የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 23.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ጦማሪያን እና የፖለቲካ አቀንቃኞችን ጨምሮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታስረው የነበሩ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች የመለቀቃቸው ዜና እና የጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ መመረቅ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ጎልተው የወጡ የሳምንቱ መነጋገሪያ ርእሰ ጉዳዮች ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:18
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:18 ደቂቃ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አበይት መነጋገሪያዎች

በኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለእርስር ከተዳረጉ እስረኞች መካከል  ገዢው ፓርቲ ከ4 ሺህ በላይ «አሰልጥኜ» ፈታሁ የማለቱ ዜና የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኗል። ከእስረኞቹ መካከል ታዋቂ ጦማሪያን እና የፖለቲካ አቀንቃኞች እንደተፈቱ መሰማቱም በስፋት መነጋገሪያ ኾኗል። የጊቤ ቁጥር ሦስት የኃይል ማመንጫ ግድብ መመረቅ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሌላኛው የሳምንቱ የመነጋገሪያ ጉዳይ ነበር።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለእስር ከተዳረጉ በሺህዎች የሚቆጠሩ እስረኞች መካከል ከአራት ሺህ በላይ የሚሆኑት መለቀቃቸው መሰማቱ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በስፋት አነጋግሯል።

በዶይቸቬለ የአማርኛ ቋንቋ የፌስቡክ ገጽ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ገላዬ ሚደቅሳ አጠር ባለ መልእክቱ፦ «አረ ወንድሜን ልቀቁልኝ» ብሏል። አብርሃም ዓለሙ፦ «አዉቀዉም ሆነ ሳያዉቁ በመንግስትና በህዝብ ላይ በደል ያደርሱት ወገኖች በሚገባ ተምረዉ ሲፈቱ የተሻለ ዜጋ ይሆናሉ!» ብሏል። ጀሚል ጀሚል «ህፃናቶችንና ወጣቶችን የፈጀ ቀሪውን ለስደት ለከፋ ስቃይና ለባህር አሳ ቀለብ እዲሆኑ የወሰነ ጨካኝ መግስት ፈጣሪ ሰላሙን ያምጣልን» የሚል መልእክት አስፍሯል። «ባይፈቱ ይሻላል አቦ» ሲል አስተያየት የሰጠው ደግሞ  ዎሾም ጆራ  ነው። ሽኩር የሙሉ ልጅ፦ «አረ የሰዉ ያለህ ያገሬ ልጆች አብሮ አደጎቸ ናፈቁኝ ይፈቱልን አላህ ይርዳችሁ ወዳጆቸ» የሚል መልእክት አስነብቧል።

የዞን ዘጠኝ ጦማሪው በፍቃዱ ኃይሉ የመፈታቱን ዜና ሐሙስ ዕለት አዲስ ስታንዳርድ በትዊተር ገጹ ሰበር ዜና ሲል ነው ያቀረበው። «የዞን ዘጠኝ ጦማሪ እና የመብት ተሟጋች በፍቃዱ ኃይሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከ34 ቀናት እስር በኋላ ተለቋል» ሲል አዲስ ስታንዳርድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ አስነብቧል።

የዞን ዘጠኙ ጦማሪ ዘላለም ክብረት በበኩሉ፦ «ያለማስረጃ ለ40 ቀናት እና 39 ሌሊቶች ከታሰረ በኋላ  ጓደኛዬ በፍቃዱ ኃይሉ በስተመጨረሻም ተፈትቷል ሲል በእንግሊዝኛ ጽፏል። እናም እኔ» ከሚለው ጽሑፉ ስር ብሎ ስክስታ የሚወርድ አጠር ያለ ቪዲዮ አያይዞ አስገብቷል።

ደብረብርሀን  ብሎግ ስዩም ተሾመ፣ ኢያስፔድ ተስፋዬ፣ ብሌን መሥፍን እና ፍቃዱ ኃይሉ መፈታታቸውን በመግለጥ «ዘላለም ወርቃገኘሁንም አሁኑኑ ፍቱ» ሲል በትዊተር ጽፏል።

አምደ-መረብ ጸሐፊው እና የዩኒቨርሲቲ መምህሩ ስዩም ተሾመ በፌስቡክ ገጹ «ክቡራት እና ክቡራን ተመልሼ መጥቻለሁ! ሁላችሁንም አመሰግናለሁ!» የሚል መልእክት ጽፏል። የሆርን አፍሪቃ ድረ-ገጽ ጦማሪ ዳንኤል ብርሐኔ፦ «የሚያምንበትን በመናገሩ ታስሮ የነበረው የሆርን አፍሪቃ  ጦማሪ ሥዩም ተሾመ  ከሁለት ወራት ሕገ-ወጥ እስራት በኋላ ተፈትቷል» ሲል አስነብቧል።

ጋዜጠኛ መሐመድ አዴሞ በትዊተር ገጹ፦ «የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቁም ነገር መታየት እና ጸጥታን ማስፈን የሚሹ ከሆነ፤ በቀለ ገርባ፣ መረራ ጉዲና እና ሌሎች ፖለቲከኞችን ሊፈቱ ይገባል» ብሏል።

በምጸታዊ ጽሑፎቹ የሚታወቀው አበበ ቶላ ፈይሳ በፌስቡክ ገጹ ቀጣዩን መልእክት ከፎቶግራፍ ምስል ጋር አያይዞ አስነብቧል።

«አፈር ስሆን አንድ የማላልፋት ጉዳይ ሆናብኝ ነው ጣልቃ አስገቡኝ... እሱማ አዎ ተጠፋፍተናል... አሁንም ድንገት ነው የተከሰትኩት አንድ የምተኩሳት ጉዳይ አለችኝ እሷን በቅጡ ካገባደድኩ በኋላ እንደልባችን እንገናኛለን... የገረመኝ ነገር... ዛሬ በኮማንድ ፖስቱ ታስረው የነበሩ በርካታ ነጹሃን መፈታታቸውን ሰማሁ፤ እሰይ እሰይ! የገረመኝ ነገር... ሰዎቹን ያለበሷቸው ቲሸርት፤ ምን ብለው ቢጽፉበት ጥሩ ነው፤ «አይደገምም!» እስቲ ማነህ አንድ ጥሩ ሰው... ለአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ... «ምን አቀበጠኝ!» የሚል ቲሸርት አዘጋጅልን!» ይላል አበበ ያሰፈረው ጽሑፍ። አበበ ምንጭ ጠቅሶ ከጽሑፉ ጋር አያይዞ ያቀረበው ምስልም ነጭ ካናቴራ የለበሱ በእድሜ የገፉ ሰዎች ይታዩበታል፦ ልብሳቸው ላይ «አይደገምም» የሚል ጽሑፍ ይነበባል።

«የተቃውሞ ድምጾችን ለማፈን» የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጭር ዳሰሳ፡- አዲስ አበባ እንደማሳያ» በሚል ርእስ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት በድረ-ገጽ ዘለግ ያለ  ጽሑፍ ይዞ ቀርቧል። ጽሑፉ «የአዋጁ ዓይነት፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤  የታወጀበት ጊዜ፡- መስከረም 28/2009 ዓ.ም ተፈጻሚ የሚሆንበት ጊዜ፡- ከመስከረም 27/2009 ዓ.ም ጀምሮ በሚታሰብ ለስድስት ወራት የሚቆይ፤ የተፈጻሚነት ወሰን፡- በመላ ኢትዮጵያ፤በተወካዮች ም/ቤት የጸደቀበት ዕለት፡-ጥቅምት 10/2009 ዓ.ም» በማለት ይንደረደራል።

«የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 93 (1) ላይ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይደነግጋል» በማለት የሚያብራራራው ጽሑፍ በአንቀጹ መሰረት «የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ የሚገባው (የሚችለው) ‹‹የውጭ ወራሪ ሲያጋጥም ወይም ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ስርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማነኛውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት» ነው ይላል፡፡

[በአሁንኑ ወቅት] ‹የውጭ ወራሪም ሆነ የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ› ባይከሰትም፣ መንግስት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮምያና አማራ ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶ የገጠመውን ህዝባዊ ተቃውሞ፣ በተለይም በኦሮሞ የኢሬቻ በዓል አከባበር ወቅት ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ቁጣ፣ ‹ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ› ነው በሚል ሰበብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጅ ችሏል» ሲልም ያብራራል።

በአዲስ አበባ ከታሰሩት በርካቶች መካከል ለማሳያነት በሚልም የተወሰኑ ሰዎችን ስም ዝርዝር ይዞ ወጥቷል። ጽሑፍ የአብዛኞቹ እስረኞች  የፍርድ ቤት መብታቸው እንዳልተከበረላቸው በመጥቀስ «አዲስ አበባም ሆነ ከአዲስ አበባ ውጭ የታሰሩት ሰዎች በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ በተለያዩ የወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት (ማጎሪያ ማዕከላት/concentration camp) ተግዘው፣ ጠያቂ ተከልክለው፣ ያሉበት ሁኔታ በውል ሳይታወቅ ወራትን እያስቆጠሩ ነው» ሲል ተደምድሟል።

የጊቤ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ምረቃን በተመለከተ በብዙዎች ዘንድ የተለያዩ ስሜቶች ተንጸባርቀዋል። የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች እና አባላት ደስታቸውን ሲገልጡ የመንግሥት ተቺዎች፣ ተቃዋሚዎች እና የውጭ ሃገር ጸሐፍት ግድቡ ሊያደርስ ይችላል ያሉትን ጉዳት ተንትነው ጽፈዋል።

ሰንደቅ ጋዜጣ በኢንተርኔት ፦ «ጊቤ ሦስት ሲታቀድ 18 ቢሊየን ብር፣ ሲጠናቀቅ 35 ቢሊየን ብር» የሚል ጽሑፍ ለንባብ አብቅቷል። ጊቤ ሦስት ለመጠናቀቅ ዐሥር ዓመት እንደፈጀበት የሚገልጠው ጽሑፍ የግድቡ ምረቃ ዜና የመንግሥት መገናኛ ዘዴዎችን «የአየር ሰዓት አጣብቦ ከርሟል» ይላል።

ፕሮጀክቱ በኬንያ እና ኢትዮጵያ ድንበር የሚኖሩ ሰዎችን ሕይወት የሚያናጋ መዘዝ አለው በሚል» በተደጋጋሚ የተደረጉ ቅስቀሳዎች «አበዳሪ ሀገራትና ተቋማት እጃቸውን እንዲሰበስቡ አድርጓል» ይላል የሰንደቅ ጽሑፍ። ቅስቀሳውም የተሳሳተ አቋም መሆኑን ይጠቅሳል።  «ኬንያዊያን በአካል ፕሮጀክቱን እንዲጎበኙ ጭምር በማድረግ በኢትዮጵያ በኩል የተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ውጤት እንደነበራቸው መካድ አይቻልም» ሲልም ሠንደቅ አክሏል።

በርካታ የውጭ ሀገር የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች  ጊቤ ሦስት በተገነባበት አካባቢ እና በነባር ህዝቦች ላይ «ጉዳት ያደርሳል» የሚል ጽሑፍ ለንባብ አብቅተዋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic