ ያቀረበው እንደሆነ የተነገረለት መልእክት በኢንተርኔት በስፋት ተሰራጭቷል። «እኔ እና ዳንኤል ሺበሺ ባለቤት አልባ የግፍ እስረኞች ሆነናል» ሲል የሚንደረደረው ጽሑፍ፦ጋዜጠኛ ኤልያስ እና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ከታሰሩበት እስር ቤት ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ፤  ከማዕከላዊ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንደተላኩ እና ጉዳያቸውን የሚመለከት እንደጠፋ ይገልጣል። «አምስት ወር በግፍ መታሰራችን ሳያንስ ፣ ለተጠረጠርንበት ጉዳይ እስካሁን መፍትኄ የሚሰጠን አካል በመጥፋቱ በሀገራችን በጣም አዝነናል» ያለው ጋዜጠኛ ኤልያስ ለተሻለ የሀገር ግንባታ ዛሬም ሆነ ነገ ጠንክሮ እንደሚሠራ ገልጧል። የማኅበራዊ መገናኛ አውታር አስተያየት ሰጪዎች ይህ የሚደረገው ሆን ተብሎ እስረኞቹን ለማጉላላት ነው፤  ያለ አግባብ መታሰራቸው ሳያንስ በግፍ ጊዜያቸው እንዲባክን መደረጉ አሳዛኝ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በግብፅ የቅብጥ ኦርቶዶክስ አብያተተክርስቲያናት ላይ በሆሳዕና በዓል አሸባሪዎች በፈንጂ ጥቃት 45 ሰዎችን መግደላቸው በማኅበራዊ መገናኛ አውታር አስቆጥቷል። ብዙዎች በጥቃቱ ሕይወታቸውን ያጡንትን ምዕመናን ሰማእታት እንደሆኑ ገልጠዋል።

በዚሁ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትኩረትን ከሳቡ ጉዳዮች መካከል የጀግናው ሊትዮጵያዊ ሌፍተናንት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ሥርዓተ-ቀብር ይገንበታል። ገና የ15 ዓመት ለጋ ሳሉ የፋሺስት ጣሊያን ወታደሮችን ለመፋለም ዱር ቤቴ ብለው የነበሩት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ  የፋሺስት ወታደሮችን በማርበድበድ «የበጋው መብረቅ» የሚል ቅጽል ስም ያገኙ ጀግና ናቸው። «የተዘነጉ የአፍሪቃ ጀግኖች» በሚል ርእስ ቢቢሲ ከስምንት ዓመት በፊት ባዘጋጀው ዘገባ  ስለ ጀግናው ጃጋማ ኬሎ ዘግቧል። በ1953 ዓም በነበረው መፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ለንጉሠ ነገሥት ዓጼ ኃይለሥላሴ ታማኝ ከነበሩ የኦሮሞ ተወላጆች አንዱ እንደነበሩም በታሪክ ስለመነገሩ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተጽፏል። በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች አንዳንድ ሰዎች ይኽን ታሪክ በማንሳት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎን ለመንቀፍ ቢሞክሩም ጀግንነት ውዳሴው ግን ጎልቶ ወጥቷል። በተለይ ከአዲስ አበባ በ55 ኪሎ ሜትር ርቀት ፋሺስት ወታደሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝረው 72 የጣሊያን ወታደሮችን በመግደል 3,000 ነፍጥ የማረኩበት ታሪካቸው በኢትዮጵያውያንም ኾነ በውጭ ሀገር በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ተስተጋብቷል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች