የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 10.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

አዲስ አበባ ከተማ በጠራራ ጸሐይ በተፈጸመባት ጥቃት ሕይወቷ ያለፈው የ17 አመቷ ታዳጊ ናዖሚ ጥላሁን ጉዳይ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል። አሜሪካዊው ዴቪድ ሽታይንማን  'የኢትዮጵያ መንግሥት ሹማምንት ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ 30 ቢሊዮን ዶላር መዝብረዋል።' ሲሉ በፎርብስ መፅሔት ያሰፈሩት ውንጀላም መነጋገሪያ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:16

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሰዓሊዋ ምኅረት ከበደ አዲስ አበባ ሜክሲኮ አደባባይ አቅራቢያ በ17 አመቷ ታዳጊ ላይ የተፈጸመው ድርጊት እጅግ አስቆጥቷታል። ምኅረት ባለፈው ሰኞ በፌስ ቡክ ማኅበራዊ ድረ-ገፅ ላይ ባሰፈረችው አስተያየት «ታዳጊዋን የገደለው አንድ ግለሰብ ብቻ አይደለም።» ብላለች። በምኅረት አስተያየት ገዳዩ በእንዲህ አይነት ስነ-ልቦና ተቀርፆ እንዲያድግ የተባበረው ማኅበረሰብ ሁሉ  አለበት። ምኅረት ወንድን የበላይ አድርጎ ያነገሰው ማኅበረሰብ ሊለወጥ ግድ ነው የሚል አቋም እንዳላት በዚህ ፅሁፍ ጠቁማለች። ሰላም ሙሴ የተባለች የፌስ ቡክ ተጠቃሚ አስተያየቷን «ከመዘግየቱ በፊት ስለምን አላመለከተችም? ብሎ የሚጠይቅ ይኖራል?» ስትል ጀምራለች። «ምክንያቱም ፖሊስ ሊስቅባት እና ወድዷት እንደሆነ ብቻ ሊነግራት ይችላል።» ስትል መሰል ጥቃቶች ቀድሞ ለመከላከል አስቸጋሪ ነው ብላ እንደምታምን ገልጣለች። በሰላም እምነት ታዳጊዋ ሥጋቷን ለፖሊስ ብትገልጥ እንኳ «ጥቃት እስካልፈጸመብሽ ድረስ ምንም ልናደርግ አንችልም።» የሚል ምላሽ ሊሰጧት ይችላሉ የሚል እምነት እንዳላትም የግል አስተያየቷን አስፍራለች። 

በማኅበራዊ ድረ-ገጾች በስፋት የተሰራጨው የኢትዮጵያ ኦብዘርቨር ዘገባ እንደሚጠቁመው የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ናዖሚ ጥላሁን አንገቷ ላይ በስለት በተፈጸመባት ጥቃት ሕይወቷ አልፏል። ታዳጊዋ ወደ ባልቻ ሆስፒታል ብትወሰድም ሕይወቷ ሊተርፍ አለመቻሉን ድረ-ገፁ አስነብቧል። የናዖሚ ጓደኞች ጥቃት ፈፃሚው «እወድሻለሁ» ባይ እንደነበር ለድረ-ገፁ ነግረውታል።

አዲስ አበባ እንዲህ በመውደድ እና በፍቅር ስም ጥቃት ሲፈጸምባት የመጀመሪያው አይደለም።  ከሶስት አመታት በፊት ሐና ላላንጎ የተባለች የ16 አመት ታዳጊ በተፈጸመባት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሕይወቷ ማለፉ አይዘነጋም። በአደባባይ በቀድሞ የትዳር አጋሯ በበርካታ ጥይቶች የተገደለች እናት፤ በአፍሪቃሪዋ ፊቷ ላይ አሲድ የተደፋባትን ወጣት አዲስ አበባ ታውቃለች። እንዲህ አይነት ጥቃቶች መቆም አለመቻላቸው ካሳሰባቸው መካከል ዶ/ር እሌኒ ዘውዴ ይገኙበታል። የኤኮኖሚ ባለሙያዋ የዓለም ሴቶች ቀን ሲከበር በፌስ ቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ «በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት ዛሬም በመኖሩ ልቤ ያዝናል። የአሁኑ ደግሞ ያስደነግጣል። ፊታችንን ባዞርንበት ሌላው የዓለም ክፍል የሚፈጸሙትም እንደዚያው።» ብለዋል። ዓለም ከሌላው ጊዜ በተለየ እኛን ትሻለች» ያሉት ዶ/ር እሌኒ የሴቶችን መብት ለማስከበር ትግሉን መቀጠል ያሻል ሲሉ ኃሳባቸውን ጠቅልለዋል።

Äthiopien Solar

«ወንዶች እና ሴቶች ልጆቻችንን ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ነገር አስቀድመን ልናስተምር ያሻል።» ያለችው ደግሞ ድምፃዊት ሙኒት መስፍን ነች።/ ድምፃዊቷ እንዲህ አይነት ጥቃቶች ከመፈጸማቸው በፊት ልጆች ከወላጆች ጋር የሚነጋገሩበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግም ጠቁማለች። እንዲህ አይነት አሰቃቂ ጥቃቶች መደጋገማቸው «አሳዛኝ» ነው ያለችው ሙኒት ለውጥ ያስፈልጋል ብላለች። 

ግርማ አበበ «በጣም አሳዛኝ እና የሚያስቆጣ ድርጊት፡፡እውነተኛ አፍቃሪ፦ ሲሰደብ ዝም የሚል፣ቢጎዳ የሚበቀል ሳይሆን ለወደዱት መድከም እረፍት መሆኑ የሚገባው፣ በጣም ትዕግሥተኛ፣ ከዚህም በላይ እሷን ቢያጣ እንኳ ምርጫዋን የሚያከብር ነዉ፡፡ ማንኛችንም ብንሆን ለራሳችን እንዲሆንልን የምንመኘውን ለሌላው ብናስብ እንኳን መግደል ጥላቻም በውስጣችን አይፈጠርም፡፡ሴት ልጅ እኮ እናት፤እህትም ናት፡፡የፍቅር አምላክ ለገዳዮቿ የንሥሓ ልብ አና አስተማሪ ፍርድ እንዲሁም ለቤተሰቦቿ መጽናናትን ይስጣቸው፡፡» ሲል አስተያየቱን አስፍሯል። ሲያን ኤ ባሪ «በፍቅር ስም መግደል-አሁን በሰው ላይ ተስፋ ቆረጥኩ» የሚል አስተያየቷን በትዊተር አጋርታለች። 

በዚሁ ሳምንት በዕለተ-ረቡዕ ዓለም የሴቶች ቀንን ሲያከብር ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በየአገሮቻቸው ሊታወሱ ይገባቸዋል ያሏቸውን ግለሰቦች አጋርተዋል። መቀመጫዋን በስዊድን ያደረገችው እና የኤረና ራዲዮ አቅራቢዋ ሜሮን እስጢፋኖስ ከጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በኤርትራ በእስር ላይ የምትገኘውን ወጣት 'ልቀቁ' የሚል አቋሟን በትዊተር አጋርታለች። ሜሮን በፎቶ ግራፍ አስደግፋ ባሰራጨችው መልዕክት የቀድሞው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒሥትር ልጅ የሆነችው ሲሐም በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም. ስትታሰር የ15 አመት ታዳጊ እንደነበረች አስፍራለች። አባቷ አሊ አብዱ የሚያገለግሉትን መንግሥት ጥለው በመኮብለላቸው ከአያቷ እና አጎቷ ጋር ለእስር የተዳረገችው ሲሐም ምንም አይነት ወንጀል አልፈጸመችም ብላለች-ሜሮን።

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ንቁ ተሳታፊው ኪሩቤል ተሾመ እድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙትን ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙን አስታውሷል። ወ/ሮ እማዋይሽ ሕገ – መንግስቱን በኃይል ለመናድ በሕቡዕ ሰርተዋል በሚል በእነ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ መዝገብ የተከሰሱት ናቸው ። 25 ዓመት እስር የተፈረደባቸው ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ዛሬም እስር ላይ ይገኛሉ። ኪሩቤል ወይዘሮዋን በዘከረበት የትዊተር አጭር መልዕክት «የአራት ልጆች እናት የሆኑት እና የ51 አመቷ ወይዘሮ እማዋይሽ አለሙ አሰቃቂ እና ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ማሰቃየት የሚፈጸምባቸው የፖለቲካ እስረኛ ናቸው።» ብሏል። 

Parlamentswahl in Äthiopien (hier: Anhänger der Regierungspartei)

ጋዜጠኛ በላይ ማንአየ «ልጅ በጀርባ አዝላ፣ የኩበት ጭስ ዓይኑዋን እየለበለበው፣ ባሉዋ 'ቶሎ በይ ቁርስ አቅርቢ' እያለ ዱካ ላይ ተዘርፍጦ ለሚያንባርቅባት፣....ለዚያች እናት ቀን መቃናት እንዲሆን ማርች 8!» የሚል ፅሁፍ በትዊተር አስነብቧል።

የሲራክ ተመስገን የፌስ ቡክ ፅሁፍ ደግሞ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በሴቶች ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ ብዙ መንገድ ይቀረዋል የሚል አንድምታ አለው። ሲራክ «ቦሌና ፒያሳ የሚውል ወንድ፣ ሴትና ወንድ እኩል የሆኑ ይመስለዋል። በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ወንዱ አሁንም የተሻለ እድል አለው። መአት ምክንያቶች መደርደር ይቻላል። ለዛሬ ይህን እንይ… በአቅራቢያችሁ ወደሚገኝ ት/ቤት ሂድ። ሄዳችሁም የአመቱ መጀመሪያ የተመዘገቡ ተማሪዎችን ቁጥር በፆታ አሳዩኝ በሉ። የአመቱ መጨረሻ ላይ ተመልሳችሁ ሂዱና አሁንም ዳታውን እዩ። ብዙ ያቋረጠ እና የደገመ ቁጥር የምታገኙት ሴት የሚለው ምድብ ላይ ነው። አመቱ መጨረሻ ድረስ መጠበቅ ያልቻለ ሰው ያለፉ አመታትን ዳታ አሳዩኝ ይበል። ለምን ያቋርጧሉ? ለምን ይደግማሉ? መልሱ እዚህ ላይ ነው። ኢኮኖሚያዊው፣ ማህበራዊው… ጫና ከወንዱ ይልቅ ሴቱ ላይ ይበረታል። ሴቶች እንዳይበቁ ገና ከስሩ ይቀጫሉ!» ሲል ሐሳቡን ገልጧል። 


እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic