የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 23.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

121ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ሐሙስ የካቲት 23 ቀን፣ 2009 ዓም ዓ.ም. ይከበራል። የአድዋ ድል ኢትዮጵያዉያን የኢጣሊያን ወራሪ ቅኝ ገዢ ጦርን አድዋ ላይ ድል ያደረጉበት ድንቅ የታሪክ ክስተት ነው። የአድዋ ድል የተመዘገበበት የየካቲት ወር ግን የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎችን እዚህ እና እዚያ ማላተም ከጀመረ ሰነባብቷል። ዳስሰነዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:02

ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሳምንቱ ውስጥ

121ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የፊታችን ሐሙስ የካቲት 23 ቀን፣ 2009 ዓም ዓ.ም. ይከበራል። የአድዋ ድል ኢትዮጵያዉያን የኢጣሊያን ወራሪ ቅኝ ገዢ ጦርን አድዋ ላይ ድል ያደረጉበት ድንቅ የታሪክ ክስተት ነው። የአድዋ ድል የተመዘገበበት የየካቲት ወር ግን የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎችን እዚህ እና እዚያ ማላተም ከጀመረ ሰነባብቷል። ዳስሰነዋል። በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳግም በሀገሪቱ በተቀሰቀሰው የውጭ ሃገራት ነዋሪዎች ጥላቻ የጥቃት ስጋት አንዣቦባቸዋል። በሣዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በእስር ቤቶች እየማቀቁ እንደሚገኙ መሰማቱም ሌላ ያነጋገረ ጉዳይ ነው። ቃኝተነዋል። በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የተነሱ ሌሎች ርእሰ-ጉዳዮችንም ተመልክተናል።  

የካቲት ወር በገባ ቊጥር ፌስቡክ እና ትዊተር የኢትዮጵያውያን መወዛገቢያ መኾን ከጀመሩ ሰነባብተዋል። የአድዋ ድል በዓል ድምቀቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚወሰን ሳይኾን የጥቁር ሕዝቦችም ኩራት ነው የሚሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች አድዋን በኩራት ሲያወድሱ ይታይል። በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አድዋ ሲነሳ የዳግማዊ ዐጼ ምንሊክ እና የእቴጌ ጣይቱ ገናና ስም  አብሮ በክብር ይነሳል።

በሌላ ወገን ደግሞ የዳግማዊ ምንሊክ ስም አይነሳብን የሚሉም አልታጡም። የካቲት ወር ከአድዋ ድል ባሻገር በጀግኖች አርበኞች ሰማእታት ቀን መታሰቢያነትም ይዘከራል።  የህ.ወ.ሓ.ት የምስረታ በዓልም በዚሁ በየካቲት ወር ነው። ወደ ኋላ ሩቅ ከተኬደም ግብታዊው አብዮት በኢትዮጵያ የፈነዳው በየካቲት ወር ነበር። የካቲት በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲህ በተዛነቀ መልኩ ከመታየትም አልፎ ብዙዎችን ሲያነታርክም ይስተዋል። 

አፈንዲ ሙተቂ የየካቲት ወር ንትርክን በመታዘብ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዲህ ሲል ትችቱን አስፍሯል። «የካቲት በመጣ ቁጥር ውዝግብ አድዋ ኦፊሴላዊ የድል በዓል ነው። ከርሱ በስተቀር በኢትዮጵያ ምድር በየካቲት ወር የሚከበር ሌላ በዓል የለም። ነገር ግን ፌስቡከኛው ማኅበር የካቲትን መወዛገቢያ አድርጎታል። ከአድዋው ድል በላይ ውዝግቡ ነው የሚጦዘው። ዘይገርም ነገር!!»

የአድዋ ድልን አስመልክቶ ከቀረቡ አስደማሚ ምስሎች መካከል፦ «ሴትነት ! ድሮና ዘንድሮ» በሚል ርእስ አርበኞች ሴቶች ነፍጥ አንግበው የሚታዩበት ምስል የሺሻ ዘንግ አፋቸው ላይ ሰክተው ጢሱን ከሚያንቧልሉ «ዘመናዊ» ሴቶች ጋር በተነጻጻሪነት መቅረቡ ይገኝበታል።

ከአርበኞቹ ሴቶች ጋር የተያያዘው ጽሑፍ፤ «ክብር ለእናንተ ይሁን! እናንት ጀግና ኢትዮጵያውያን እናቶቻችን» ይላል። ከሺሻ ማጊዎቹ ሥር ደግሞ፦ «የዶሮ ማነቂያና የቺቺንያ ነፃ አውጪ ግንባር አባላት በከፊል» የሚል አጭር የጽሑፍ መግለጫ ይገኛል። ዘመድኩን በቀለ ነው በጽሑፍ የተደገፈውን ምስል በፌስቡክ ገጹ ያቀረበው።

በሳውዲ አረቢያ በእስር ላይ ስለሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን  በተመለከተ በዶይቸ ቬለ የፌስቡክ ገጻችን ላይ መረጃ እና ጥቆማ እንድታደርሱን የሚጠይቅ ጽሑፍ አስፍረን ነበር። በርካታ አስተያየቶች ልካችሁልናል። የተወሰኑትን እናቀርባለን።

በሙሐመድ እድሪስ አስተያየት እንጀምር። «በሀገራችን ያለተከበረን በሰው ሀገር በንሰቃይ ምኑ ይገርማልብቻ ጌዜ ይፍታው የኢትዮጵያን ነገር» ሲል  አጭር መልእክቱን አስፍሯል። ብርትኳን ማሬ በበኩሏ፦ «እያንዳዳችን ለመኖር ብለን የምንወሰነው ውሳኔ ዋጋ ያስከፍለናል ከመወሰናችን በፊት ማሰብ ግድ ይለናል እግዛብሄር ይርዳን እኛ ለመወሰን እራሳችን እንወቅ» ብላለች። ኢዮአታም ይሳኮር ደግሞ፦ «ወገኖቼ ከዚሁ ከአገራችን ላይ ተስማምተንና ተግባብተን ብንኖር እኮ ይህ ሁሉ ነገር ባልተፈጠረ ነበር» የሚል አስተያየት አስፍሯል፡፡

«አያድርስ ብንል የሚቀል ይመስለኛል አብዛኞቻችን የጻፍነው ወገንተኝነትን ይመስላል ዳሩ ግን ሁሉም ኢትዮጲያዊ እህቶችና ወንድሞች ለሁላችንም እህትና ወንድሞቻችን እስከሆኑ ድረስ ሁላችንም በምናምነው አምላክ ስም ብንጸልይ ይሻላል ስቃዩን ለማወቅ ግድ መሰደድ ወይም መታሰር አይጠበቅብንም አምላክ የታሰሩትን በምህረቱ ይጎብኝልን አሜን» የሚለው መልእክት በራስ ተፈሪ የቀረበ ነው።ተስፋዬ እሸቱ፦«ቸሩ መድሀኒዓለም መፍትሄ ያምጣላቸዉ ነገር ግን ችግሩን መንግስት ጋር ብቻ ከማነጣጠር በዚህ ጉዳይ የእኔ ድርሻ ምንድን ነወ? ማለት አለብን» ሲል ሳሚ ኡመር፦«ለእንደዚህ ዓይነት ችግሮች ነበር ኤምባሲ ያስፈለገው እንጂ በየሀገሩ ቴሌቶን አዘጋጅቶ ገንዘብ ለመሰብሰብ አይደለም« ብሏል»።

አቡ አቡ አማር የተባለ አስተያየት ሰጪ፦ «ከኢትዮጵያ ኑሮ የሰዑዲ ዐረቢያ እስር ቤት ይሻላል ሁሉም ኑሮነው ብዙ አትጨናነቅ» ብሏል። የኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ኑሮ እና ፍዳ በሳዑዲ አረቢያ አያበቃም። በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ከወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚሰማውም ብዙዎችን ያስደነገጠ ነው።

በደቡብ አፍሪቃ ዳግም እንደተቀሰቀሰ በተነገረለት የውጭ ሃገራት ነዋሪዎች ጥላቻ ኢትዮጵያውያን ጥቃት እንዳይደርስባቸው የሚያስጠነቅቁ ጽሑፎች በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ተሰራጭተዋል። ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለይ ትናንት ሐሙስ እና ዛሬ ነቅተው እንዲጠብቁ የሚያስጠነቅቁ ጽሑፎች ተሰራጭተዋል። በደርባን በፖሊስ ኃይል እንዲሁም ጦር ሠራዊቱ እና ስደተኛ ለማጥቃት ባሰፈሰፉ ሰዎች መካከል ፍጥጫው ማየሉንም ጠቅሰዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች